በኦነግ ደጋፊዎች እና በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ያለመግባባት ተከስቶ እንደነበረ ተዘገበ

አባይ ሚዲያ ዜና

በአዲስ አበባ በተወሰኑ ቦታዎች በኦነግ ደጋፊዎች እና በህዝቡ መካከል ግጭቶች ተከስተው እንደነበረ የሚወጡ መረጃዎች አመለከቱ።

የትጥቅ ትግሉን በመተው በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካውን ለመታገል ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ በመስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም የሚገባውን በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ድርጅትን ለመቀበል ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ያደረጉት እንቅስቃሴዎች ከነዋሪዎች ጋራ ግጭት ሊፈጥር እንደቻለ ተሰምቷል።

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የተሰቀሉ ሰንደቅ አላማዎችን በመንቀል የኦነግ ድርጅት መለያ አርማን በቦታው ለመትከል የተወሰኑ ግለሰቦች ያደርጉትን ተግባር ቁጣን መቀስቀሱ ከማህበራዊ ሚዲያዎች የሚወጡ መርጃዎች ያሳያሉ።

ከአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ ከተሞች ህዝብን በሚጭን ተሽከርካሪዎች በብዛት ከገቡት የኦነግ ደጋፊዎች እና ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት መኪኖች መስታወታቸው ተጎድቶ ቆመው የሚያሳዩ ምስሎችም በማህበራዊ ሚዲያዎች ታይተዋል።  

ግጭቱ በመዳኒአለም ፣ በጳውሎስ ሆስፒታል እንዲሁም በአዲሱ ሚካኤል በተባሉ አከባቢዎች ተቀስቅሶ እንደነበረ ሲጠቀስ በቦታዎቹ የፖሊስ ሃይል በመድረስ ግጭቱን ሊቆጣጠረው እንደቻለም ለመረዳት ተችሏል።

በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ድርጅት በጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አስተዳደር የቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀብል በመስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሲገባ በመስቀል አደባባይ የአቀባበል ፕሮግራም እንደተዘጋጀለት ተዝግቧል።

የቀድሞው የኦነግ መሪ የነበሩት እና በቅርቡ የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባርን በመመስርት እየመሩ የሚገኙት አቶ ሌንጮ ለታ ከወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ለሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴዎች ለማድርግ መወሰናቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራውም የኦነግ ድርጅት በተመሳሳይ ሁኔታ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የሰላም ትግል ለማካሄድ በመስማማት ወደ አገር መግባቱ ይታወቃል።

የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎች የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድን የሰላም ጥሪ በመቀብል ኢትዮጵያን ሰላማዊ እና  ዲሞክራሲያዊ አገር ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን ለማበርከት ወደ አገር መግባታችው ይታወሳል። 

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ህዝቡ እጅግ አንገብጋቢ  በሆነው በሀገር ህልውና ጉዳይ ላይ እንዲያተኩር መልክታቸውን  አስተላልፈዋል። በህዝቡ መካከል ሆን ብለው ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን  ህዝቡ ስራቸውን እንዲያከሽፍ አቶ ታዬ ደንደአ በመልክታቸው አስፍረዋል።