ግሎባል አልያንስ በቡራዩና አከባቢው ለደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት እርዳታ የሚውልና ከትውልደ-ኢትዮጵያውያን የሰበሰበን 13 ሚሊየን ብር በዛሬው ዕለት ለገሰ

አባይ ሚዲያ ዜና
በኤልያስ ገብሩ

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብት፣ በቅርቡ በቡራዩና አከባቢው ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሆን 13 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር እርዳታ አደረገ።

እርዳታው በቀጥታ ወደተረጂዎች እንዲደርስ ከመንግስት ንክኪ ውጪ የሆነ የባንክ ሂሳብ መክፈቱንና ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችል 10 አባላት ያሉት ኮሚቴ መዋቅሩን የግሎባል አሊያንስ የቦርድ ሰብሳቢ  አክቲቪስትና አርቲስት ታማኝ በየነ ዛሬ ረፋድ በጣይቱ ሆቴል በተካሄደው የርክክብ ስነስርዓት ላይ ገልጿል።

global-alliance-13-million-abbay-media-1

በዚህ የርክክብ ሥነ ሥርዓትና ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አክቪስትና አርቲስት ታማኝ በየነ እንደተናገረው፣ “ይህንን ጥቃት የፈጸሙም ሆነ የተፈጸመባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው። ይህንን እኩይ ተግባር ለፈጸሙ ከብሄር ጋር እያገናኙ መኮነንና ፓለቲካ ለማትረፍ መንቀሳቀስም አግባብ አይደለም። ተግባሩ ግን በኢትዮጵያዊ ዜጎች የተፈጸመ እኩይ ተግባር ነው።” በማለት ያወገዘ ሲሆን፤ ለተጎጂዎች ግን በቻሉት ሁሉ በሰብዓዊ እርዳታ መድረስ እንደሚያሻ አጽንኦት ሰጥቷል።

በተጨማሪም ግሎባል አሊያንስ ባለፋት ዓመታትም ውጪ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ  በሱማሌ ክልል ለተፈጠረው ድርቅ፣ ከቤንሻንጉል ለተፈናቀሉ ወገኖች፣ ከሳዑዲ አረቢያ ተባርረው ለመጡ ኢትዮጵያውያን፣ በጫና ምክንያት ሀገር ጥለው ለተሰደዱ ጋዜጠኞችንና ለሌሎችም ኢትዮጵያውያን የእርዳታ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበረ በመግለጽ አስታውሷል።

በጎ ፈንድ ሚ (Go fund me) እርዳታ የማሰባሰብ ጅማሮ እንድሚቀጥል አክቲቪስትና አርቲስት ታማኝ፣ ሀገር ውስጥ ያሉ ኢትየጵያውያንም ለዚህ ተብሎ በተከፈተው ልዩ የሂሳብ ቁጥር (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ሼል ዴፓ ቅርንጫፍ፣ አካውንት ቁጥር 1000258694736) -እርዳታቸውን መለገስ እንደሚችሉ ገልጿል።

እንዲህ አይነት ወገን በወገኑ ላይ የሚፈጥረው ግጭት ከአሁን በኋላ መከሰት እንደማይገባውም መክሯል። እርዳታውን ለለገሱ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በተጎጂዎች ስም አመስግናል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ቅነሳ ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመና ዳሮታ በበኩላቸው፤፣ ለተደረገው እርዳታ አመስግነው፣ መስሪያ ቤታቸው እርዳታውን ለተጎጂዎች በቀጥታ እንዲደርስ ይህንን ከሚያስተባብሩ የኮሚቴ አባላት፣ ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና ከቡራዩ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን በጥንቃቄ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here