የዶ/ር አብይ የግድያ ሙከራ በኦነግ ስም በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ተፈጽሟል የሚል ክስ አቃቤ ህግ አቀረበ

አባይ ሚዲያ ዜና

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድን በመደገፍ በሰኔ 16 ቀን 2010 አም በመስቀል አደባባይ በተጠራው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የቦምብ ጥቃት አድርሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች የሽብር ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው።

በህዝቡ ተወዳጅነት ባፈሩት ጠቅላይ ሚንስርትር ዶ/ር  አብይ አህመድ ላይ የግድያ ሙከራ ያደጉት ግለሰቦች የኦሮሞ ነጻ አውጪ (ኦነግ) ደጋፊ እንደሆኑ የአቃቤ ህጉ ክስ ያስረዳል።

ዶ/ር  አብይ አህመድን በመግደል በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ እንዲደናቀፍ በሰኔ 16 ቀን በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ተሳታፊ ሆነዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ተጠርጣሪዎች አምስት እንደሆኑ ለመረዳት ተችሏል። በዚህ የሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸርው ግለሰቦች አቶ ጌቱ ግርማ ፣ አቶ ብርሃኑ ጁፋር ፣ አቶ ጥላሁን ጌታቸው ፣ አቶ ባህሩ ቶላና አቶ ደሳለኝ ተስፋዬ እንደሆኑ አቃቤ ህጉ ገልጿል።

የዚህ ቡድን አባል እንደሆነች የተነገረላት እና ነዋሪነቷ በኬኒያ የሆነች ገነት ታምሩ ወይም በቅፅል ስም ቶሎሺ ታምሩ የምትባል ግለሰብ በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ  ላይ በሰኔ 16 ቀን 2010 አም በመስቀል አደባባይ ግድያ እንዲፈጸም ከላይ የተጠቀሱትን ተከሳሾች እንዳስተባበረች እና መመሪያ እንደሰጠች አቃቤ ህጉ በክሱ ላይ አስደምጧል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር  አብይ አህመድ አስተዳደር እንደ መንግስት እንዳይቀጥል እንዲሁም በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ዶ/ር  አብይ አህመድ ተፈላጊ እንዳልሆኑ አድሮጎ ለማሳየት በተደረገው የሰኔ 16ቱ የግድያ ሙከራ ላይ ሁለት ኤፍ 1 ቦንብ እንዲሁም አንድ የጭስ ቦንብ አደጋውን ለማድረስ እንደተዘጋጀ ክሱ ያስረዳል።

ቲም ለማ እና ቲም ገዱ በህውሃት የሚመራውን መንግስት በውስጣዊ ትግል ተፋልመው  ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ የዶክተር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን መረከባቸው ያስቆጣቸው ቡድኖች በሰኔ 16 ቀን 2010 አም በፈጸሙት የቦምብ ጥቃት የሁለት ንጹኋን ኢትዮጵያውያን ህይወት ሲያልፍ ከ 160 በላይ ኢትዮጵያኖች ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።