ጠ/ሚ ዶክተር አብይ በአዲስ አበባ የተከሰተውን ግጭት በጽኑ ኮነኑ

አባይ ሚዲያ ዜና

በአዲስ አበባ በኦነግ ደጋፊዎች እና በነዋሪዎች መካከል የተቀሰቀሰውን አላስፈላጊ ግጭትን በመኮነን ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ አህመድ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመስከረም 5 ቀን 2011 አም በዳውድ ኢብሳ የሚመራውን የኦነግ ድርጅትን በመስቀል አደባባይ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ በህዝብ መጫኛ ተሽከርካሪዎች የገቡት ደጋፊዎች እና የከተማው ነዋሪዎች በፈጠሩት አለመግባባት የጸጥታ መደፍረስ መታየቱ ተዘግቧል።

በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ድርጅት በጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር የቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካዊ ፉክክር ለማድረግ ወደ አገር እንደሚገባ በታወቀበት በዚህ ወቅት በደጋፊዎች እና በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል የተከሰተው ግጭት አላስፈላጊ እንደነበረ ተነግሯል።

ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ሃሳቡን ለመግለጽ መፈክሮችን አሊያም ጽሁፎችን እንደሚጠቀም የገለጹት ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ ከዚህ በተጨማሪም አርማንም እንደ ድርጅቱ መለያ አድርጎ መጠቀም እንደሚችል አብራርተዋል። አንድ የፖለቲካ ድርጅት መለያ አርማውን ከመጠቀም አንስቶ የቆመለትን ሃሳብ ሳይሸማቀቅ በነጻ ለህዝቡ ማስተላለፍ የሚችልበትን ነጻነት እንደተሰጠው ዶክተር አብይ ተናግረዋል።

ባንዲራን በተመለከተ ግን ህዝቡ መክሮ መርጦ ባንዲራው ይቀየር የሚል ከሆነ የማይቀየርበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካን እንደምሳሌ በማድረግ ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ ለማብራራት ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ጉልበት ስላለኝ ባንዲራን በጉልበት አስቀይራለው ብሎ ሙከራ ማድረግ አዋጪ አለመሆኑ ጠቅላይ ሚንስትሩ አስረግጠው ተናግረዋል። ባንዲራን በጉልበት ማስቀየር የሚፈልግ ካለ እሱ ጉልበት እንዳለው ሌላውም ጉልበት ስላለው አያዋጣም ብለዋል ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ ።

በመገዳደል የሚደረግ መሸናነፍን ለማስቀረት በማሰብ አስተዳደራቸው እጁን በመዘርጋት በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩትን ሁሉንም የፖለቲካ ኋይሎች ወደ አገር መጥራቱን ጠቅላይ ሚንስትሩ በማስታወስ፤ በጥይት የተነጋገርንበት ወቅቶችን ወደ ኋላ በመተው በውይይት እና በሰከነ መልኩ ለአገራዊ አንድነት መትጋት እንደሚያስፈልግ እንደ በሬ ቅርጫ ለ 32 ክልሎች ተከፋፍላ መከራ የምታየው ደቡብ ሱዳንን እንደ ማስረጃ በመጥቀስ ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ በአንድነት ዙሪያ ቆምጠጥ ያለ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተያያዘ ዜናም የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በአዲስ አበባ የተከሰተውን ግጭት በመኮነን መግለጫ አውጥቷል። ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ ማንም ግለሰብ የድርጅቱን መለያ ማንገብ ሊከለከል እንደማይገባው አሳውቋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በቀን ሁለት ጊዜ መብላት ያቃታቸው በርካታ ወገኖች እንዳሉ እንዲሁም እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እራሱን ለማስተዳደር ስራ የሌለው መሆኑን ከዚህም በተጨማሪ ጧሪ ቀባሪ ያጡ መኖሪያቸው በላያቸው ላይ ሊፈርስ የተቃረቡ አያሌ አረጋውያን ባሉቧት ኢትዮጵያ መገዳደሉን ትተን መረባረብ ያለብን ይህን የልመና እና የውርደት ጊዜ ተባብረን በምናሳልፈበት ጉዳይ ላይ እንዲሆን ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።