ቡራዩና ጎፋ (በላይነህ አባተ)

ምረቱን ያምጣልሽ እማማ ኢትዮጵያ፣

በቀደም አማራ አሁን ደሞ ጎፋ፡፡

ድር ተማግ አስማምቶ በሸፈነ ገላ፣

እንደ ሳር ታጨደ ተነቀለ ጎፋ፡፡

እንዴት ቢረገሙ ምን ጭራቅ ቢሆኑ፣

የልጇን ጡት ቆርጠው ለናቲቱ አሳዩ?

ከምስራቅ ተነስቶ በእግሩ እያዘገመ፣

በደኖ ተጉዞ ቡራዩ ደረሰ፡፡

መወርወሪያ ገደል ሸለቆ ስላጡ፣

በገጀራ አንገትን መጎመድ መረጡ፡፡

ቫይረስ የለከፈው ለሃጭ ጣዩ ውሻ፣

የቤት ሰው ይነክሳል እንደ ባድ እንግዳ፡፡

መደመር መታደስ እየወሸከቱ፣

ስንቱን አስቀጥፈው ስንቱን አስነቀሉ፡፡

ኢያሱና ሙሴ ብለው የሾሟቸው፣

በደም ተነከሩ ዙፋን ተቀምጠው፡፡

ተደመርኩ እያለ ንጹሐን ታረደ፣

ወረተኛው መንጋ በደም ተበከለ፡፡

መለኮት በሰዶም ገሞራን ያመጣው፣

ሁሉም ተደምሮ ፃድቅ ሲጠፋ ነው፡፡

አራጊ ፈጣሪው እግዚአብሔር እንኳን፣

ሊደምር አይቃጣም ጽድቅና ኩነኔን፡፡

በየትኛው ትንቢት በየትኛው ታምር፣

ፍትህ ሳትዳምን ሰላሙ ያካፋል፡፡

ዳግም እንዳይወጣ የቡራዩው ዕጣ፣

ብሩክ ገነት እልፍኝ እርጉም ሲኦል ይግባ፡፡

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

መስከረም ሁለት ሺ አሥራ አንድ ዓ.ም.