ኦነግ የታገለው ለእኩልነት እንጂ ባንዲራ ለመቀያየር እንዳልሆነ የስራ አስፈጻሚው ገለጹ

አባይ ሚዲያ ዜና

የኦነግ የስራ አስፈጻሚ አባላት በአዲስ አበባ በተከሰተው ግጭት ዙሪያ ከሚዲያ ጋራ ባደረጉት ቆይታ መቻቻል ከሌለ የዲሞክራሲ ግንባታው አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አስገነዘቡ።

ከኦነግ የስራ አስፈጻሚ አባላት በተጨማሪ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፊሰር ብርሃኑ ነጋም  አንደኛው ወገን የሌላኛውን ወገን መብት ማክበር እንደሚገባው ተናግረዋል።

የኦነግ የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ አሚን ጂንዲ የታገልነው በኢትዮጵያ ውስጥ እኩልነት እና  ዲሞክራሲ የለም ብለን እንጂ ባንዲራ ለመቀያየር እንዳልሆነ ገልጸዋል።

አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን አውርደው የኦነግን አርማ የሚሰቅሉ ወይም የኦነግን የሚያወርዱ ግለሰቦች እሳቸው በከፍተኛ አመራርነት ያለቡት የኦነግ ድርጅት ያስተማራቸው እንዳልሆኑ እና የኦነግም አላማ እንዳልሆነ አቶ አሚን ጂንዲ አክለው ለሚዲያ ተናግረዋል።

ያለምንም ግጭት የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ወሰነው እንደገቡ በማስታውስ ክቡር በሆነው የሰው ህይወትም ሆነ በንብረት ላይ አንዳች ጉዳት መድረስ የለበትም በማለት የገለጹት ሌላኛው የኦነግ ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ኢብሳ ነገዎ  ናቸው። ይህን ጥሪ በመቃወም ብጥብጥ በሚያነሱ አሊያም በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት በሚያደርሱት ላይ የመንግስት የጸጥታ አካል እርምጃ መውሰድ እንደሚገባውም  አቶ ኢብሳ ነገዎ   አሳስበዋል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ለፍትህ እና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከሚዲያ ጋር ባደርጉት ቆይታ የኔ ብቻ የሚል አመለካከት ላይ የሚመሰረት ዲሞክራሲ እንደሌለ አስረድተዋል። ልዩነትን አቻችሎ የአንዱን መብት በማክበር አንዱ የፈለገውን በሰላማዊ መንገድ እንዲያከናውን መፍቀድ ለዲሞክራሲ መጎልበት ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነም ፕሮፌስር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል።

መስከረም 5 ቀን 2011 አም በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ አመራር ቡድኖች  አዲስ አበባ ሲገቡ የአቀባበል ፕሮግራም ተዘጋጅቶላቸዋል። ይህ የአቀባበል ፕሮግራም በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ መንግስትን ጨምሮ የኦነግ አመራሮች እንዲሁም የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በተቀስቀስው ግጭት ዙሪያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በመገዳደል እና ንብረትን በማውደም አሸናፊ መሆን እንደማይቻል በመጥቀስ በትናንሽ አጀንዳዎች ተከፋፍለን ከመበታተን በአንድነት ተደምረን ኢትዮጵያን እንቀይራት የሚል ጥሪ ለመላ ኢትዮጵያውያን አቅርበዋል።