አርቲስቶች ለሜሪጆይ የህፃናትና አረጋውያን መርጃ ማህበር የሚውል ገንዘብ አሰባሰቡ

አባይ ሚዲያ ዜና

በኢትዮጵያ በግብረሰናይ ተግባር ለበርካታ አመታት ጠንካራ ስራ እያከናወነ ለሚገኘው ሜሪጆይ የህፃናትና አረጋውያን መርጃ ማህበር አርቲስቶች በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ያሰባሰቡትን የገንዘብ እርዳታ አበረከቱ።

በመንግስት እና በግል ድርጅቶች በመዘዋወር ከ 425 ሺህ ብር በላይ ለሜሪጆይ የህፃናትና አረጋውያን መርጃ ማህበር እርዳታ የሚውል ገንዘብ አርቲስቶቹ ማሰባሰብ ችለዋል።

በሃዋሳ በመገኘት ያሰባሰቡትን የገንዘብ እርዳታ ለሜሪጆይ መስራችና ስራ አስኪያጅ ለሆኑት ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ያስረከቡት አርቲስቶች ወገንን የመርዳት ጥሪን ለመላው ኢትዮጵያውያን አስተላልፈዋል።

ሜሪጆይን ከ 25 አመታት በፊት በመመስረት ከ 1 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያን ወገኖቻችን ተስፋ እንዲሆን ድንቅ ተግባርን እያከናወኑ ያሉት ሲሰተር ዘቢደር ዘውዴም አርቲስቶቹ ለበርካታ አመታት ከሜሪጆይ ጎን በመቆም እያደረጉ ያሉትን ወገናዊ እና አገራዊ ሃላፊነትን በማድነቅ ምስጋናቸውን አስተልፈዋል።

“ኢትዮጵይውያን ለኢትዮጵያውያን” በሚል መርህ ህብረተስቡ ሜሪጆይን በመደገፍ ወገኖቻችንን እራሳችን እንድንረዳ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንዳይቋረጥ ላደርጉ አርቲስቶች እና የሚዲያ ተቋማትም ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለበጎ አድራጎት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአቅሙን ያህል ለመርዳት ቢረባረብ በወገኖቻችን የሚደርሰውን ችግር መቀነስ እንደሚቻል የጠቆሙት አርቲስቶቹ እንዲህ አይነቶች የበጎ ተግባራትን የሚሰሩ ማእከሎችን እንዲደግፉ ለህዝቡ የእርዳታ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በጀርመን ሽቱትጋርት ከተማ በተዘጋጀው የኢትዮጱያውያን የባህል እና ስፖርት ፌስቲቫል ላይ የሜሪጆይ የክብር አምባሳደር በመሆን አርቲስት መቅደስ ጸጋዬ እና አርቲስት አብራር አብዶ በመገኘት ለሜሪጆይ ድጋፍ ሲያሰባስቡ እንደነበረ ይታወሳል።

“የፈራ ይመለስ” በሚል ርእስ መጽሃፉን ያሳተመው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በጀርመን በተካሄደው የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌስቲቫል ላይ መጽሃፉን ለታዳሚዎች በሽያጭ በማቅረብ ገቢውን  ለሜሪጆይ እርዳታ በማዋል ከጋዜጠኝነቱ በተጨማሪ ለበጎ አድራጎት የበኩሉን አስተዋጾ ለማበርከት ችሏል።   

በቅርቡ ከተለያዩ ከተሞች በግዳጅ እንዲፈናቀሉ የተደረጉ ኢትዮጵያውያንንም ለመርዳት ፍላጎት እንዳላቸው አርቲስቶቹ በተጨማሪ ገልጸዋል።

ተስፋቸው ለመነመነ ኢትዮጵያኖች እርዳታ በመለገስ ህይወታቸው እንዲቃና በግብረሰናይ ተግባር የሚንቀሳቀሰው ሜሪጆይ የህፃናትና አረጋውያን መርጃ ማህበር በ 25 የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ወገኖቻችንን እየረዳ ይገኛል።

ሜሪጆይ የህፃናትና አረጋውያን መርጃ ማህበር በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ አቅመ ደካማ አረጋውያንን እና እናቶችን በመጦር እንዲሁም በማሳከም ኣገራዊ ኋላፊነትን እየተወጣ ይገኛል።

ሜሪጆይ አሳዳጊ የሌላቸውን ህጻናት ከመንከባከብ አልፎ የወደፊት ህይወታቸውን ብሩህ ለማድረግ የትምህርት ወጪያቸውን በመሸፈን የትምህርት ገብታ እንዳይቀርባቸው የሚታገል አኩሪ ድርጅት ነው።

የሜሪጆይ የህፃናትና አረጋውያን መርጃ ማህበርን ለመርዳት ፍላጎት ካለዎት አሊያም ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ካስፈለጎ የሜሪ ጆይ ፌስ ቡክ ገጽን  ወይም ዌብ ሳይትን  ይጎብኙ።