የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ምርመራ ሊካሄድ እንደሆነ ተገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና

ባሳለፍነው መስከረም 30 ቀን 2011 አም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድን ማነጋገር አለብን በሚል ምክንያት ባልተለመደ መልኩ ቤተ መንግስት ሊገኙ የቻሉትን የመከላከያ ሰራዊትን ተገቢውን ክትትል ባላደረጉ አመራሮች ላይ ምርመራ ሊካሄድ እንደሆነ ተገለጸ።

የወታደራዊ ህጉ  ከሚፈቅደው የስርአት አካሄድ ባፈነገጠ መልኩ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደ ቤተመንግስቱ ያቀኑትን ከ 200 በላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከመነሻው መቆጣጠር ያቃታቸው አመራሮችን የመለየት እና የማጣራት ስራ እንደሚከናወን ታውቋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ የመረጡት መንገድ የመከላከያ ሃይሉ ከሚፈቅደው ስነ ምግባር እና ህግ ውጭ መሆኑን በማስረዳት የነዚህን ወታደሮች ድርጊት ከመነሻው ያልተከታተሉ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ምርመራው እንደሚካሄድ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ገልጸዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ጥያቄያቸውን ያቀረቡበት መንገድ የተሳሳተ ነበር በማለት የመከላከያ ሚንስትሩ አቶ ማቱማ መቃሳ ኮንነዋል።

የሰራዊቱ አባላት ጥያቄያቸውን ያቀረቡበት መንገድ የተሳሳተ ቢሆንም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ግን በሰከነ እና በተገቢ መልኩ የሰራዊት አባላቱን እንዳስተናገዱዎቸው ይታወቃል።