ድምር እማይገባው ፍቅርን የማያውቅ (በግርማ ቢረጋ)

ምንስ  ነው የመጣው  ከኦሮሞው መንደር ፣

ማን ይዞብን ገባ የማይሆን ለሃገር ።

በሌላም ላይ አይደል በራሱ በሃበሻ ፣

የጭካኔው ብዛት ያሳጣ መሸሻ ።

ብርሃን ላይታይ ጥቁር ጭላንጭል ፣

አስወግደው ጣለው የዘርን ጭንብል ።

ከኖረበት ምድር ህዝብን ማፈናቀል ፣

ወንድነት መስሎሃል ያፈቀረን መግደል ።

እኔስ  መስሎኝ ነበር ያወቁ የበቁ ፣

የፍቅርን ማሸነፍ ቀድመው የሰበኩ ።

አረ ምን ነካቸው ምን አመጡ ደግሞ ፣

እንደያዙት ሜንጫ ቃላቸው ተጣሞ ።

ጀግንነት መስሏቸው ገደሉት  ፍቅርን ፣

ወያኔ ጭን ገብተው ሆነው በቀቀን ።

ቁፋሮው ሲበዛ የዘር ግንድ መረጣ ፣

ወንድም በወንድም ላይ ሲሆነው ባላንጣ ።

ለፍቅር ተገዝቶ ተዘናግቶ ሳለ ፣

በዚያ  በችግር ቀን ጥሬን ላቀበለ ።

ይሆናል ወይ መልሱ  አጠና  ገጀራ ፣

ግዳዬን ጣልኩ በል ውጣና ፎክራ ።

ተለጣፊው በዛ እራሱን ያልሆነ

ተኝቶም በቁሙ እንዲሁ የባነነ ።

የተማረ መስሎኝ ሲጨበጨብለት ፣

ቅን አሳቢ መስሎኝ ሲውለበለብለት ፣

ነካስ እርጉም  ኖሯል ጉዳይ አስፈፃሚ ፣

የቀን ጅቦች ወዳጅ መቀመጫ ሳሚ ።

እህል በአፉ ወስዶ በአፉ የሚተፋ ፣

በከፈተው ቁጥር ከቶ የሚከረፋ ።

ዘጠኝ ግዜ ካጂ ልፍስፍስ ወስላታ  ፣

ከሩቅ ሃገር ሆኖ ከበሮ የሚያስመታ ።

በቃ ቁረጥ አንተ እሱ አይደለም ያንተ ፣

መደመር ካቃተው ቁረጥ ለካው አንተ ።

መቀነስን ተማር ሰው ሲሆን አተላ ፣

ይበቃሃል አንተም አትሁን ተላላ ።

ድምር ለማይገባው ፍቅርን ለማያውቅ ፣

ቆስቁስ ጎራዴህን ደምክን አሟሙቅ ።

ስቶክሆልም

ሴፕቴምበር 2018