የአዲስ ዓመት መልእክት ይድረስ ለጥምር ጎሳ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ( በአገሬ አዲስ )

መስከረም 1 ቀን 2011 ዓም (11-09-2018)

ማንኛውም የሰው ልጅ የሚወለድበትን ቤተሰብ፣ቦታና ጊዜ መርጦ አልተፈጠረም። በሁኔታ አጋጣሚ በሁለት ጾታዎች ፍቅር፣መፈቃቀድ ወይም የኑሮ ግዴታ በሚፈጠረው ግንኙነት ባላሰበበትና ባልወሰነው ቦታና ጊዜ ወይም ከእገሌ ጎሳ ልወለድ  ብሎ ባልመረጠው ሁኔታ ይወለዳል።ያ የተወለደ ልጅ ከሁለት አብራክ፣ደምና ስጋ  የተፈጠረ በመሆኑ በውስጡ የሁለቱም ጾታዎች፣የእናትና የአባቱ እኩል ድርሻ የሆነ ማንነት አለው።የተወለደው ህጻን የተለያዩ ቋንቋዎችን ከሚናገሩ ጎሳዎች ከሆነም የነዚያ ጎሳዎች ጥምር ማንነት ይኖረዋል። ከቶም ቢሆን የአንዱን ጥሎ የሌላውን አንጠልጥሎ፣አንዱን ወዶ ሌላውን ጠልቶ ሊኖር አይቻለውም።ለሁለቱም እኩል ፍቅርና ክብር አለው።በዚህ የጋራ ማንነት የተወለደ ለጎሳ ማንነቱ ሳይሆን በሰው ልጅነቱ ለሁሉም የሰው ልጅ የማያዳላ ፍቅር ይዞ ያድጋል።የአንድነትም ተምሳሌት ይሆናል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰማንያ የሚበልጡ የጎሳ ማህበረሰቦች ይኖራሉ፤እነዚህ ማህበረሰቦች በሚኖሩበት አገር የሚቀራረቡበት መንገድ የኤኮኖሚ፣የባህል፣የቋንቋና የታሪክ ዘርፎች ብቻ ሳይሆኑ በመውለድና በመዋለድ የቤተሰብ ሐረግ በመፍጠርም ጭምር ይሆናል፤ሆኗልም።ይህንን የቤተሰብ ሐረግ ለመፍጠር ያስቻላቸው ትልቁ ምክንያት ኢትዮጵያ የምትባለዋን አገር በጋራ በመመስረታቸውና በአገር ባለቤትነት ኩራት የአንዱ ጎሳ ተወላጅ እንደልቡ በፈለገበት ቦታ ሄዶ ከሌላው ጎሳ ተወላጅ ጋር ተቀራርቦ ለመኖር በመቻሉ ነው። ያም መቀራረብ በጎረቤትነት ብቻ ሳይወሰን በቤተሰብነት ደረጃ ከፍ እንዲል እረድቶታል።ወልዶ ተዋልዶ አንዱ በሌላው ውስጥ የሚኖርበትን ልጅ የተባለ ሰንሰለት፣ በሥጋና ደም የተገነባ ህያው መታሰቢያ ለመፍጠር በቅቷል።

በዚህ አገራዊና  የኢትዮጵያዊነት የዜግነት ስሜት በፈጠረው ዕድል የተገናኙ የተለያዬ  ጎሳ ተወላጆች በመሰረቱት የትዳርና የፍቅር ጎጆ በብዙ ሚሊዬን ብሎም ከአንዳንዶቹ የክልል ነዋሪ ሕዝብ የበለጠ ቁጥር ያላቸው የሁለት ጎሳ ስብጥር ፍሬዎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ተወልደዋል።ብዙዎቹም ላገራቸው አንድነትና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተው አልፈዋል፤አሁንም በማበርከት ላይ ይገኛሉ።የሁለት ጥምር ጎሳ ልጆች በመሆናቸው የአንድ  ነጠላ ጎሰኝነት አጥሩን አፍርሰውታል።የአንዱ ጎሳ ወዳጅ የሌላው ጎሳ ጠላት ሳይሆኑ ሁሉንም ጎሳ በሚያስተሳስረው ፣ለመፈጠራቸው ምክንያት የሆነውን ኢትዮጵያዊነትን ለመጠበቅ ግንባር ቀደም ሰልፈኞች መሆናቸውን በታሪክ አስመስክረዋል።እነዚህ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ውጤት፣የጥምር ጎሳ ፍሬ የሆኑ ዜጎች ባላቸው ብዙ ቁጥር ላይ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑት የነጠላ ጎሳ ተወላጆች ሲጨመሩበት የአገሪቱን ሕዝብ ከፍተኛ ቁጥር እንደሚሸፍኑ አያጠራጥርም።ይህንን ወሳኝ ቁጥር ግን እንደሌለ ተቆጥሮ ድምጸ አልባ ሆኖ የጥቂት አክራሪዎች ተጎታች  ካሮሳ  እንዲሆን ለማድረግ በሽብርና በተሳሳተ ታሪክ ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል፤አሁንም እየተሞከረ ነው።ለድፍረቱ ዕድል የሰጠው ኢሕአዴግ በተባለ መሰሪ የጎሰኞች ስብስብ የሰፈነው የጎሳ ስርዓት ከመሆኑም በላይ ያንን የሚቃወመው ሃይል  አለመደራጀቱ ነው። አደረጃጀቱ ኢትዮጵያዊነትን በሚያጎላና ወላጆቹን ለመገናኘትና ለእሱም መወለድ ምክንያት በሆነው ቀድሞ በነበረው  የክፍላተ ሃገር አወቃቀርን በሚያራምድ የፖለቲካ ድርጅት እንቅስቃሴ ስር ቢሆን የተሻለ ከመሆኑም በላይ አሁን በየአቅጣጫው እንደ መብትና ፋሽን የሚዥጎደጎደውን ጎሰኝነትንም ያጠፋል። ስጋት ላይ ያለውንም አገር የመበታተን አደጋ ያስወግዳል። ምስጋና ይግባቸውና ይህንን በተረዱት የየክፍላተ  ሃገሩ ተወላጆች ኢትዮጵያውያን ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት  የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት ተመስርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

ከጥምር ጎሳ የተወለዱት ኢትዮጵያውያን የእናታቸውን ወይም የአባታቸውን ነጠላ የጎሳ ማንነት እንዲሸከሙና የሌላውን አካላቸውን ክፍል የሆነውን ጎሳ እንዲረሱ ብሎም እንዲጠሉ የሚደረገው ቅስቀሳ ከቀን ወደ ቀን እያደገ በመምጣት ላይ ነው። ከመጥላትም አልፎ ከማጥቃት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ አዝማሚያ በፍጥነት ካልተቀጨና በእውነተኛ ከጎሳ አደረጃጀት ነጻ በሆነ አገራዊ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ካልተተካ በቤተሰብነት ክፉና ደጉን ተካፍለው የኖሩትን ባልና ሚስቶች፣ ልጆችና የልጅ ልጆችን የሚያጠፋ ብቻ ሳይሆን በፍቅርና በደስታ በሰላም የኖሩባትን ፣ለግንኙነታቸው ምክንያት የሆነችውን አገራቸውን አትዮጵያንና በዓለም መታወቂ የሆናቸውን ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያጠፋ ይሆናል።

ከሁለት ጎሳ ቤተሰብ የተወለዳችሁ ኢትዮጵያዊያን  ሆይ!

ከቶ ከወላጆቻችሁ መካከል የትኛውን ወዳችሁ የትኛውን ልትጠሉ ትችላላችሁ? የአባቶቻችሁን ጎሳ መርጣችሁ ዘጠኝ ወር ተሸክማ ወልዳ፣ጡት አጥብታና ተንከባክባ ያሳደገችን እናት ጎሳ  መጥላት ማለት የእራሳችሁን ግማሽ አካል መጥላት  ብሎም የጠቡበትን ጡት ነካሽነትና  ከሃዲነት  ይሆናል።የእናትንስ ጎሳ መርጦ የአባትን ጎሳ መጥላት ደፋ ቀና ብሎ ያሳደገን አባት  እጅ ቆርጦ መጣል ብሎም የራስን ግማሽ አካል መካድና መጥላት  አይሆንምን?ብዙሃኑ የዚህ አይነት ጎደሎ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ የምትቃወሙ እንጂ የምትደግፉ እንዳልሆናችሁ ይታወቃል። ለእናንተ ለጥምር ጎሳ ተወላጆች መፈጠር የእናትና ያባቶቻችሁ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑ አይካድም። ለዚያ ደግሞ የመገናኛው ምክንያት የሁሉም ጎሳ ተወላጅ ተከባብሮ በሰላም የኖረባት ኢትዮጵያ መኖሯ ነው።በጎሳ ተዋረድ የሚደረግ የጠባብ ጎሰኝነትና ጸረ ኢትዮጵያ ቅስቀሳ የኢትዮጵያዊነት ፍሬ የሆናችሁትንም መብት ለመግፈፍና ለማጥፋት የታቀደ ሴራ መሆኑን አትዘነጉትም። ስለሆነም የጎሰኞችን ተንኮል ማክሸፍና ኢትዮጵያን ማዳን እራሳችሁን፣ወላጆቻችሁንና በቤተሰብ ሐረግ የተሳሰረውን ዘመድ አዝማድ ማዳን ማለት ነው።ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትንም ማዳን ማለት እናንተም እንደ እናትና አባቶቻችሁ፣እንደ አያትና ቅድመ አያቶቻችሁ የጎሳ ማንነት ሳያግዳችሁ ከፈለጋችሁት ጋር አብሮ የመኖርና ወልዶ የመሳም ፣በፈለጋችሁበት ቦታ በመኖር የመሥራትና ንብረት የማፍራት መብታችሁን ማስከበር  ማለት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጠላት መሳሪያ የሆኑ ጥቂት መሰሪዎች በሚያራምዱት ጸረ አንድነት የጥላቻ ዘመቻ ጎሳ ለይቶ መፋጠጡ፣ማፈናቀሉ፣መግደሉና ማሳደዱ፣መሬት መንጠቁ እያደገ በመምጣት ላይ ነው፣እርምጃው አገራችንንና ሁላችንንም ከመበታተን ስጋት ላይ ጥሏል። በጊዜው ካልተገታ ሁሉም ተያይዞ መቀመቅ መግባቱ አይቀሬ ነው። ያ ከመሆኑ በፊት የአንድነት ተምሳሌት የሆናችሁት የጥንድ ጎሳ ተወላጆች ድምጻችሁን ማሰማት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እርምጃ ልትውስዱ ይገባችኋል።የጎሰኝነትን አስተሳሰብና የተገነባውን የክልል ግምብ አፈራርሶ አገራዊ አንድነትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባት ከሚታገሉት ጋር በመሆን  ብሔራዊ ግዳጃችሁን ለመወጣት ተነሱ። በሰላም ተከብራችሁ ለመኖር የሚያስችላችሁን ኢትዮጵያዊነትን ለማዳን በአንድነት ተሰለፉ።ኢትዮጵያን ማዳን ማለት እራስን ማዳን ነውና!

 የጥቅም ተገዥ የሆኑ አነስተኛ የጥንድ ጎሳ ተወላጆች ወይም ከሌላው ጎሳ ጋር ተጋብተው የኖሩና የሚኖሩ ብሎም የወለዱ በአንዱ የጎሳ ሰልፍ ውስጥ ገብተው የአባታቸውን ወይም የእናታቸውን፣የኑሮ ጓደኛና የልጆቻቸውን ግማሽ አካል የሆነውን ሌላውን ጎሳ ሲያጠቁና ሲያስጠቁ እንደኖሩና አሁንም በማስጠቃትና በማጥቃት ላይ እንዳሉ የሚታወቅ ነው።ይህ ኢሰብአዊና ከፋፋይ ስልት የቅኝ ገዥዎች ሲሆን ያንን ተረክቦ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መዳፍ ላይ የወደቀው ኢሕአዴግ የተባለው ቡድን ያሰፈነው ስርዓት ለሃያ ሰባት ዓመት ተጠቅሞበታል።በአሁኑ ጊዜ ሕዝብ አንቅሮ ስለተፋው በመንገዳገድ ላይ ይገኛል።ምንም እንኳን ስልትና መሪዎቹን ቢለዋውጥም የጊዜ ጉዳይ ነው መውደቁ አይቀርም፣ ይወድቃል።ታዲያ የዚያን ጊዜ እነዚህ አድር ባዮች ምን ይውጣቸው ይሆን?በተጨማሪም በተመሳሳይ የፍቅረ ጎሰኝነት አባዜ የተለከፉ የስልጣን ጅቦች በሚያማልል የውሸት ዲስኩር አሰፍስፈው ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው በግልጽ እዬታዬ መጥቷል። ቦታው በነዚህ አስመሳይ የጎሳ ስብስብ መሳሪያ በሆኑ ቡድኖች እንዳይወሰድ ነቅቶ መጠበቅና መከላከል የሁሉም ድርሻ ነው።ከተሳካላቸው ከድጡ ወደማጡ የመግባት ያህል ነው።

የፖለቲካ ሥራ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገርና ሕዝብ የተጋለጡበትን አደጋ ለማስወገድ፣ የወደፊቱንም ትውልድ  ዕድልና ኑሮ የተሻለ እንዲሆን የሚቀይሱበት ሁለንተናዊ ሳይንሳዊ ችሎታ እንጂ በጭፍን ጥላቻና ፍላጎት ላይ የሚመሰረት የመንጋ ወይም የጭፍራ ድግስና ዳንኪራ የሚመቱበት የሆያሆዬ መድረክ  አይደለም።

የጎሳ ማንነት የፖለቲካ መዘውር ከሆነ አገር ያፈርሳል፣ሕዝብ ያጫርሳል። ይህንን ከሌሎች አገሮች በተለይም ከጎረቤቶቻችን ከሩዋንዳና ከሶማሊያ በደረሰው ልንገነዘበው እንችላለን። በአገራችንም የሚከናወኑት ጎሳ ተኮር ጥፋት፣ጥቃት፣ማፈናቀልና የጥላቻ እርምጃዎች የዚያ መንደርደሪያዎች ናቸው። ይህ ጎሳ ተኮር አሰላለፍ  የአስራ ስድስተኛው የዘመነ መሳፍንት ስርዓት ነጸብራቅ እኩይና ዃላ ቀር ድርጊት ነው። በሰለጠነው የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ተቀባይነትና ቦታ የለውም። ጎሰኝነት ከከረረ ፋሽዝምን ይወልዳል። የጎሰኝነት ትርፉ ደቆና ደህይቶ አገረቢስ ሆኖ በመሰደድ ፤መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆን በተረፈ በእራስ ኪሳራ ለባዕዳንና  ለመሳሪያ ቸብቻቢ ማፊያ  የንግድ ድርጅት የጥቅም በርና ዕድል መፍጠር ነው።

በአዲስ ዓመት አሮጌውን የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ አውልቀን ዘመናዊና አገራዊ የፖለቲካ አመለካከት እንላበስ!

ኢትዮጵያንና እራሳችንን ከጎሰኞች ጥቃትና ጥፋት እንከላከል!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ የተባበረ ትግል በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!!