አባይ ሚዲያ ዜና

የኦነግ አመራሮችን ለመቀበል በሚል ሰበብ ከአዲስ አበባ አቅራቢያ በህዝብ አመላላሽ አውቶቢሶች ተጭነው የመጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ግለሰቦች በፒያሳ ግጭት ለምፍጠር ያደርጉት ሙከራ እንደከሸፈ ተገለጸ።

በአውቶቢሶች ተጭነው በመምጣት ፒያሳ እንዲበተኑ የተደረጉት ግለሰቦች ሰላማዊ ያልሆነ እንቅስቃሴዎች ሊያደርጉ ሲጥሩ በፖሊስ መበተናቸው ተዘግቧል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት በቆመው የንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ሚንሊክ ሃውልት ላይ ያልተገባ እንቅስቃሴ ለማድረግ ከአውቶቢሶቹ ዱላዎችን ይዘው የወረዱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች በፒያሳ እና በአከባቢው በሚገኙ ነዋሪዎች ከፍተኛ መከላከል እንዳጋጠማቸውም ተነግሯል።

ፖሊስ በቦታው በመገኘት ሊከሰት የነበረውን ወንጀል እና ግጭት ለመቆጣጠር እንደቻለ ሲገለጽ፤ የንግድ ቤቶች እና ትራንስፖርቶች በፒያሳ አከባቢ ተስተጓጉለው እንደነበረ የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ከ 500 በላይ የሆኑ ግለሰቦች በአውቶብሶች ተጭነው በመምጣት በዳግማዊ አጼ ሚንሊክ ሃውልት ላይ ጉዳት ለማድረስ በፒያሳ መንገዶች ላይ ሲነጉዱ መታየታቸው ተዘግቧል። የነዚህን ግለሰቦች እንቅስቃሴ ለመግታት የፒያሳ እና የአከባቢው ነዋሪዎች የመከላከል እርምጃዎችን እንደወሰዱ እና ፖሊስም ጣልቃ በመግባት ግጭቱን ለማብረድ እንደቻለ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።

በአውቶብስ ተጭነው ወደ ፒያሳ እንዲያቀኑ የተደረጉ ከአዲስ አበባ አቅራቢያ ከሚገኙ የኦርሚያ አከባቢዎች የመጡ ግለሰቦች ይህንን ድርጊት እንዲፈጽሙ ማን እንደላካቸው ፖሊስ አልገለጸም። የንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ሚንሊክ ሃውልት በበርካታ የጽጥታ ሃይሎች ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑንም ተጠቁሟል። 

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ በዜናው ሽፋን የፌዴራል መንግስት በወሰደው እርምጃ ሁለት ግለሰቦች ህይወታቸው እንዳለፈ የቡራዮ ጤና ጣቢያን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል። በጉለሌ አከባቢ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በመያዝ የተደራጁ ግለሰቦች በህንጻዎች ላይ ጉድት አድርሰዋል በማለት ይህ የዜና ተቋም በተጨማሪ አስደምጧል። ይሁን እንጂ በዚሁ አከባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት ህይወቱ ስላለፈው እና ስለተቀበረው የአዲስ አበባ ወጣት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ዘገባ አላቀረበም።

አቶ በቀለ ገርባ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ቴሌቭዝን ቀርበው የኦሮሞ ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መንግስት በአስለቃሽ ጭስ ለማባረር ሞክሯል እንዲሁም የአዲስ አበባ ህዝብም በንብረቶች ላይ ጥቃት አድርሷል በማለት ክሳቸውን ሲያሰሙ ተደምጠዋል። ባለፉት ቀናት ወደ አገር ለገቡት የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች የአቀባበል ስነስርአት እንዲሳካ የመከላከያ ሰራዊቱ እና ፖሊስ እገዛ ሲያደርጉ እንደነበረ አቶ በቀለ ገርባ ከሚዲያው ጋር ባደርጉት ቆይታ ተናግረዋል። ነገ ለሚገቡት የኦነግ አመራሮች የሚደረገው የአቀባበል ፕሮግራምን የመከላከያ ሰራዊቱ እና ፖሊሱ ለማበላሸት እየጣሩ እንደሆነ የ ኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ክሳቸውን በኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ አስደምጠዋል። የአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ መምህር የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ በፒያሳ ስለተደረገው ግጭት ማብራሪያ አልሰጡም።

አክቲቪስት ጃዎር መሀመድ በበኩሉ የኦነግ አመራሮችን ለመቀበል የሚደረገው ፕሮግራም በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም መረባረብ አለበት በማለት መልክቱን አስተላልፏል። የኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ ስራ አስኪያጅ አክቲቪስት ጃዋር መሀመድ ወደ አዲስ አበባ በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የገቡት ግለሰቦች ክፍተኛ ዲሲፕሊንን የተጎናጸፉ  እንደሆነ በመጥቀስ በግለሰቦቹ ላይ ጥቃት ደርሶባቸዋል በማለት ቅሬታውን አሰምቷል።

የአቀባበል ፕሮግራሙ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ መልክታቸውን በማስተላለፍ በፕሮግራሙ ላይ ሰላምን ለማወክ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ከመንግስት ትእዛዝ እንደተቀበሉ ገልጸዋል።

አርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነ በበኩሉ ልዩነቶችን በማቻቻል የተገኘው እድል ባክኖ እንዳይቀር መላ ኢትዮጵያውያንን በማሳሰብ የአቀባበል ፕሮግራሙ በሰላም እንዲጠናቀቅ መልክቱን አስተላልፏል።