ክቡር ፕ/ት ዶ/ር ለማ መገርሳ ህገ ወጥ ተግባራትን እና ወንጀልን የሚፈጽሙ አካላትን አስጠነቀቁ

አባይ ሚዲያ ዜና

ክቡር ፕሬዝዳንት ዶክተር ለማ መገርሳ በኦሮሚያ ውስጥ በኦነግ ስም እየተፈጸሙ ያሉትን ውንጀሎች እና ግድያዎች በተመለከተ መግለጫ ሰጡ።

ርእሰ መስተዳድር ክቡር ዶክተር ለማ መገርሳ እየታየ ባለው የወንጀል እና የግድያ ተግባራት ከኦነግ አመራሮች ጋራ ውይይት እንደተደረገ ገልጸዋል።

ከኦነግ አመራሮች ጋራ በተደረገው ውይይት እየተፈጸመ ያለው ህገ ወጥ ተግባራት እና ግድያዎች ከኦነግ አመራሮች እውቅና ውጭ እንደሆነ የኦነግ አመራሮች በውይይቱ እንደገለጹ ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ  መገርሳ በጋዜጣ መግለጫቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ በመንቀሳቀስ እንዲሰሩ በቀረበው ጥሪ መሰረት የኦነግ አመራሮች ወደ አገር እንዲገቡ የተደረገው ጥረት ስኬታማ እንደነበረ የገለጹት ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው የኦነግ ድርጅት ጋር በአስመራ የተሳካ ስምምነት መደረሱን አክለው ገልጸዋል።

በቅርቡ በሻሸመኔ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ አባላትን ለመቀበል በተጠራው ሰልፍ ላይ ቦምብ ይዟል በሚል የተሳሳተ መረጃ በመመርኮዝ በሰልፉ የተሳተፉ ግለሰቦች አንድ ግለሰብን በአሰቃቂ መልኩ ቁልቁል ሰቅለው መግደላቸው ይታወሳል።

በተሳሳተ መረጃ እንዲሁም ያለ ስልጣናቸው ግለሰቡትን ራቁቱን ቁልቁል ሰቅለው ከገደሉት በኋላ አስክሬኑን ከተሽከርካሪ ኋላ በገመድ በማሰር በመንገድ የመጎተት አረመናዊ ተግባር የፈጸሙ ግለሰቦች በህግ እንደሚጠየቁ የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ መግለጻቸው አይዘነጋም።

ከኦነግ አመራሮች ጋር የተደረሰው ስምምነት ህገ ወጥ ተግባራትን ማከናወን እንደማይጨምር የጠቆሙት ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ለማ መገርሳ የተለያዩ ወንጀል እና ስህተት እየፈፀሙ ያሉ አካላት ከዚህ ተግባራቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አስጠንቅቀዋል።