ግልጽ ደብዳቤ ( ከፍትህ ለኢትዮጵያ ግብረኃይል )

ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም.

ለ፦ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
     የኢትጵያ ፌዴራል ሪፑብሊክ ጠቅላይ ሚኒስቴር
     አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

ከ፦ ፍትህ ለኢትዮጵያ ግብረኃይል
     2201 Murfreesboro Pike, Suite A-109

       Nashville, TN  37217

ክቡር ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ፤

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴርነትን ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ በኢትዮጵያችን የፈነጠቀው የዴሞክራሲ የአንድነት የነጻነትና የፍቅር ተስፋ ለምልሞ ፍሬ አፍርቶ ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ገናናነቷ እንደምትመለስ ለሚወድዎት ሕዝብ አብስረዋል፡፡ ለዚህ ለተቀደሰ ታላቅ ግብ አቅም በፈቀደ ሁሉ ከጎንዎ በመቆም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነታችንን እንደምንወጣ እናረጋግጥልዎታለን፡፡

በሀገራችን ቂምና ቁርሾ ቀርቶ አንድነት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲጎለብት በተለያዩ ጊዜ የሚወዱትን ሕዝብ ተማጽነዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ወንጀል ሲሰራ አይቶ ፊትን ማዞር ወይንም አንድ ወንጀል የሰራ ሰው ደግሞ የመከላከል መብቱ ተጠብቆለት በፍ/ቤት ተጠያቂ እንዳይሆን ወይም በበዳይና በተበዳይ መካከል እርቅ ሳይወርድ ወንጀሉ ተዳፍኖ ይቅር ማለትዎ እንዳልሆነ መገመት የቻላል፡፡ ክቡርነትዎ እንደሚታወቀው የአፄ ኃይለሥላሴ ዘውዳዊ መንግስት በሕዝባዊ አብዮት ከተወገደ በኋላ እጅግ ጨካኝና አምባገነናዊ ወታደራዊ መንግስት  በትረ-ስልጣኑን ጨብጦ ለአስራ ሰባት ዓመታት ሕዝብን በተለይም ወጣቱን ጭዳ እያደረገ ሲጨፈጭፍ ሃይ ያለው አልነበረም፡፡ ሃገራችን በተለይም አዲስ አበባ በወጣት የደም ጎርፍ ታጥባለች፡፡ በገጠሩ ወጣቶች በየመንገዱ ተገድለው ተጥለው የጅብ እራት ሆነዋል፡፡ በአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ስሌት መሰረት በመንግስቱ ኃይለማርያም መንግሥት ትእዛዝ 500,000 ኢትዮጵያውያን ተጨፈጭፈዋል። ቀይ ሽብር ተብሎ በተሰየመው ትውልድ የማጥፋት ዘመቻ አባቱ ወይም እናቱ ወይም እህቱ ወይም ወንድሙ ወይም ልጁ በሞት ያልተቀጠፈ ቤተሰብ የለም ማለት ያስቸግራል፡፡ ይህ መዓት ከወረደ እጅግም ሩቅ ባለመሆኑ ዛሬም ወላጅ አልባ የሆኑ ወጣቶች እና ጠዋሪ አልባ የሆኑ አዛውንት በሃዘን ተቆራምተው ያነባሉ፡፡

በ 1983 ዓ.ም የኮሎኔል መንግስቱ አስተዳደር በኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በጦር ሃይል ከተወገደ በኋላ ኢሕአዴግ በትረ ስልጣኑን በጨበጠ ማግስት ኮሎኔል መንግስቱ ወደ ዝምባብዌ ሲፈረጥጥ የተቀሩት የደርግ አባላት ወህኒ ወርደዋል፡፡ ከዚያም አዲስ አበባ በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት መንግስቱን (በሌለበት) ጨምሮ የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ፍ/ቤት ቀርበዋል፡፡ የቀረበባቸውም የክስ መስመር የጦር ወንጀል ሆኖ፤ ሲዘረዘር የዘር ማጥፋት  ወንጀል (genocide)፤  በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል (crime against humanity)፤ ሰቆቃ (torture)፤ ሌሎችም፤ ሲሆኑ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ አይደለንም ሲሉ ጠበቃ ቆሞላቸው እንዲከራከሩ ተደርጓል፡፡ የደርግ አባላቱ በሙሉ፤ መንግስቱ ኃይለማርያም ደግሞ በሌለበት ጥፋተኛ ተብለው በአብዛኛዎቹ ላይ የሞት ቅጣት ተበይኖባቸዋል፡፡  ሆኖም የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በሚደነግገው መሰረት የሞት ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮ፤ የእስራቱ ጊዜም በአመክሮ ተቀንሶ እጃቸው ከተያዘ ከአስር ዓመት በኋላ ከእስር ተፈትተዋል፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም ክሱን ሳይከራከር የሞት ፍርድ ተፈርዶበት  ፍርዱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮለት አንድም ቀን ሳይታሰር አሁንም ዝምባብዌ እየኖረ ለዓለም አቀፍ  መገናኛ ብዙሃን ዝንብም አልገደልኩም፤ እያለ በግፍ በተጨፈጨፉት ንጹህ ኢትዮጵያውያን ላይ ያፌዛል፤ ያላግጣል፡፡ በመሆኑም እስከ ዛሬ በመንግስቱ ኃይለማርያም ላይ ሕግ የሚፈቅደው ምንም እርምጃ አለመወሰዱ ኢሕአዴግ ለፍትህ ያለውን ግዴለሽነት ያመለክታል፡፡

ክቡርነትዎ በተደጋጋሚ በሀገራችን ፍትህ እንዲሰፍን ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል የገቡ ሲሆን የኮኔሌል መንግስቱ የፍርድ ውሳኔ እንዲፈጸም ማድረግ የዚሁ ቃል አካል ነው፡፡

ስለሆነም በ “ፍትህ ለኢትዮጵያ ግብረኃይል” አመለካከት ለፍትህ ሲባልና ለወደፊቱ በኢትዮጵያ መሪዎች ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይደገም ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት መፍትሄዎች አንዱ ይተገበር ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

  • ከዚምባብዌ መንግስት ጋር በመደራደር ኮኔሌል መንግስቱ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የፍርድ ውሳኔ እንዲፈጸምበት ማድረግ፡፡
  • የቻዱ ፕሬዘዳንት ሁሴን ሀብሬ የሃገሩ የቻድ ፕሬዘዳንት በነበሩበት ወቅት ለፈጸሙዋቸው ወንጀሎች ጎረቤት በሆነው በሴኔጋል የተባበሩት መንግስትና የሴኔጋል መንግስት ትብብር ባቋቋሙት ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦባቸው እንደተፈረደባቸው ሁሉ መንግስቱም በተመሳሳይ መልኩ በአንድ በጎረቤት ሃገር ክስ እንዲቀርብበት በአክብሮት ስናሳስብ አላማችን ቂም በመቋጠር በቀል ለመወጣት ሳይሆን በአገራችን ፍትህ እንዲሰፍን ማንም ሰው ለሰራው ወንጀል የመከላከል መብቱ ተጠብቆለት ተጠያቂ እንዲሆን በአክብሮት ለማሳሰብ ብቻ ነው፡፡

ከታላቅ አክብሮትና አድናቆት ጋር፤
ፍትህ ለኢትዮጵያ ግብረ ኃይል
ሊቀመንበር – አምባሳዶር እምሩ ዘለቀ

የቦርድ አባላት   
አቶ ኪዳኔ አለማየሁ፤

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፤

ዶ/ር ምስማኩ አሥራት፤ 

አቶ ተስፋሚካኤል መኮንን፤

አቶ ፀሐይ ደመቀ፤

አቶ ነሲቡ ስብሐት

ግልባጭ፤
ለኢትዮጵያ ኤምባሲ

3506 International Drive, NW

Washington, DC 20008, USA

ለኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ሚስዮን

866 2nd Ave #3,

New York, NY 10017, USA

ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

P.O.Box 393

Addis Ababa, Ethiopia