ለ 27 ዓመታት የተረጨዉ የዘረኝነት ፖለቲካ መርዝ ሰሞኑን በቡራዩና አካባቢው በደረሰዉ የወገን እልቂት ዉጤቱ ምን  ያህል አስከፊ እንደሆነ ተመልክተናል። ቀደም ባሉት ጊዜያትም በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ተመሳሳይ አሰቃቂ ድርጊቶች በወገን ላይ ተፈጽመዋል። የዉጭ ጠላት ድንበራችን ጥሶ መጥቶ ቢፈጀን ኖሮ ፍጅቱ እምብዛም አያስደንቅምም፤አሳዛኝም አይሆንም ነበር። የሚጠበቅ ነዉና። እጅ በእጅ ሲቆረጥ ግን ከማሳዘንም አልፎ አንጀት ይቆርጣል። ባንድ ወቅት በእንደዚህ  ዓይነት ክስተት አግራሞት ያተረፈ አንድ አልቃሽ፤

የሞተዉ ወንድምሽ፤

የገደለዉ ባልሽ፤

ሀዘንሽ   ቅጥ አጣ፤

ከቤትሽ አልወጣ።

እንዳለዉ በአንድ ቤት ዉስጥ የሚደረግ የእርስ በእርስ የወንድማማቾች እልቂት በእርግጥም ቅጥ ያጣና ትርጉም የለሽ  እልቂት ነዉ። በሚገባ ሊጤን የሚገባዉና  በአስቸኳይ መፍትሔም ማግኘት ያለበት አሳሳቢ ችግር ነዉ። እንደሚታወቀዉ በሀገራችን ከጥቂት ወራት ወዲህ በታየዉ ለዉጥ ምክንያት የነፃነትና የዴሞክራሲ አየር እየነፈሰ ስለመሆኑ በየቀኑ የምንጋራዉ ያገጠጠ እዉነት ነዉ። ነገር ግን በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል ነዉና የተጀመረዉ ለዉጥ እንዲገፋበትና ወደፊት እንዲራመድ አልተፈለገም። ስለ ይቅርታና ምሕረት እየተሰበከ፤ ሌላኛዉ ወገን የወገኑን አንገት በሰይፍ ይቀላል። ስለ አብሮነት (ስለመደመር) እየተነገረ እርስ በእርስ በመጠፋፋት ላይ ተጠምደናል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያየ መልኩ የተደራጁና የተለያየ ሥምም ያላቸዉ አካላት  (ቡድኖች) የወያኔን መንግሥት በፅኑ ታግለዉ አሽመድምደዉታል። እንደ ቀድሞዉ መግዛት እንዳይችልም አቅመ ቢስ አድርገዉታል። ሳይወድ በግድ እራሱንም እንዲለዉጥ አስችለዉታል። ለዚህ የጀግንነት ተጋድሏቸዉም ሕዝባችን አድናቆቱን ችሯቸዋል።  ሆኖም ይህን የተቀደሰ ዓላማቸዉን ግን እራሳቸዉ መልሰዉ ፅልማሞት እያለበሱት ነዉ። ሕዝባችንን እያሳዘኑት ነዉ። እርስ በእርስ ለመተራረድና  ለመጨፋጨፍማ የቀድሞዉ ጅብ ምን አለንና አዲስ ያልጠገበ ጅብ አስፈለገን ?  እያላቸዉ ነዉ።

በጀርመን የኢትዮጵያዉያን የዉይይት ና ትብብር መድረክ የለዉጡ ዓላማ የሕግ የበላይነትን ማስፈን እንጂ፤ አዳዲስ ገዳይና ሟቾችን ማፍራት እንዳልሆነ ይረዳል። የተጀመረዉንም ለዉጥ በመደገፍ ባለፈዉ ሐምሌ ወር ፍራንከፈርት ከተማ እጅግ ቁጥሩ በርካታ የሆነ ሕዝብ ወጥቶ አጋርነቱን አሳይቷል። አሁን ደግሞ ሰሞኑን በቡራዩና አካባቢዉ በደረሰዉ የእርስ በእርስ የወገን እልቂት የተሰማዉን መሪር ኃዘን ሳይገልጽ ማለፍ ይከብደዋል። እንደመር ሲባልም ወገን ወገኑን እያየ የሚኖርበት የተሳሰተ መስመር አራማጅ ክፍሎችን አይቶ እንዳላየ በማለፍ አይደለም። ጥሩ ሲሰራ በማወደስና ከለዉጡአራማጆች ጎን በመቆም፤ ከመስመር ያፈነገጠ አስጸያፊ ድርጊት ሲፈጸም ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን አካል በማዉገዝ ነዉ፣አብሮ መሄድየሚቻለዉ።

በመሆኑም  የትብብር መድረካችን ሰሞኑን የተፈጠረዉን ችግር መነሻ በማድረግ፤

1ኛ. በደል አድራሽ ወገን ካለ ወደ ሕግ በማቅረብ በሕግ እንዲዳኝ ማድረግ ሲገባ እንደ እንስሳ የእርስ በእርስ የጅምላ ፍጅት ማድረግ የወንጀል ወንጀል ነዉና የድርጊቱ ፈጻሚዎች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ፤

2ኛ. ምንም በማያዉቁት ጉዳይ ከመኖሪያ ቀያቸዉ የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ወደ ነበረቡት ተመልሰዉ የተረጋጋ ኑሯቸዉን እንዲጀምሩ፤ መንግሥትም አስፈላጊውን ድጋፍና   ዕርዳታ እንዲያገኙ እንዲያደርግ፤

3ኛ. የአንድ ሀገር የፀጥታ ኃይልም ሆነ የክልሉ ፖሊስ ዋንኛ ተግባር እንዲህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም ቀዳሚ ተግባሩ   መሆን ያለበት የሰዉን ሕይወት ማዳን እንጂ፤ የሚመለከተዉ  እገሌን ነዉ ፣ ወደሚል የሥራ ክፍፍል ማምራት በእሬሳ ላይ እንደ መደነስ የሚያስቆጥርና ከወንጀል ፈጻሚዎቹ ተነጥሎ የሚታይ ድርጊትም ባለመሆኑ ለወደፊቱ እንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ተግባር እርማት እንዲያገኝ እንጠይቃለን።

4ኛ. ከጥቂት ዓመታት በፊት በሊቪያ በእምነታቸዉ ምክንያት አንገታቸዉ በሰይፍ በመቀላቱ የደረሰዉን አሳዛኝ ድርጊት ገና አልረሳነዉም። በቀለም፤ በደም፤ በስጋ በተሳሰርነዉ በገዛ ወንድሞቻችን የአንድ አገር ልጆች እጅ ወገን ወገኑን ሲያርድ፤ ባልን ገለዉ ሚስትን ሲደፍሩ ከዚህ የባሰ የእንስሳነት የወረደ ተግባር የለምና ይህንን ድርጊት በፅኑ የምናወግዘዉ ልባችን  እየደማ፤ ህሊናችንም እየቆሰለ ጭምር በመሆኑ ድርጊቱን አጥብቀን እንኮንናለን።

5ኛ. የሰሞኑ የቡራዩ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ በሀገራችን በየቦታዉ የሚታየዉ አንደኛው ባለቤት ሌላኛዉ መጤና ሰፋሪ እየተባለ፣ በየጊዜዉ የእርስ በእርስ ፍጅትና እልቂት ችግር በተደጋጋሚ መድረስ መሠረታዊዉ ምክንያት የጎሳ ፖለቲካ በመሆኑ፤ የዚህ ፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች በሕግ የሚዳኙበትና ችግሩንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ የሚያገኝበት ዘዴ እንዲቀየስ መድረካችን ለመንግሥት ጥያቄዉን ያቀርባል።

6ኛ. በተለይ ደግሞ በየሚኖሩበት አገር ሕግን አክብሮ መኖር ብቻ በቂ መሆኑን እያወቁ በዉጭ አገር እየኖሩ በሀገራችን አንዱን ሰፋሪ፤ ሌላዉን መጤ፤ አንደኛዉን ነባር ኗሪ ባለመብት፤ ሌላዉን መብት አልባ የሚያደርግ መርዝ የሚረጩ ፊደላዉያን ተማርን ነን ባዮች መርዘኞችን በፅኑ እናዋግዛለን! አደብ እንዲገዙም ጥሪያችንን እናቀርብላቸዋለን።

7ኛ. በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ ማዕዘናት እየታዩ ያሉ ችግሮች ሲፈተሹ የጀርባ ምክንያታቸዉ በአዲሱ አመራር ላይ የፖለቲካ ቀዉስ በመፍጠር ወደ ቀድሞዉ ዘረኛ አምባገነን ሥርዓት እንድንመለስ የሚደረግ ሤራ በመሆኑ ይህንን የማይታሰብ ሕልም ሕዝባችን እንዲያከሽፈዉ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን

ገዳይና ሟች አይደመሩም  ! ይቅርታም ገደብ አለዉ             !

ትናንትም፤ ዛሬም፤ ምንጊዜም የወገናችን ደም ደማችን ነዉ

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

በጀርመን የኢትዮጵያዉያን የዉይይትና የትብብር መድረክ (ፍርንክፈርት)