አባይ ሚዲያ ዜና

በቡራዩ እና በአዲስ አበባ በንጹኋን ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው አረመናዊ ግድያ ህይወታቸው ያለፈ ዜጎቻችን ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አለማየሁ እጅጉ እንደገለጹት 23 ንጽኋን ኢትዮጵያውያን በቡራዩ እና በተወሰኑ የአዲስ አበባ ቦታዎች በአሰቃቂ መልኩ እንደተገደሉ መረጃ እንደደረሳቸው ተናግረዋል። ይህ ቁጥር ግን ሊጨምር እንደሚችል ኮሚሽነሩ በተጨማሪ ገልጸዋል።

ቡራዩ እና አዲስ አበባ ላይ ጭካኔ የተሞላበትን ግድያ እና ዝርፊያ የፈጸሙ ግለሰቦች በህዝቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል አለማየሁ እጅጉ ጠቅሰዋል። ጭካኔ የተሞላበት ወንጀል የተፈጸሙባቸው ቦታዎች በአሁን ወቅት መረጋጋታቸውን እና ለህይወት የሚያሰጉ እንዳልሆኑ የኦሮሚያ ፓሊስ ኮሚሽነሩ አክለው ገልጸዋል።

ህይወታቸውን ለማትረፍ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎቻችን በአስኮ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተጠልለው ይገኛሉ። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በመስከረም 6 ቀን 2011 አም እነዚህን ተፈናቃዮች በመጎብኘት አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ ጊዜያዊ ኮሜቴ ተዋቅሮ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ለሚዲያ አስታውቀዋል።

በንጹኋን ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን አረመናዊ ድርጊት በመቃወም በርካታ ኢትዮጵያውያን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ቁጣቸውን ለማሰማት ወጥተዋል።

ክቡር የሆነውን የንጹህ ሰውን ህይወት በአሰቃቂ መንገድ የመግደል፣ ጭካኔ የተሞላበት የድብደባ እንዲሁም የዘረፋ ድርጊቶች በፍጽሙ የኢትዮጵያዊ ባህሪ እንዳልሆነ ነፍሳቸውን ለማዳን ተፈናቅለው አዲስ አበባ የገቡት እና በሰልፉ ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን በምሬት ሲገልጹ ተደምጠዋል።

በአርባምንጭም በንጽኋን ኢትዮጵያኖች ላይ የደረሰውን ግድያ እና ዝርፊያ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል። በፖሊስ እና ለተቃውሞ በወጡት ሰልፈኞች መካከልም ግጭት መከሰቱ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

በወገኖቻችን ላይ ለመስማትም ሆነ ለማየት በሚሰቀጥጥ መልኩ ለተፈጸመው ወንጀል የዶክተር አብይ አስተዳደር ቆራጥ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።

ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ በቡራዩ እና በአንዳድ የአዲስ አበባ ቦታዎች በንጹኋን ኢትዮጵያውያን ላይ በደረሰው ግድያ እና መፈናቀል የተሰማቸውን ሃዘን እንደገለጹ መዘገቡ ይታወሳል።

በንጽኋን ኢትዮጵያውያን ላይ በተፈጸመው ድርጊት ህይወታቸውን ባጡ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።