የዴምህትን ወታደሮች ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ ተሽከርካሪ አደጋ ደረሰበት

አባይ ሚዲያ ዜና

የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሐርነት ንቅናቄ (ዴምህት) ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል።

ንቅናቄው ኤርትራ ሆኖ ሲያደርግ የቆየውን የትጥቅ ትግል በማቆም ወደ 2500 የሚደርሱ ወታደሮቹን ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ምድር እንዲመለሱ ማድረጉ ተዘግቧል።

ወታደሮቹን ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ ሲያጓጉዝ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ በደረሰ አደጋ የሶስት ወታደሮች ህይወት እንዳለፈ ተገለጿል።

ወታደሮቹን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው ተሽከርካሪ ከኤርትራ ወደ ትግራይ ክልል እያቀና በነበረበት ወቅት ሰገነይቲ በሚባል ቦታ ላይ አደጋው እንዳጋጠመው ተነግሯል።

የአደጋው ምክንያት እየተጣራ እንደሆነ ሲገለጽ በአደጋው ከ 20 በላይ የዴምህት ወታደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ወደ ትግራይ ክልል የገቡት የዴምህት ወታደሮች ዉቅሮ በሚገኘዉ የጦር ካምፕ እንዲሰፍሩ እንደተደረጉ እና ከክልሉ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል።