“የይሁዳ ፖለቲካ” (ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ )

0

የሀገራችን ፖለቲካ በላቀ ሀሳብና ዕሳቤ ላይ ተመስርቶ ሳይኾን ስሜትና አስተያየት የሞላበት እንደኾነ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በዚህም ኹለንተናዊ ነገሮችን ለመገመት፣ ለመተንተንና ሞያዊ ምክሮችን ለመስጠት አስቸጋሪ ከመኾኑም ባሻገር በውስጡ ማስመሰል፣ ወረኛነት (ወረተኛነትን)፣ ሃሰተኛነትና ሴራን በእጅጉ ባለቤት ማድረግን በሚጠይቀው የሥልጣን ፖለቲካችን ውስጥ ምክንያታዊ ትንታኔዎችን ማቅረብ እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ በምክንያት ኹለንተናዊ ሂደት ውስጥ የማያልፍን ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ በኹለንተናዊ አመክንዮ መፈተሽ ከባድ ነው፡፡

  ስለኾነም ከባድነቱን፣ ውስብስብነቱንና ስፋቱን ከግንዛቤ አስገብተን የሥልጣን ፖለቲካችን ከእምነት (አስተሳሰብና አመለካከት) እና ከእውቀት (ስልትና ስትራቴጂው) ባሻገር ከድርጊቱ አንጻር ስንመለከት ባሕሪያቱና ጠባያቱን የይሁዳ ፖለቲካ ብለን ልንጠራው እንችላለን፡፡

  የይሁዳ ፖለቲካ ምንድነው? ምን ምን ነገሮችን ይይዛል? በውስጡ ምን አይነት ተግባራት ይንጸባረቁበታል? የሚለውን – በሀገራችን ግለሰቦችንና ቡድኖችን እየጠቀሱ ከመተንተን ይልቅ በሀሳብ ደረጃ ያሉትን ዋነኛ አምዶች ከማዕቀፍ አንጻር መመልከት ይሻላል፡፡

   የይሁዳ ፖለቲካ ከግብር አንጻር ይሁዳዊ ባሕሪያትና ጠባያትን የያዘ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በተለይ የሥልጣን ፖለቲካ ተዋንያን የግብር መጠርያ ነው፡፡ ሰባት ዋነኛ መገለጫዎችም አሉት፡፡ መገለጫዎቹም የግብሩ ህልውና ማስጠበቂያ አምዶች ናቸው፡፡

እነዚህም፡-

አንደኛ፡- አመጣጡ በርሱ ችሎታ ሳይኾን በአምጭው ችሮታ ላይ የተመሰረተ ነው፤

   ክርስቶስ ይሁዳን መረጠው እንጂ ይሁዳ ክርስቶስን መርጦ ለሃዋርያነት አልተመረጠም፡፡ እንዲሁም ችሎታው፣ ዕውቀቱ፣ ልምዱና ክህሎቱ ሳይኾን በማይመረመር ማንነቱ የመረጠው ክርስቶስ ለምን? እንደምን? ብለን በሰውኛ የፈጣሪን ምክንያት ማወቅ ቢከብደንም ለተልዕኮ እንደተመረጠ መገመት እንችላለን፡፡

   በአንጻሩ በአንድ ነገር ፍጹም እርግጠኞች ነን፡፡ ይሁዳ በማንኛውም የሰው ልጆች መለኪያ ከሰው ልጆች ኹሉ የላቀ ችሎታ ስለነበረው እንዳልተመረጠ በደንብ እናውቃለን፡፡ በዘመኑ ከይሁዳ የሚበልጡ ብዙዎች እንደነበሩ መገመትና ማስተዋል ቀላል ነው፡፡ ኾኖም ጌታ ለታላቅ ባለሟልነት መርጦታል፡፡

   የሥልጣን ፖለቲካችንም እንዲሁ ነው፡፡ ግለሰቦችና ቡድኖች በሥልጣን ፖለቲካችን በአሽከርነታቸውም ይኹን በባለሟልነታቸው የተለየ ችሎታ፣ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ልምድና ፍላጎት ሳይኖራቸው ከምንም ተነሥተው ለትልቅ ቦታ ይታጫሉ፡፡

  ግለሰቦቹ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ፕሬዝደንት፣ ሚኒስተር፣ ዳይሬክተር – – – ወዘተ የኾኑትና የሚኾኑት አጠገባቸው ካሉ ሰዎች በብዙ ነገር የተሻሉ ኾነው ስለተገኙና ስለሚገኙ ሳይኾን የሥልጣን ፖለቲካ ኃይል የያዙ አካላት በፈለጉት ሰዓት ለፈለጉት ቦታ ያስቀምጧቸዋል፡፡ ለምን?

   የምናውቀው የተገለጠውን ስለኾነ ጌታ ይሁዳን የመረጠበትን ትክክለኛ ምክንያት ፍጹም እርግጠኛ ኾነን እንደማናውቀው ኹሉ ፍጹም እርግጠኞች ኾነን ያለ ችሎታቸው፣ ያለ አቅማቸው፣ ያለ ዕውቀታቸው፣ ያለ ልምዳቸው፣ ያለ የተለየ ችሎታቸው ለታላቅ ቦታ የደረሱና ደረሱ የተባሉ ሰዎችን አመጣጥና አካሄድ በአንጻራዊ መልኩ ከመገመት ውጪ ፍጹም እርግጠኛ መኾን አይቻልም፡፡

ኹለተኛ፡- መራጭ በዓላማ ይመርጠዋል – ተመራጭ በራሱ ዓላማ ይከተለዋል፤

  ክርስቶስ ይሁዳን የመረጠበት ዓላማ እንዳለ ኹሉ ይሁዳም እንዲሁ ክርስቶስን የተከተለበት የራሱ ዓላማ ነበረው፡፡ የዓላማው ዓይነት ልዩነት፣ የዓላማው ትርጉም ፋይዳ የተለያየ እንደኾነ ሳይዘነጋ የዓላማው ቅደም ተከተል የተለያየ እንደነበር እየተሰተዋለ – እያንዳንዱ ድርጊት ዓላማ ነበረው፡፡

    የሥልጣን ፖለቲካችን የራሱ ደራስያንና ተዋንያን እንዲሁም ተመልካቾች ያሉት ነው፡፡ ተዋንያን የደራሲውን ዓላማ አያውቁም፡፡ ደራስያን ለተዋንያን ተልዕኮን ለያይተው ይሰጣሉ – የተልዕኮዎቹን ድምር ውጤት የሚያውቁት እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ ተዋንያን ለራሳቸው ዓላማ /ዓላማዎች/ ይተውናሉ፡፡ በተወኑት ልክ ኹለንተናዊ ፍላጎቶቻቸውን የሚያሟላ ኹለንተናዊ ጥቅማ ጥቅሞችን ያገኛሉ፡፡ ተመልካቾች የሁለቱን አካላት ትርጉም ያለው ኹለንተናዊ ፍላጎት ትስስርና የኹለንተናዊ ግንኙነቶች መስተጋብር ትርጉም ባለው መንገድ ሳይረዱት የድርሻቸውን – የተመልካችነት ሚና ይወጣሉ፡፡

    የሃገራችን የሥልጣን ፖለቲካ እንዲህ ስለመኾኑ ያለፍንበት ኹለንተናዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዞም ኾነ ያለንበት ነባራዊ ኹለንተናዊ ኹኔታ ዐቢይ ምስክር ነው፡፡  

ሶስተኛ፡- ይሁዳ ከሃዋርያት መሐከል ሥልጣን ነበረው፤

   ክርስቶስ ለይሁዳ ከመመረጥ ባሻገር ከተመራጮችም መሐከል ሥልጣን የነበረው እንዲኾን ስለማድረጉ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ይሁዳ ሥልጣኑን ተጠቅሟል፡፡ ሌሎችም እሱን ለወዳጅነት የመረጡት ከቀረቤታውና ከኃላፊነቱ አንጻር ነው፡፡ የሥልጣን ፖለቲካችን ከመመረጥ ባሻገር በተመራጮች ላይ ሥልጣን ይኖረን ዘንድ የሚሰጥና የሰጠ ነው፡፡ ስለኾነም ሥልጣን ያላቸውን ብዙዎች ይፈልጓቸዋል፡፡ እነሱም ብዙዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ይህንም በመጠቀም የተለያዩ ሴራዎችን ይጎነጉናሉ፡፡ የተሳካላቸው ጌቶቻቸውን ወደ አሽከርነት ይለውጣሉ፡፡ ያልተሳካላቸው ደግሞ አሽከርነቱንም ራሱ ያጣሉ፡፡

አራተኛ፡- ግንኙነቱ ከወዳጅ ባሻገር ይሻገራል፤

  ይሁዳ ግንኙነቱ ከወዳጆቹ፣ ከመሰሎቹና ወዳጅና መሰል ሊኾኑ ከሚችሉት ብቻ ሳይኾን ፍጹም ከክርስቶስ ተቃራኒ ከኾኑ ወገኖችም ጭምር ነበር፡፡

    የኛ የሥልጣን ፖለቲካ ተዋንያንም እንዲሁ ግንኙነታቸው በርዕዮተ ዓለምና በሀሳብ ከሚመስሏቸው ብቻ ሳይኾን እጅግ ሊያጠፏቸው ከተነሱ ወገኖችም ጋር ጭምር የአደባባይና የምሥጢር ግንኙነቶችን ይፈጥራሉ፡፡ ለምን? ምክንያቱም የሥልጣን ፖለቲካችን በሃሰተኛነት፣ በአስመሳይነትና በሴረኛነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

   “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው፡፡” የሚለው ብሂል ለውጭ ትግል ብቻ ሳይኾን በውስጥ ለሚደረግ ኹለንተናዊ ትግልም የሚያገለግል ነው፡፡ ሴራው በውጭ ላለ ብቻ ሳይኾን ለውስጥም ያገለግላል፡፡ ሃሰተኛነቱ፣ ውሸታምነቱ፣ አጭበርባሪነቱ፣ አስመሳይነቱና መሰሪነቱ ለጋራ ተቀናቃኝ ብቻ ሳይኾን ለራስ በወዳጆችና በመሰል መሐከልም ለሚደረግ ኹለንተናዊ ትግል ያገለግላል፡፡

   ይሁዳ የልቡን መሻት ደብቆ ከጌታው ጋር እንደተጓዘ ኹሉ ክርስቶስም የይሁዳን የልብ መሻት እያወቀ አብሮት እንዲጓዝ አድርጓል፡፡ የሥልጣን ፖለቲካችንም ማን ምን እንደሚሻ በደንብ እየታወቀ አብረው እንዲጓዙ ተደርጎበታል፡፡ እየተደረገበትም ይገኛል፡፡

አምስተኛ፡- አስመሳይነት፣ ቅናትና ትዕቢት መለያዎቹ ይኾናሉ፤

   ይሁዳ እጅግ አስመሳይና ቀናተኛ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የሥልጣን ፖለቲካችን በአሰመሳዮች፣ በቀናተኞችና በትዕቢተኞች እንደተሞላ ይታወቃል፡፡ አንዳንዶች የጀርባ ታሪካቸውን ዘንግተው – ዛሬ የተወለዱ ይመስል ኹሉን ነገር እንደአዲስ መጀመር ይሻሉ፡፡     

ስድስተኛ፡- ፈጣሪውንና ወዳጁን አሳልፎ ይሰጣል፤

  ይሁዳ የልቡን መሻት ደብቆ አቆይቶ ምቹ ኹኔታን ሲያገኝ ፈጣሪውንና ወዳጁን አሳልፎ እንደሰጠ ኹሉ፡፡ የሥልጣን ፖለቲካችንም ከምንም አንሥተው ትልቅ ደረጃ ያደረሷቸውን በመክዳትና በመብላት የተሞላ እንደኾነ ታሪክም ኾነ አኗኗራችን ዐቢይ ምስክር ነው፡፡ ሲጠሩ “አቤት” – ሲላኩ “ወዴት” ብቻ በማለት ረዥም ዓመታት ያገለገሉ ተላላኪዎች ምቹ ኹኔታዎችን ሲያገኙ ያገለገሏቸውን ይክዳሉ፡፡ አሳልፈውም ይሰጣሉ፡፡

  ይሁዳ አንድ ቀን አሳልፎ እንደሚሰጠው ክርስቶስ እንደሚያውቅ ኹሉ የሥልጣን ፖለቲካ ደራስያንም – ተዋንያኖች ከቆይታ ብዛት ወደ ደራሲነት ሲሸጋገሩና ለመሸጋገር ሲተጉ እነሱን አሳልፈው እንደሚሰጧቸው በደንብ ያውቃሉ፡፡ ምክንያቱም እነሱም አሳልፈው ስለመጡ – የመጡበትን መንገድ ልዘንጋ እንኳ ቢሉ መዘንጋት ስለማይችሉ – ከፍ ሲልም የታሪካቸው አንድ አካል ስለኾነ አሳልፎ መስጠትን ብቻ ሳይኾን ጊዜና ኹኔታዎች ሲቀያየሩ አሳልፎ መሰጠት እንዳለ በደንብ ያውቃሉ፡፡  

   ሰባተኛ፡- ታሪካዊ ተጠያቂነት፤

   ይሁዳ በምግባሩ የተነሣ ራሱን ብቻ ሳይኾን ቤተሰቦቹንና የሀገሩን ሰዎች እንዳሳፈረና ማሳፈሩም ትውልዶችን ተሻግሮ የሰረቀ ኹሉ በይሁዳነት እንዲጠራ ምክንያት ከመኾን ባሻገር “ባልተወለደ ይሻለው ነበር፡፡” ተብሎ ተጽፏል፡፡ በሥልጣን ፖለቲካ ተዋንያን የኾኑ ይሁዳዎችም ከግብራቸው የተነሣ ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው የሚያፍሩባቸው ከመኾናቸውም ባሻገር የአካባቢያቸው ሰዎች አንገታቸውን የሚደፉባቸው እንደኾኑ ይታወቃል፡፡

   ከላይ በሰባት ነጥቦች እንደተመለከትነው የሀገራችን ፖለቲካ ይሁዳዊ ባሕሪያትና ጠባያትን የያዘ እንደኾነ አስቀምጠናል፡፡ ጥያቄው ከዚህ መኾን ባሻገር በዚህ ውስጥ የምንፈልጋትን ሀገር ማየት እንችላለን ወይ? ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥንስ ማምጣት እንችላለን ወይ? በዚህ ጉዞ ከሌሎች መሠል ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ መኾን እንችላለን ወይ? የሚል ይኾናል፡፡

   ይሁዳዊነት በይሁዳ ተጀምሩ በይሁዳ ያበቃ ሳይኾን ይሁዳ ከመወለዱ በፊት የነበረ፣ ከተወለደም በኃላ የነበረ፣ ከህልፈቱም በኃላ ቢኾን ትውልድ ተሻግሮ ያለና የሚኖር ነው፡፡ በሥልጣን ፖለቲካ ውስጥ ይሁዳዊ ባሕሪያትና ጠባያት – ስለሕዝብና ስለሀገር በአደባባይ እያነቡ በጓዳ ሕዝብና ሀገርን የሚጎዳ ተግባር መስራት፤ ስለሀገር ፍቅር አብዝተው እየለፈለፉ የሀገር ጠላቶች አሽከርና ባሪያ መኾን፤ ሕዝብ ጌታ ነው እያሉ እየደሰኮሩ ሕዝብን አሽከር ማድረግ፤ ሕዝብ ከሚያስፈልገው ይልቅ ደካማ ጎኑን ስሜታዊነትና አማኝነት በመጠቀም የሚፈልገውን በመንገር እንዲሰክር ማድረግ፤ በተለያየ ቦታ ፍጹም ተቃራኒ የኾኑ ነገሮችን መናገር፤ ሴራ መጎንጎንን እንደሥልጣኔ መውሰድ፤ – – – ከብዙ በጥቂቱ ተጨማሪ ማሳያዎቹ ናቸው፡፡

   የሀገራችን የሥልጣን ፖለቲካ ከይሁዳዊ ባሕሪያትና ጠባያት ወደ ትክክለኛ ሕዝባዊ (አብርሃማዊ) ባሕሪያትና ጠባያት ካልተሻገረ በቀር ኹለንተናዊ መሠረታዊ ለውጥ የማምጣትም ኾነ የመሠልጠን ሕብረተሰባዊ ጉዞ ወደ ኃላ እንጂ ወደ ፊት እንደማይጓዝ መረዳት አስፈላጊ ይኾናል፡፡ ስለኾነም ኢትዮጵያውያን ሕዝባውያን /አብርሃማውያን/ ከወዴት አሉ? ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!