አባይ ሚዲያ ዜና 
በሰላም ሃገሬ 

በቅዳሜ መስከረም 5, 2011 ዓ.ም ጥዋት የአርበኞች ግንቦት 7 አመራር እና አባላት በባህር ዳር የመጀመሪያውን ስብሰባ በባህር ዳር  ስታዲዮም አድርጓል።

የንቅናቄው አመራሮች በባህርዳር አማራ ክልል ምክር ቤት አዳራሽ ውስጥ ሁለተኛውን ስብሰባ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ማድረጋቸው ተዘግቧል።

በሁለቱም ስብሰባዎች ላይ የንቅናቄው ሊቀመንበርና ፀሀፊን ጨምሮ ከኤርትራ እና ከውጭ ሀገራት የገቡ አመራሮች እና የድርጅቱ አባላት ተካፋይ እንደነበሩ ታውቋል።

በተጨማሪም በዛሬው እለት በባህር ዳር አዳራሽ ውስጥ በተደረገው ውይይት ላይ ለታደሙ የባህር ዳር እና አካባቢው ነዋሪዎች ድርጅቱ ወደፊት ወደ ፓርቲነት ሲቀየር ለመከተል የፈለጋቸውን መርሆዎች በብሮሸር መልክ ተሰራጭተዋል።

የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች ከባህር ዳር እና ከአከባቢዎች ካሉት ኢትዮጵያውያን ጋር ያደረጉትን ውይይት በማጠናቀቅ ቀጣይ መርሃ ግብራቸውን ወደ ጎንደር ለማድረግ ጉዞዋቸውን መጀመራቸው ተገልጿል።

በመስከረም 6 ቀን 2011 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች  ከኢትዮጵያኖች ጋር በመገናኘት ተመሳሳይ የውይይት ስብሰባዎችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።   

የንቅናቄው መሪዎች አዲሱን የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የጋንቤላ እንዲሁም የአፋር ህዝብ ድርጅት ተወካዮችን ማነጋገራቸው ተነግሯል። ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች የድርጅቶች አመራሮች እና ተወካዮች ጋራ ውይይት ለማድረግ ንቅናቄው እቅድ እንደያዘ ተገልጿል።