የገና ዳቦ – ዓቢይ አህመድ! እባካችሁ ከጎን አታንድዱበት!(ድንበሩ ደግነቱ)

0
  1. የዘር ቡድን ልዩነቱን እያከረረ ነው!

ሀ. ኤልቲቪ ከክቡር ኦቦ በቀለ ገርባ ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ በጥሞና ተከታተልኩት። ከዶ\ር ደሳለኝ ጋር ያደረገውን ቆይታም አላለፍኩትም። ኤልቲቪ ከምናውቃቸው ጋዜጠኞች ላቅና ለየት ያለች ጋዜጠኛ አፍርቶልናል። ምን አለ ሁለት ወይ ሶስት የሱዋን አይነት ባገኘን። ከጉዋደኞቹ የረዘመ ማሽላ ወይ ለወፍ ወይ ለወንጭፍ እንዲሉ እንዳይሆንብን እግዜር ይጠብቃት። ወፍም ወንጭፍም ከውስጥም ከውጭም በዝቶዋል። እስካሁን የማውቀው አንድ ወንጭፍ ስቶዋታል። ቱቱ ብያለሁ ከወደፊቱም ይሰውራት።

“ክቡር ኦቦ በቀለ ገርባ ኢትዮጵያዊ ነዎት ወይስ ኦሮሞ?” ተብሎ ለተጠየቁት ጥያቄ የሰጡት መልስ አገራችን የሚጠብቃትን መከራ የሚጠቁም ነው። ዶ\ር ዓቢይ የተጣዱበትን ምድጃ የሙቀት መጠንም ያመላክታል። “ኢትዮጵያዊ ነኝ።” ወይም “ኦሮሞ ነኝ።” ብለው ባጭሩ መመለስ ሲችሉ ዙሪያ ጠመዝማዛውን ሄደው ልጃቸው ሴት መሆንዋን፥ እሳቸውም ረዥም መሆናቸውን ሁሉ ነገሩን። ለማ ሱስ የሆነበትን ኢትዮጵያዊነት ለመሸሽ ክቡር አቶ በቀለ ገርባ ዙሪያውን ዞሩ። ጋዜጠኛዋ ማንን ምን መጠየቅ እንዳለባት ጠንቅቃ ታቃለችና ይህን ጥያቄ ለጋሞው ተወላጅ አሠፋ ጫቦ አታቀርብለትም እንጂ፥ ብታቀርብለት “ጥያቄው ስቱፒድ ነው።” ይላት ነበር። የአልጀዚራ ጋዜጠኛ ለኦቦ ጃዋር ያቀረበችው ጥያቄ “መጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ነህ ወይስ ኦሮሞ?” እንጂ ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ጥያቄ አልነበረም።

ክቡር ኦቦ በቀለ በዚሁ ቃለ መጠይቃቸው ውስጥ፥ ህወሀት በአዲስ አበባ ዙሪያ በግፍ የሚነቅላቸውን ገበሬዎች ዋይታ እስካስተዋሉበት የህወሀት የፖለቲካ የበላይነት የቅርብ ዘመናት ድረስ፥ ፖለቲካ በዞረበት የማይዞሩ እንደነበሩ ገልፀዋል። ሌሎች የኦሮሞ ብሔርተኞች እንደሚጠቅሱት፥ አገርን አንድ በማድረግ ዘመቻው የተረገጠው ቁዋንቁዋና ባህል አልቆጠቆጣቸውም ነበር። የፊደል ሠራዊትን ለኦሮምኛ ተናጋሪው ኅብረተሰብ ለማዳረስ በመወጠናቸው፥ ዘብጥያ የተወረወሩት የሜጫ ቱለማ ማኅበር አባላት በደል ወኔያቸውን አልቀሰቀሰባቸውም ነበር። ታዲያ ምንድን ነው ከኢትዮጵያ ይህን ያህል ያስፈነገጣቸው ነገር? ምንድን ነው ከኦነግ ጋር እጅና ጉዋንት እንዲሆኑ ያደረጋቸው መርህ? ከመገመት እንቆጠብ – ጊዜ ያሳየን ብለን።

ቤቲ “እኛ በሞትንለት ትግል ጠላቶቻችን ቤተ መንግሥት ገቡ።” ያሉበትን ምክንያት በተመለከተ ለሰነዘረችው ጥያቄ፥ ከአንዳጋቸው ቀድሞ ለእሥር ስለተዳረገ አንድ የኦሮሞ ታጋይ በመዘርዘር መልስ ሰጥተው አልፋቸዋለች። ቤቲ በዶ\ር ደሣለኝ ላይ ያሳየችውን ሞጋችነት እዚህ ጋ አላልታዋለች። ሰው ስለሆነች በጊዜው አምልጦዋት ይሆናል። ወይም የሳታት ወንጭፍ በሁለተኛው እንደማይምራት፥ አነጣጣሪውም ጀዋር እንደሚሆን አውቃ ሊሆን ይችላል። “ላንቺ ነው ኢትዮጵያ!” እያለ አይሆኑ ሆኖ ልጆቹን በትኖ በሀሳብ ሳይሆን በእግሩ፥ እየራበው እየጠማው በበረሀ የተንከራተተላት፥ ከዛም ቀን ክዶት በወሀኒ የማቀቀላት፥ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዴት የክቡር አቶ በቀለ ገርባና ወክለዋለሁ የሚሉት የኅብረተሰብ ክፍል ጠላት እንደሆነ አልሞገተችም። አንዳርጋቸው ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ሲከፍል ከወያኔ ሌላ ጠላት አልነበረውም። መስዋዕትነቱ ኦርሞንም ላካተተ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነበር። እንደኔ በአንዳርጋቸው ክፉ መዋል የበሉበትን ወጪት መስበር ነው። ይህ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ባህል አይደለም። የክቡር አቶ በቀለ ገርባ የግል ባህርይ ሊሆን ይችላል።

ለ. ዘረኝነት ከየትም በኩል ይምጣ አደገኛና ቁሻሻም ነው። የፌስ ቡክ ደንበኛ አይደለሁምና ቤቲ ቃለመጠይቁን ባታደርግ ኖሮ በዐማራ ድርጅት (ዐብን) መሪነት ከተሰየሙት ግለሰቦች የፌስ ቡክ ገፅ ላይ የቃረመቻቸውን አቁዋሞች ባላየሁ ነበር። “ሰው ፈጣሪውን እንደሚያከብር ሁሉ ኢትዮጵያም ፈጣሪዋን አማራን ማክበር አለባት።” “አማራ የሰውነት መለኪያ ውሃ ልክ ነው።” የዓመቱ ፀያፍ ጥቅሶች። ማኅበረሰብን የሚያንጽ (building block) ግለሰብ ነው። በጊዜው አስገዳጅነት ለመምረጥ ተገድጄ አጣብቂኝ ውስጥ ብገባ ደምሬ ቀንሼ እንደ ግለሰብ ዐማራ በሚባለው ጠገግ ውስጥ የምወድቅ ነኝ። ለኔ ከላይ የተገለፁት አባባሎች በጣም ፀያፍና ውነትም አይደሉም። “ዐማራ ኢትዮጵያን ፈጠራት።” የሚለው ትርክት ሀሰት ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያን ዕድሜ ወደ ከመቶ ዓመታት ብዙም ያልዘለለ ያሳጥራል። ዐማራ የሚለውን ፖለቲካዊ ማንነት መጀመሪያ መሠረት የጣለው ጣሊያን ነው። ከዛ ቀደም የጎጃም ንጉሥ የሸዋ ንጉሥ የወሎ ንጉስ ሕዝብና ድንበር ነበራቸው እንጂ ዐማራ በሚል ስም አይጠሩም ነበር። የኢትዮጵያ ዕድሜ ከ 3000 ይዘላል እያልን አማራ ፈጠራት ማለት ከተራ ቅጥፈት በላይ አደገኛም ነው። በዘር መደራጀት ከሌላው ጋር ለዘለቄታው አብሮ መኖር የማያስችል መሆኑንም ጠቁዋሚ ነው። ኢትዮጵያውያን ዘር ሳይለዩ ኢትዮጵያን ፈጥረዋታል። ወይም ጀዋር አዳልጦት አንድ ጊዜ እንደተናገረው እግዚአብሔር የ80 ብሔሮች አገር አድርጎ ፈጥሮዋታል።

“አማራ የሰውነት ውኃ ልክ ነው።” የሚለው ዘግናኝ አባባል ከሰው አይደለም ከአምላክም ያቆራርጣል። የኢትዮጵያዊነት መለኪያ አይደለም የተባለው፥ ልብ በሉ የሰውነት ነው። ይታያችሁ ለማ መገርሳ ከእኔ ተወዳድሮ አዎ ብቁ ሰው ነው ሲባል፥ ወይም ይሄ ይጎለዋልና ተስተካክሎ ይምጣ ሲባል። እንዲህ የሚያስቡና ለዚህ ተግባራዊነት የሚታገሉ መሪዎች ኢትዮጵያን ቶሎ አፈራርሶ ለመጨረስ ይረዱናል? ወይስ ኢትዮጵያን ለመገንባት? በዐማራነቴ እንዳፍር እንጂ እንድኮራ የሚያደርጉኝ አባባሎች አይደሉም። እስኪደክመኝ ባስብ ባስብ ከዚያም ከዚህ መፈናቀልና መሳደድ ለበዛበት አማርኛ ተናጋሪ ወገን፥ አባባሎቹ እንዴት ሊጠቅመው እንደሚችል አልገባህ አለኝ። ዓለምነው መኮንን ያቆሰለውን ልብ ለማሻር ከሆነም፥ ሁለት ስህተቶች አንድ ትክክል አይወጣቸውም። እነዚህ ሁለቱም (በ ሀ ና ለ የተጠቀሱት) ከላይ እየነደዱበት ዳቦውን እያሳረሩት ነው።

  1. ህወሀት አድብቶ ጊዜ እየጠበቀ እያጠቃ ነው!

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት የረከሰበት ህወሀት፥ ፖለቲካው ቢሰናከልበትም በዘረፋ ያካበተው ጥሪት በቀላሉ የሚሙዋጠጥ ባለመሆኑ አገር ለመበጥበጥ ያለው አቅም ላልተወሰነ ጊዜ የሚያዘልቀው ነው። እዛም እዚህ ብሩን እያፈሰሰ አገር እንዳይረጋጋና ለውጡ እንዳይሳካ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ከአፋር፥ ከቤኒ ሻንጉልና ከጋምቤላ ክልሎች የህወሀት ጥፍሮች ገና አልተነቀሉም። የህወሀት ማንነትና ምንነት መገለጫ የሆነውን፥ በወንጀል የሚፈለገውን ጨካኝ በማን አለብኝነት በኃላፊነት ሾሞዋል። ህወሀት ዛሬም በዳቦው ሥር እሣቱን እያንበለበለው ነው።

  1. ለውጥ ያስፈራል ዋጋም ያስከፍላል!

ለሀያ ሠባት ዐመታት የተሰበከው ጥላቻ ያደነደው መንፈስ በተለያዩ የመንግሥት ሥልጣን ላይ እስካሁን ይገኛል። የዘረፋው መንገዶች እንደሚዘጋ ሲገነዘቡ፥ ትናንት የሰሩት ወንጀል ለውጡ ከተሳካ ነገ ሊያስጠይቃቸው እንደሚችል እያሰቡ የለውጡን መሰናክል ሆነዋል። አገር እንዳይረጋጋ፥ ለውጡ እንዳይሳካ፥ የመሪው ስብዕና እንዲወርድ የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። እነዚህም ከላይ የሚነደውን እሣት ይቆሰቁሱታል።

  1. ሚዲያው ችግሩን ሳያስተውል ቀድሞ አድጎዋል!

ሚዲያዎች የሚሰጡት ትንታኔ አገሪቱና በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ያሉበትን መከራ ያገናዘበ ሳይሆን የራሳቸውን የተንታኝነት ክህሎት ለማሳየት የሚጥሩ ይመስላል። ከሩቅ ሆነው እየገመቱ ይኸው ያልነው ሆነ ለማለት ይታትራሉ። የሴረኞቹን ጎራ ሰልሎ በማጋለጥ ለውጡን ለመርዳት ጥረት በማድረግ ፈንታ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከላይና ከታች እየነደደበት ያለውን ዳቦ ከጎንም እየለበለቡት ነው። የአዲስ አበባ ወጣት በማይረባ ብሽሽቅ ተጠምዶ እንዲደራጅና የመንግሥቱን ራሥምታት ከፍ እንዲያደርገው እየቀሰቀሱ ነው። መብትን ሁሉ በአንድ ጊዜ መጠየቅ እስካሁን የተገኙትን መብቶችም ማስወሰድን ሊያመጣ እንደሚችል ማገናዘብ ተስኖዋቸዋል። የነበርንበትን የህወሀት የበላይነትን የገሀነም ዘመን ዘንግተውት፥ በአንድ ጊዜ የአሜሪካን ዴሞክራሲ ደረጃ እንድንደርስ ዓቢይን ሱሪ ባንገት እያሉት ነው።

ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት ሲጠይቁ ነበር። ዶ\ር ዓቢይ ለውጡን ማንም ከጠበቀው በላይ በማፋጠናቸው የሽግግር መንግሥትን የሚጠይቅ ድምፅ አሁን የለም። ማንም በምንም ቢለካው ዶ\ር ዓቢይ ያበጁት ከብዙዎች ግምት በላይ ነው። ጥፋት አልተሰራም ለማለት አይደለም። የዶ\ር ዓቢይ የለውጥ ሂደት ዛሬ ቢጨናገፍ የአገሪቱ ህልውናም የሚያከትምበት ቀን ነው የሚፈጠረው። OMN ላይቸግረው ይችላል ኢሣት ግን የለፋበት ሁሉ ገደል ገብቶ አመድ አፋሽ ከመሆኑም በላይ አዲስ ስም ማውጣት ያስፈልገዋል። ቢያንስ ‘ኢ’ን ከስሙ ውስጥ ለመፋቅ ይገደዳል። ይህ አይሆንም አንበል። “ኤርትራ አንገት ነች።” ሲል የነበረው የደርግ መንግሥት አንገቱን አስቆርጦ በኖዋል። አሁንም ሊሆን ይችላልን ይዘን፥ ያ እንዳይሆን ጠንክረን ነገሮች ወደፊት ይሻሻላሉ በሚል ተሥፋ ከለውጡ ኃይሎች ጎን እንቁም። በነገራችን ላይ በአሜሪካ ካሉ ሜድያዎች ወገንተኛነትን የሚያሳዩ አሉ። በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ሁልጊዜም የሚቃወሙ እንዳሉ ሁሉ ሁልጊዜም የሚደግፉም አሉ። አሜሪካ ችግር ውስጥ በገባች ጊዜ ውነትን (objectivism) ገሽሽ አድርገው ተባብረው ለአገሪቱ ጥቅም በአርበርኝነት አንድ ሆነው ይቆማሉ። ኢትዮጵያም የሜድያውን አርበኝነት የምትፈልግበት ነው ወቅቱ። ዓቢይ አፍ አውጥቶ “እርዱኝ!” ብሎዋል።

ዶ\ር ዓቢይ ከሚነቀፉበት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን አቅመቢስ በመሆናቸው የሚሞት፥ የሚፈናቀልና ጥቃት የሚደርስበት ዜጋ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መሄዱ ነው። ይሄንን እሳቸውም የሚያውቁትና እንቅልፍ የሚያጡበት ጉዳይ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ለሀያ ሰባት ዓመታት በቤተ ዕምነቶች ላይ በሽምግልናና በባህል ላይ የተደረገው ጥቃት አገሪትዋን ኦና አድርጎዋታል። ትኅትና ይሉኝታና መደጋገፍ ከእያንዳንዱ ዜጋ ዐዕምሮ እንዲረግፉ ተደርገዋል። ተቁዋማት የሕዝብን አደራ ተሸክመው በተጠያቂነት መንፈስ ሥራቸውን ከሚያከናውኑ ይልቅ ኪሳቸውን የሚያደልቡበትን መንገድ ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ተምረዋል። በጥቅሉ ማኅበራዊ ካፒታልም ሆነ የሕግ አስከባሪ ተቁዋማት አቅም ዜሮ ነው። ይህን ችግር መፍታት ጊዜ ይወስዳል። አማራጭ የለንም – መታገስና በምንችለው መንገድ ሁሉ መደገፍ ብቻ።

ሌላው ነቀፋ ግልፅ አለመሆናቸው ነው። አንዳንዴም ከመለስ ዜናዊ ጋር የሚወዳደሩ ሀሰት ተናጋሪ አድርገው የሚስሉዋቸውም አሉ። አገሪቱ ያለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ የአስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ ግድ ሊል ምንም ባልቀረው ሁኔታ ውስጥ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ቀደም ብለው በገቡት ቃል መሠረት መንግሥታዊ መረጃን ከሥር ከሥሩ ቢለቁ ኢትዮጵያ ውስጥ ተንጋግተው የገቡ እርስ በእርስ የማይታረቅ ቅራኔ ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች እንደመሆናቸው መጠን ድርጅቶቹ የሚሰጡት ምላሽ አገሪቱን ገደል እንዳይከታት ያስፈራል። ተቁዋማቱ ተገንብተው እስኪያልቁ ትዕግስትን ቢሰጠን።

በዶር ዓቢይ ላይ ከሚነሳባቸው ወቀሳዎች ሌላው፥ ሁሉ ቦታ ሁሉን ነገር አዋቂ ሆነው እየታዩ የራሣቸውን ስብዕና እየገነቡ ነው ይህ ደግሞ ለአንባገነንነት ይጋብዛቸዋል የሚል ነው። ስለዚህም አንዳንድ ጉድፎችን እያወጡ ለማሳየት በመጣር ሊገነቡ ነው ብለው ያመኑትን ስብዕና ለመናድ ጥረት ሲደረግ ይታያል። በዚህ ክፉ ቀን የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ በአንድና በሁለት ግለሰቦች እጅ ባለበት ሁኔታና ከኢትዮጵያ መፍረስ እናተርፋለን ብለው የሚጠብቁ ወገኖች በሞሉበት ወቅት፥ የዶ\ር ዓቢይ ስብዕና መግነን ከመኮስመኑ በተሻለ ኢትዮጵያን ይጠቅማል። ሥልጣን ላይ በወጡበት ሰሞን በደቡብ በተደረገ ግጭት “በሚቀጥለው ሣምንት መጥቼ እስክንነጋገር ድረስ ግጭቱን አቁሙ!” ብለው ከርቀት የላኩት መልዕክት ተቀባይነት አግኝቶ ግጭቱ ቆሞ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። አሁንም ያልረጋች አገር ነችና ልቀው መታየታቸው ከጉዳቱ ጥቅሙ ያይላል – እምንመካባቸው ተቁዋማት እስኪገነቡ ድረስ።

ዶ\ር ዐቢይ ለረዥም ጊዜ፥ ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምረው የሠሩበት ነውና ከከበቡዋቸው ባለሥልጣኖች አንፃር በዕውቀት ገዝፈው የወጡ ናቸው። የሣቸው መግዘፍ ብቻ አይደለም ብዙዎቹ ካድሬዎች የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ሚ\ር ደኤታ ጥሩ አድርገው እንዳስረዱን፥ በካድሬ ትምህርት ቤት (ዶምቦስኮ) ገብተው ስፍትዌራቸው ዲሊት ተደርጎ አብዮታዊ ዴሞክራሢ የተጫነበት በመሆኑ ለዶር ዓቢይ ተማሪ እንኩዋን የመሆን ብቃት ያንሳቸዋል። ሥልጠና በሚሰጡበትም ሆነ ትንታኔ ሲሰጡ ብስለት እንዳላቸው ብዙ ምሁራን የመሰከሩላቸው ነው። በተወካዮች ምቤት መናገሪያውን በያዙ ጊዜ ሁሉ የፓርላማ አባላት በማሸለብ ፈንታ፥ ጆሮዋቸውን አቁመው፥ ዐይናቸውን በልጥጠው፥ አፋቸውን ከፍተው ሲያዳምጡዋቸው ዶ\ሩ አንድም ስጦታ ወይም የረዥም ጊዜ ጥረት ስኬት ባለቤት እንደሆኑ መስካሪ ነውና ስብዕናቸውን አፍ አውጥተው መናገር አይጠበቅባቸውም። ለፍተው ያገኙትን ብስለትና ዕውቀት ለምን ልንነሳቸው ይከጅለናል?

ኢሳትና OMN የፋይናንስ ችግር ይገጥማቸዋልና ባለሀብቶች ማስታወቂያችሁን በነሱ ላይ አውጡ ብለው ላደረጉት የፈንድ ሬይዚንግ ውለታ፥ “አለምነህ ዋሴን በስም የጠቀሱት ለኖቤል ሽልማት ስላጫቸው ነው።” የሚል መልስ ማግኘታቸው ያጎረሰን እጅ የመንከስ ያህል ነው። ያልተረጋገጠ ግምት ከመሆኑም በላይ ተራ ብሽሽቅ ነው። ያስተዛዝባል። ወታደር በመሆን ፋንታ ሲቪል ቢሆኑ ኖሮ የወታደሮቹ ጥያቄ አጉዋጉል መጨረሻ ይኖረው እንደነበር መግለፃቸው ራስን ማግዘፍ ሆኖ አልታየኝም። በተለይ ወታደሩ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ፖለቲካውን ካጨቀየው በሁዋላ ወታደርነት የሚኮራበት ሙያ አልነበረም። ከቀደሙት መሪዎች የሚሻሉበት የትምህርት ደረጃ አላቸው – ፒኤችዲ። ራሳቸውን ለማግዘፍ ከመንግሥቱ ኃ/ማ ጋር መወዳደር አይጠበቅባቸውም።

ዶ\ር ዓቢይና ቡድናቸው ካለሕዝቡ ማናም ከጎናቸው የለም። ይህንንም አፍ አውጥተው ተናግረዋል። ይህ ብቻ አይደለም ለኢትዮጵያም በዚህ ወቅት ከዶ\ር ዓቢይና ቡድናቸው በላይ ምንም ምድራዊ ጠባቂ የላትም። በተለይ የአዲስ አበባ ሕዝብ አሁንም ከጎናቸው እንዳይለይ ሜድያዎች በርትተው ሊሰሩ ይገባል። አዲስ አበባችንን እናስመልስ ብለን ኢትዮጵያችንን እንዳናስወስድ። ሰንበትን እየገደፉ በስራ የሚጠመዱትና ከሰማያዊው ፀጋ ቆንጥረው የሚያፈሱት ለኢትዮጵያ ሲሉ ነውና ምሣሌነታቸውን ባንከተል እንኩዋ በትችት ከመጥበስ እንታቀብ። ሜድያ ዐይን ጆሮና አንደበት ብቻ ሳይሆኑ አመዛዛኝ ዐዕምሮም ሊሆኑ የግድ ነው – ድልድዩን እስክንሻገር። ኢትዮጵያን እስከጠቀመ ድረስ አይቶ እንዳላየ፥ ሰምቶም እንዳልሰማ ማለፍ፥ አይቶና ሰምቶም ዝም ማለት አርበኝነት ነው። ከኢትዮጵያ የሚበልጥ እውነት የለም።

ይልቅ:

  • ፕሮጀክት ተነድፎ የትግራይ ወጣት በህወሀት ላይ እንዲነሳበት ቢሠራ።
  • ኢትዮጵያ ከርሰ ምድርዋ ሙሉውን አዱኛ መሆኑንና ወጣቱ ተስፋው የትየለሌ መሆኑን ቢስበክ
  • በቪድዮ የተደገፈ አገርን የማስተዋወቅና የማስጎብኘት ፕሮግራም ቢተላለፍ
  • የሶስት ሺህ ዘመናት የአንድነት ታሪካችንን መለፈፍ
  • የብሔር መከፋፈል አደገኛነትን በምሣሌ በኪነትም ተደግፎ ማራገብ ላይ ብንጠመድ
  • የሞራል ትምህርቶች በወጣቱ እንዲሰርፁ ቢደረግ ወዘተ