በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው የለውጥ ሂደት የከፈተውን ዕድል በመጠቀም ሕብረቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ለሕዝብ ለማስረዳትና  እንቅስቃሴውን በአገር ደረጃ ለማካሄድ የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት በዛሬው እለት ሦስት የምክር ቤት አባላት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘዋል።

የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገር ህብረት ከአንድ ዓመት በፊት በአሜሪካ ሴያትል ከተማ ውስጥ በአምስት ክፍላተሃገር ተወላጆች በተመሰረቱ ማህበራት የተቋቋመ ህብረት ሲሆን ከዚያ ወዲህ የሌሎቹ ክፍላተ ሃገር ተወላጆች በማህበር ተደራጅተው በመቀላቀል የሕብረቱ አባላት ቁጥር እያደገ በመምጣት ላይ ይገኛል።

 በኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት 27 ዓመታት የሰፈነው የዘርና የጎሳ ፖለቲካ ተወግዶ የአገር አንድነትና የሕዝቡ ሰላማዊ ኑሮ የሚረጋገጥበትን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማስፈን በሚደረገው ትግል የድርሻውን ለማበርከት ሲሆን፣ በቅድሚያ ሕዝብን በጠላትነት ለያይቶ ለማፋጀት የተገነባው ቋንቋ መሰረትን ያደረገው የክልል ግምብ ፈርሶ ሃገራዊ የአንድነት ድልድይ ሊገነባ የሚችለው  በሕዝቡ ነባር ስብጥርና መልክአምድራዊ አቀማመጥ ላይ በተመሰረተው በቀድሞው የክፍላተሃገር አወቃቀር ቢሆን  የተሻለ መሆኑን ያምናል፤ያንንም  ለሕዝቡ  በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ለመግለጽና ለዚያ ውጤት ለማብቃት ጥረት ያደርጋል። 

 የቀድሞ ክፍላተሃገር አወቃቀር ሲባል የቀድሞውን ስርዓት ለመመለስ ሳይሆን፣ ከቀድሞው ታሪክ፣ባህልና ልማድ  መልካሙን እየወሰዱ የሚሻሻለውን በማሻሻል አገርን መገንባት ይቻላል በሚል እምነት በመነሳት  የፌዴራላው አስተዳደሩ ፍጹም ዴሞክራሲያዊና ለሕዝቡ የሚበጅ፣ሕዝቡም የአስተዳደሩ ባለቤት የሚሆንበትን ስርዓት ለማስፈን እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን።የክፍላተሃገር አስተዳደር በሌሎቹም አገሮች የተለመደና ስኬታማ ሰላምና እድገትን ያበሰረ መሆኑን ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና  ከሌሎቹም አገሮች የአስተዳደር አወቃቀር መረዳት ይቻላል።ከሃያ ሰባት ዓመታት በፊትም በስርዓቶቹ ድክመት የተነሳ እድገት ባይታይም አገራችን ሕዝብ ሳይለያይ፣መጤና ባለቤት ሳይባል በሰላም አብሮ የኖረበት አወቃቀር እንደነበረ አይዘነጋም። 

 የክፍላተ ሃገር አስተዳደር አወቃቀር ሌላው ጥቅሙ ሕዝብ ለአነስተኛ ጉዳዩ ከሚኖርበት አካባቢ በብዙ መቶ ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ ከሚገኘው ወደ ክልሉ አስተዳደር ጽ/ቤት የሚጓዝበት አሠራርና  ግዴታ ተወግዶ በሚኖርበት አካባቢ  በመረጠው  አስተዳደር ጥያቄው መልስ የሚያገኝበትንና  ችግሩ የሚፈታበትን ሁኔታ ይፈጥራል።ነዋሪው ሕዝብ በቅርበት አስተዳዳሪዎቹን ለማወቅና ለመቆጣጠር ይችላል።ሁሉም ነዋሪ ለመምረጥና ለመመረጥም መብቱ የተጠበቀ ነው።       

የክፍላተ ሃገሩ ህብረትም ሆነ ልዑካኑ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት እንቅስቃሴ ጋር ያልተያያዘና የማንኛውንም ድርጅት ተልእኮ ለማስፈጸም እንዳልሆነ የክፍላተ ሃገሩ ህብረት ለማሳሰብ ይወዳል።  ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ትኑር!  የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት  ዋና ጸሐፊ  አገሬ አዲስ ነሐሴ 2 ቀን 2010ዓም(08-08-2018)