“ወረኛነት Vs ጀግንነት ምንና ምን ናቸው” (ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ )

0

 በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሁለት ጓደኛማቾች ከልጅነታቸው ጀምረው ሳይደባበቁ እርስ በራሳቸው ስለብዙ ኹለንተናዊ ጉዳዮች ይወያያሉ፡፡ አንደኛው ሕይወቱን በኹለንተናዊ ኹኔታዎች የሚመራ ሲኾን ሌላኛው ደግሞ ኹለንተናዊ ኹኔታዎችን በራሱ መንገድና አተያይ ለመምራትና ለመቃኘት የሚሞክር ነው፡፡

  አንደኛው የሕይወት ፍልስፍናውን ዛሬን ብቻ የሚል ሲኾን ሌላኛው ደግሞ ነገን ማዕከል ያደረገ ነገር ግን ትላንትን ያልዘነጋና ዛሬን የሚያጣጥም መንገድ የሚል፤ አንደኛው ነገሮችን አቅልሎ ሲመለከት ሌላኛው እያንዳንዷን ነገር አጥብቆ የሚመረምር ነው፡፡ እንደልማዳቸው ሲወያዩ፡- 

አድናቂ፡ “ያ ጀግና ያወራውን ሰማህ?”

ጠያቂ፡ “አልሰማሁም፡፡”

አድናቂ፡ “እንዴት አልሰማህም?”

ጠያቂ፡ “ስላልፈለኩ!!!”

አድናቂ፡ “እንዴት የጀግና ወሬ አትሰማም?”

ጠያቂ፡ “ጀግና’ ነው እንዴ?”

አድናቂ፡ “አዎ!”

ጠያቂ፡ “በምን?” 

አድናቂ፡ “እ – – – እ – – – እ – – -”

ጠያቂ፡ “ምን ሰራ?”

አድናቂ፡ “አወራ!”

ጠያቂ፡ “እና ቢያወራስ?”

አድናቂ፡ “ጤና የለህም እንዴ?”

ጠያቂ፡ “ምነው?”

አድናቂ፡ “እንዴት እንደዛ ትላለህ?”

ጠያቂ፡ “እና ምን ልበል?”

አድናቂ፡ “ሰው እንደሚለው ነዋ!”

ጠያቂ፡ “ሰው ምን ይላል?”

አድናቂ፡ “ሰውማ በወሬ ሰውን እጅጉን ያደንቃል፣ ያወድሳል፣ ከፍ ያደርጋል – ያንኳስሳል፣ ይጠላል፣ ዝቅ ያደርጋል፡፡ ወሬ እኮ የኛ መሠረታዊ ፍላጎት ነው፡፡ ያለ ወሬ ሰው እንዴት ይኖራል? ጤነኛ አይደለህም እንዴ?”

ጠያቂ፡ “ይሁና!!! – – – እስከዛሬ በወሬ የት ተደረሰ? በወሬ ላይ የተመሰረተ ጉዞስ ማንን ጠቀመ?”

አድናቂ፡ “እ – – – እ – – – እ – – -”

ጠያቂ፡ “የወሬ ባለቤቱ ወረኛ – ተቀባዩ ወረተኛ ነው፡፡ ብዙዎች በወሬ ተነድተዋል፣ ተበልተዋል፣ ተመርተዋል፣ ተዋርደዋል፣ አዋርደዋል፣ አታለዋል፣ ተታለዋል፣ አልቅሰዋል፣ አስለቅሰዋል፣ ብዙዎች ባዶዎች ሳሉ በወሬ እጅጉን ከፍ ብለው ‘ጀግና’ ተብለዋል፣ አንዳንዶች ያለ ሥራቸውና ግብራቸው በወሬ ዘመቻ ተከፍቶባቸው ጠልሽተዋል፤ ብዙዎች ወሬንና ወረኛነትን የማስመሰል እስትንፋስ አድርገው ተጠቅመውበታል – በመጠቀም ላይም ይገኛሉ፡፡”

አድናቂ፡ “እና ወሬ ፋይዳ የለውም እያልክ ነው?”   

ጠያቂ፡ “ምን? ለምን? ስለምን? ከምን አንጻር? ወሬው ትርጉም አለው? ወሬውስ ወጥነት፣ ምክንያታዊና ዕሳቤን መሠረት ያደረገ ነው? ሀሳቡና ተግባሩስ ይስማማል? ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል?”

አድናቂ፡ “እ – – – እ – – – እ – – -”

ጠያቂ፡ “እስከ ዛሬስ – በወሬው ምን ተጠቀምክ?”

አድናቂ፡ “ምንም!!!”

ጠያቂ፡ “ሕዝብስ ምን አገኘ?”

አድናቂ፡ “ምንም!!!”

ጠያቂ፡ “የወሬውስ ግብ ምንድነው?”

አድናቂ፡ “እኔንጃ!”

ጠያቂ፡ “ታድያ ለምን ትሰማለህ?”

አድናቂ፡ “ብዙ ሰዎች ስለሚሰሙት”

ጠያቂ፡ “ሕይወትህ የማን ናት?”

አድናቂ፡ “የኔ”

ጠያቂ፡ “ታድያ ዕድሜህን በአሽከርነትና በባሪያነት ለምን ታሳልፋለህ? በወሬ ስለወሬ ለወሬ በመኖርስ ለውጥ ያመጣ ማን አለ?”

አድናቂ፡ “ማንም!!! – – – ግን እኮ ብዙ ሰው ጀግና አድርጎ ነው የሚስበው፡፡”

ጠያቂ፡ “አየህ – – የነገሮች እውነት የሚረጋገጠው በነገሩ ምንነት፣ ይዘት፣ ሂደትና ተግባር አንጻር እንጂ ከተከታዩ ብዛት አይደለም፡፡ ክርስቶስ ሲሰቀል ብዙዎች እንደወንጀለኛ አይተውታል፤ ነብዩ መሐመድ ሲሰደድ ብዙዎች እንደጎጂ አይተውታል፤ ኮንፍሽየስ ሲሞት ብዙዎች እንዳልተረዱትና እንዳልተሳካለት እያሰበ ነው፤ ቡድሃን ከተቀበሉት ይልቅ ያልተቀበሉት ይበዛሉ፡፡ ጀግና መባል፣ ማስባልና መኾን የተለያዩ ናቸው፡፡ አይደል?”

አድናቂ፡ “አዎ!!!”

ጠያቂ፡ “በዓለም ላይ በርካታ ወረኞች፣ ሴረኞች፣ አስመሳዮችና ሃሰተኞች ብዙዎችን አስተዋል፡፡ ብዙዎች መሳሳታቸውን ሳያውቁት ጊዜያት አልፎ የመሳሳትን ዋጋ ከጊዜያት በኃላ ከፍለዋል – አንዳንዶች ደግሞ ሰህተታቸውን ዘግይተው በመረዳታቸው ትውልዶችን ኹለንተናዊ ዋጋ አስከፍለዋል፡፡ በማስከፈልም ላይ ይገኛሉ፡፡”

አድናቂ፡ “ታድያ እንዴት እንለያቸው?”

ጠያቂ፡ “ወረኞች ብዙ ጊዜ ከሚያስፈልግ ነገር ይልቅ የምትፈልገውን እየመረጡ ይነግሩሃል፤ የሚናገሩት ነገር ወጥነት የለውም፤ ሲበዛ አስመሳዮችና ሃሰተኞች ናቸው፤ ሰውን የሚፈልገውን እየመረጡ በመንገር ጠያቂና ተመራማሪ እንዳይኾን ያደርጋሉ፤ ከትላልቅ ጉዳዮች ይልቅ በጥቃቅንና አነስተኛ ጉዳዮች ላይ አብዝተው ትኩረት ያደርጋሉ፡፡”

አድናቂ፡ “አ – – አዎ – አንተ – ልክ ነህ!!!”

ጠያቂ፡ “ብዙ ነገር ተናግረው ፋይዳው ብለህ ስትጠይቅ የባዶ ቃላት ክምር ኾኖ ታገኘዋለህ፡፡ አስመሳይነታቸውንና ሃሰተኛነታቸውን እንደብልጠትና ብልህነት ስለሚወስዱት ራሳቸውን አላዋቂዎች ሳሉ እንደአዋቂ ያስባሉ፡፡  ብዙ ሰዎች ይህ ነገር ቶሎ አይገባንም፡፡ አንዳንዶች ሲረፍድ እንነቃለን፡፡ እጅግ ጥቂቶች ቀድመው ይረዳሉ፡፡ ነገር ግን የሚረዳቸው ሰው ያጣሉ፡፡”

አድናቂ፡ “አመሰግናለሁ!!!”

   ዕውን ወረኛነትና ጀግንነት ምንና ምን ናቸው? ፋይዳ በሌለው የወሬ ቅኝ ግዛት ውስጥ በዘቀጠ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ – ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላልን? በዚህ መንገድ የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሰ ሀገርስ ማን ነው? በጽንሰ ሀሳብና በተግባርም ቢኾን መልሱ ምን እንደሚኾን መገመት ቀላል ቢኾንም ጥያቄውን እንደጥያቄ ማንሣቱን በመጥቀስ እናጠቃል፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!