ብአዴን ስያሜውን ከነአርማው ሲቀይር ህውሃት 12 ነባር አመራሮቹን አሰናበተ

አባይ ሚዲያ ዜና

በባህር ዳር 12ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደእው ብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ስያሜውን ከነአርማው እንዲቀየር ውሳኔ አስተላልፏል። 

ድርጅቱ ከዚህ በኋላ ንቅናቄ ሳይሆን ፓርቲ መሆኑን በማወጅ  ስያሜውን ከብአዴን ወደ አዲሱ መጠሪያው ወደ ሆነው    የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለውጧል።

በአዲስ ስያሜ በአገራችን የሚታየውን ለውጥ ለማስቀጠል የወሰነው  የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የድርጅቱን የቀድሞውን አርማንም ቀይሯል። አዲሱ የድርጅቱ አርማ መደቡ ከላይ አረንጓዴ መሃል ላይ ቢጫ ሆኖ ከግርጌ ቀይ ቀለማትን የያዘ ሲሆን በአርማው ላይ የአባይ ወንዝ ፣ መጽሃፍ ፣ የስንዴ ዘለላ እና የኢንደስትሪ ምልክት እንደሚካተቱበት ተገልጿል።

የድንበር እና የማንነት ጥያቄዎች በአግባቡ በህገመንግስታዊ ስርአት ተገቢው መልስ እንዲሰጣቸው ያሳሰበው ይህ ጉባኤ ባለፉት ሶስት አመታት የተከናወኑትን ስራዎች ገምግሞ የቀረበውን ሪፖርት እንዳጸደቀ ተዘግቧል። 

በተያያዘ ዜናም 13ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመቀሌ ያካሄደው የህውሃት ድርጅት 12 ነባር አመራሮቹን ያሰናበት ሲሆን ከተሰናባቾቹ  አቶ አባይ ወልዱ ይገኙበታል። ህውሃት በክብር አሰናብቻቸዋለው ያላቸው ነባር አመራሮች ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አቶ ገብረመስቀል ታረቀኝ፣ አቶ ሚካኤል አብረሃ፣ አቶ ጎበዛይ ወልደአረጋይ፣ አቶ ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ፣ አቶ ነጋ በረኸ፣ አቶ ተወልደብርሃን ተስፋዓለም፣ አቶ ማሞ ገብረእግዚአብሄር፣ አቶ ጎይቶም ይብራህ፣ አቶ ሀይሌ አሰፈሃ እንዲሁም አቶ ኪሮስ ቢተው እንደሆኑ ከዘገባዎች ለመረዳት ተችሏል። 

ህውሃት የማእከላዊ ኮሜቴ አባላት ቁጥርን ከ 45 ወደ 55 እንዲያድግ ውሳኔ ሲያስተላልፍ ከሚመራበት አብዮታዊ ዲሞክራሲ  ርዕዮተ ዓለም ፍንክች እንደማይል የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአንጻሩ አዲሱ  የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሲመራበት የነበረውን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ሊቀይር እንደሚችል ተጠቅሷል።