የጦር መሳሪያዎች ወደ አዲስ አበባ በነዳጅ ቦቴ ሲገቡ በቁጥጥር ስር ዋሉ

አባይ ሚዲያ ዜና

በነዳጅ መጫኛ ተሽከርካሪ ውስጥ ተደብቆ ወደ መዲናዋ አዲስ አባባ እንዲገቡ የተደረጉ የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘገበ።

በህገ ወጥ መንገድ ወደ ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የገቡትን የጦር መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል እንደቻለ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።

አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች  ህዝብን ከህዝብ ለማፋጀት በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያዎች እየገቡ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ ሪፖርቶች ሲጠቁሙ ፤ በተቃራኒው በብዙ ሺህ ዶላር የሚቆጠሩ ገንዘቦች ደግሞ ከአገር ለማሸሽ ሲሞከር እንደነበረም ይታወሳል።

ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 7 ቀን 2010ዓ,ም ድረስ በተደረገ ዘመቻ እንኳን ከ መቶ ሺ ዶላር በላይ ገንዘብ በአዲስ አበባ ቦሌ ማሪፊያ በኩል ለማሸሽ የተደረገ  ሙከራ ለማክሸፍ እንደተቻለ የኢትዮጵያ የገቢዎችና ጉምሩም ባለስልጣን ማሳወቁ አይዘነጋም።

ፖሊስ በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያዎች ወደ አገር ሲገቡ አሊያም በርካታ ገንዘቦች ከአገር ሲወጡ ተያዙ ከማለት በስተቀር ይህን ህገ ወጥ ድርጊቶች ስለ ሚፈጽሙት ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ተጨባጭ መረጃ ለህዝቡ እያካፈለ አይደለም የሚሉ አስተያየቶች በተለያዩ ሚዲያዎች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ።