አባይ ሚዲያ ዜና

በቡራዩ ለጆሮ ለመስማት በሚሰቀጥጥ መልኩ  ንጹኋን ዜጎች ላይ የግድያ እና የማፈናቀል ወንጀል መፈጸሙ ተገለጸ።

በቡራዩ በተቀሰቀሰው ግጭት የንጽኋን ኢትዮጵያኖች ህይወት አረመናዊ በሆነ ጭፍጨፋ ማለፉን የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በተከሰተው አስከፊ ድርጊት በንጹኋን ኢትዮጵያኖች ላይ ግድያን ጨምሮ አስገድዶ መድፈር እንዲሁም ዝርፊያም እንደተከናወነ የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳይሉ።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እንዲሁም  ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ይህን ፍጹም የጭካኔ ድርጊትን በመሸሽ ተፈናቅለው በአስኮ  ቃሌ ተብሎ በሚጠራ ትምህርት ቤት ተጠልለው ያሉትን ኢትዮጵያውያንን በቦታው በመገኘት ጎብኝተዋል። ይህንን ኢሰብአዊ ድርጊትን በመሸሽ ለተፈናቀሉ ንጽኋን ኢትዮጵያውያን የምግብ፣ የመጠጥ እና የቁሳቁስ  እርዳታ ለማድረግ ኮሜቴ መቋቋሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገልጿል።

የኦነግ አመራሮችን ለመቀበል በመስከረም 5, 2011 ዓ.ም የተደረገው ፕሮግራም በአዲስ አበባ በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁ ይታወሳል። ይሁን እንጂ በመስከረም 5, 2011 ዓ.ም በቡራዩ በንጽኋን ኢትዮጵያን ላይ የተከሰተው ልብን የሚሰብር ግፍና ጭፍጨፋ በተለያዩ ቦታዎች ቁጣን ቀስቅሷል።

ይህንን ኢሰባዊና አስከፊ ግድያ፣ ዝርፊያ እንዲሁም መፈናቀል ያስከሰቱ ወንጀለኞች ላይ መንግስት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት በከፍተኛ ደርጃ እየተጠየቀ ይገኛል።ከዚህም በተጨማሪ መንግስት የዜጎቹን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ አለበት በማለት ማህበረሰቡ የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አስተዳደርን አጥብቆ እየኮነነ መሆኑን ለአባይ ሚዲያ የሚደርሱ መረጃወች ይጠቁማሉ።

በቡራዮ በዜጎቻችን ላይ የደረሰውን ግፍ እና በደል በመቃወም በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ቴሌቭዝን ህንጻ ፊት ቁጣቸውን ሲገልጹ ያረፈዱ ኢትዮጵያውያን መንግስት ወንጀሉን በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጥያቄያቸውን አሰምተዋል።

በቡራዩ እና በአከባቢው በዚህ የጭካኔ ድርጊት ውድ ህይወታቸውን ባጡ ንጽኋን ኢትዮጵያውያን የተሰማንን መሪር ሃዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።