ሕግና ስርዓትን የማያቅ መንጋ ፖለቲካ በኢትዮጵያ መቆም አለበት

ለሳምንታት ከሕዝብ ዕይታ ጠፍተው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲጨነቅላቸው የነበሩት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይል ዋና አዛዥ የሆኑት ዶር አብይ ዐህመድ በጦር ኃይሎች የ 11ኛ እና የ12ኛ ዙር ስታፍ መኮንኖችን በመረቁበት ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት በመቅረብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለሰራዊቱ እንዲሁም ለፖለቲካ መሪዎች የሕግ የበላይነት መከበር እንዳለበት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተመራቂዎቹ በአደረጉት ንግግር የአንድ ሰራዊት ዘመናዊነት እና ብቃት የሚለካው ፕሮፌሽናል ተቋምን በመገንባት በመሆኑ የዛሬ ተመራቂዎቹ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ሰራዊቱ በምትገቡበት ጊዜ ፕሮፌሽናል አርሚ እንድትገነቡ አደራ እላለሁ በማለት ለተመራቂዎቹ አሳስበዋል።

ሰራዊቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገነባ እንዲሆን ሳይንሳዊ የሆነ ተቋም መገንባት ያስፈልጋል። በመሆኑም ሕገ መንግስታዊ መብቱን የማያውቅ ሰራዊት ግዴታውን ያላከበረ ጦር ግዳጁን በትክክል ይወጣል ለማለት ያስቸግራል ሲሉ በንግግራቸው ገልጸዋል።

ይህ በመሆኑም የዛሬ ተመራቂዎች መብትና ግዴታችሁን በማወቅ ሕገ መንግስቱን በመረዳት ወደ ሰራዊቱ በመሔድ ለሰራዊቱ ይህንንው ማስተማር አለባችሁ ሲሉም አክለዋል።

እንደመር ይቅርታ እናድርግ ስንል ልቅ እንውጣ መረን እንሒድ በየከተማው ሽፍታ ይበራከት ማለት አይደለም። መንግስት ሕግን የማስከበር ግዴታ አለበት በማለት አጽንዎት በመስጠት ተናግረዋል።

ወታደራዊ አመራሩ ከሳይንስ እና እውቀት ባሻገር የፖለቲካ አመራሩን ፍላጎት እና የፖለቲካ አቅጣጫ በሚገባ የማወቅ እና የመተንተን አቅም ሊኖረው ይገባል ካሉ በኋላ አያይዘውም ይህን የተረዳ የጦር መኮንን ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋትም ገልጸዋል።

ከመስከረም በኋላ ሰራዊቱ ሕብረ ብሔራዊ እንዲሆንም የሪፎርም ሥራ መጀመሩን እና አዲስ የሰራዊት ኃይል ጨምሮ እንደሚገነባም ገልጸዋል።

ከተመራቂዎቹም በከፍተኛ ውጤት ያመጡትን እና እንስት ተመራቂዎችን ሽልማት እና የውጭ አገር ጉብኝት እንዲያደርጉ እድል መፍቀዳቸውም ተዘግቧል።

ነፃነት እና ስርዓት አልበኝነት መረን የወጣ ሕግ እና ስርዓት የሌለው የመንጋ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የለበትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍቅር እንደመር ስንል በየከተማው ሽፍታ እናብዛ ማለት አይደለም በማለት ባለፉት ሳምንታት አገሪቷ ውስጥ የነበረውን ቀውስ የሚመለከት ሚመስል ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከኢትዮጵያ ስታፍ መኮንኖች በተጨማሪ 10 የሚሆኑ የጎረቤት አገራት ስታፍ መኮንኖችም ጨምሮ ማስመረቁንም ለማወቅ ተችሏል።