መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም.

ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር. ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤

የፋሺሽቱ ደርግ መሪ የነበረው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በ17 ዓመት የግዛት ዘመኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የገደለ ያጉላላ፤ ያዋረደና ለስደት የዳረገ በመሆኑና ሠራዊቱን ጥሎ ፈርጥጦ ዚምባብዌ ቢደበቅም ከግብር አበሮቹ ጋር እሱ በሌለበት የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ነበር። እንደሚታወቀው የኢሕአዴግ ፕሬዚዳንት በማን አለብኝነት በቀይ ሽብር እና በዘር ማጥፋት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን የደርግ ወንጀለኞች ፍርዳቸውን ወደ እድሜ ልክ እስራት ቀይረውላቸዋል።

በብዙ የሕግ ዐዋቂዎች አመለካከት የእነርሱ ዓይነት ከባድ ወንጀለኞች የእድሜ ልክ እስራት ማለት በሀገራችን አነጋገር “እድሜ ይፍታህ” ማለት ስለሆነ ከእስር የሚፈቱት እድሜያቸው አልቆ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ መሆን ነበረበት።

በዚህም ምክንያት የደርግ ወንጀለኞች በፈጁት ሕዝብ መሃል እንደ ልብ እየተንጎራደዱና ምንም አላጠፋንም የሚል የሐሰት ተረት መጽሐፍ እያሳተሙ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በማላገጥ ላይ ይገኛሉ። ይባስ ብሎ መሪያቸው አረመኔው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፥ “እንኳን ሰው ዝንብ ገድዬ አላውቅም” በማለት በሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ላይ እያፌዘ ይገኛል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰራዊት ጠቅላይ አዛዥ ሆኖ ሰራዊቱን አጋፍጦ ከድቶ በመሸሹ፤ የሚገባው በወታደራዊ ደንብ መሰረት ፍርዱ በሰራዊቱ ፊት በጥይት ተደብድቦ መረሸን ነው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ባቀረቡት የመደመር ፍልስፍና በድንገት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ይቅርታ ተደርጎለት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ሲናገሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በትልቅ ድንጋጤና ሐዘን ተውጦ ነበር። ይባስ ብሎ፥ ከርስዎ በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ወንጀለኛው መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ቤት ሄደው በደስታና በፈገግታ አብረው ፎቶ የተነሡት ፌስቡክ ላይ ታትሞ አይተናል።

ፍትሕ ለኢትዮጵያ የተባለው ግብረ-ኀይል  አረመኔው መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ለዓለም ፍርድ ቤት ለማቅረብ ለረጅም ጊዜ የለፋበት ጉዳይ እንደዚህ ሲቀለበስ የተሰማውን ከፍተኛ ቅሬታ ለእርስዎ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወዲያውኑ ደብዳቤ ጽፈን ይህንንም ለዓለም መንግሥታት አሳውቀናል።

ክቡርነትዎ ዋሽንግቶን ዲሲ በመጡበትም ጊዜ የዚህኑ ደብዳቤ ግልባጭ እንዲደርስዎ አድርገናል።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ እርስዎ በሰጡት ማብራሪያ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የቀይ ሽብር ተሳታፊ በመሆን ስለተከሰሰ ይህ የመደመር ይቅርታ እርሱን እንደማይመለከተው በመግለጽዎ ለጊዜው ትልቅ እፎይታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጡ ስለሆነ ፍትሕ-ለኢትዮጵያ ግብረ-ኀይል ከፍ ያለ ምስጋናውን ለክቡርነትዎ ያቀርባል።

ይህ የፍትሕ ተግባር በማያዳግም ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚቀጥለውን ቀሪ እርምጃ ተጉዘው አዲሱ የዚምባብዌ መንግሥት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ወደ ኢትዮጵያ እንዲልክና ፍርዱን እንደ ግብረ አበሮቹ፥ ወንጀል በፈጸመበት  በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል እንዲፈጽም ጥያቄውን በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እንዲያቀርቡልን በትሕትና እንጠይቃለን።

ከከፍተኛ አክብሮት ጋር፤

ዶ/ር ምስማኩ አስራት

_____________________________________________

ፍትሕ ለኢትዮጵያ ግብረ-ሃይል፤ ሊቀመንበር

አምባሳደር እምሩ ዘለቀ

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ

አቶ ተስፋሚካኤል መኮንን

ነሲቡ ስብሃት

አቶ ጸሐይ ደመቀ