አንፀባራቂው ባህላዊ ሽምግልና በዕርቅ ዘመን ዕምጥ ገባ ስምጥ! – ፕሮፌሠር ኤፍሬም (ድንበሩ ደግነቱ)

0

የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ክረምት እየገባ ነው። ሁልጊዜም ክረምት ሲገባ ጭንቅ ይለኛል። ቅዝቃዜው፥ በረዶው፥ የቀኑ ማጠር፥ የማሞቂያው ቢል ከፍ ማለት ሁሉ ያስጨንቃል። በበጋው ያማረባቸውና ገመናቸው በአረንጉዋዴ ከፈን የተሸፈነው ዛፎች ቅጠላቸው እየረገፈ ገመናቸው ሲጋለጥ፥ የህይወትን ተቃርኖ እያስታወሰኝ ገና ክረምቱ በቅጡ ሳይገባ ብርድ ብርድ ይለኛል። እከክን የሰጠ ጥፍር አይነሳም እንዲሉ፥ ጠቅላይ ሚ\ሩ “አገር የዛፍ ቅጠል አይደለም ዝም ብሎ የሚረግፈው!” የሚለው ንግግር (conviction)፥ እየታወሰኝ  ከላይ ቢበርደኝም ውስጤ በሙቀት ይሞላል። እግዜር ብርታቱን ይስጣቸውና የጠቅላይ ሚ/ሩ እርምጃ፥ ምንም እንኩዋን የበርካታ ዜጎች ሕይወት እንደ ቅጠል ካለፈቃዳቸው እየረገፈ ቢሆንም፥ ደረጃ በደረጃ በተግባር ለውጥ እያሳየ ነው። ከኮሎኒያሊስቶቹ ዘመን ጀምሮ ምሥራቅ አፍሪካን ያምሳል ይባል የነበረው የዖጋዴን አውራጃ፥ በአስተዋይና ቅን ኢትዮጵያዊ እጅ አርፎ በማይታመን ደረጃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሞት ቀጠናነት ወደ ሕይወትና ተስፋ ተምሳሌነት ተቀይሮዋል። ክቡር ፕሬዝደንት ሙዝጠፋ ኡመር በቅርቡ በአማራ ክልል በሚያደርጉት ጉብኝት፥ ከጃዋር በተቃራኒው የኢትዮጵያን አንድነት አስፈላጊነትን ለአማራ ወጣት ሲያስተምሩ፥ አንገቴን የሚያስደፋኝ ቢሆንም አላህ ኢትዮጵያን ምን ያህል እንደሚወዳት እያሳየኝ ልቤን በደስታ ያሞቀዋል። የጋምቤላም ክልል ቀጣይ እንደሆነ ምልክት ይታያል። አፋርና ቤኒሻንጉልም ሰላማቸውና መረጋጋታቸው መቼ ነው ብሎ መናገር ቢያቅትም፥ ሩቅ እንደማይሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ግን እስከዛው የሚከፈለው የዜጎች ደምን ማሰብ ይጎመዝዛል። የትግራይ ክልል በሩን ዘግቶ በራሱ ዓለም ውስጥ (confederation) እየኖረ ያለ ይመስላል። ይህን ሁኔታ መታገስ ባልከበደ – ግን የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ፥ ያፈናቀለ፥ ያቆሰለ ሴራ ማውጠንጠኛ ስፍራ (launching pad) በመሆኑ ችግሩ ከቁርበቴ ልማከርን ጊዜ የሚሰጥ አይደለም።

ጠቅላይ ሚ\ሩ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ መሪነት ካባና ክብር ሳያስኮፍሳቸው፥ የግል ስብዕና (ego) ሳይወጥራቸው፥ ሳይጋበዙ ያለ አሸማጋይ  ወደ እብሪተኛው ኢሳይያስ አገር ዝም ብለው ተጉዘው የቀድሞው ኢትዮጵያ ገዢዎች ያስቡት እንደነበረው በመዋረድ ፋንታ፥ የሕዝብን ፍቅርና ከበሬታን አግኝተውበታል። ጊዜው ይዘግይ እንጂ የኖቤል ሽልማት በእጃቸው መግባቱ አይቀርም። እሳቸው የኖቤል ሽልማት ሲያገኙ ኢትዮጵያም ወደ አክሱም ዘመነ መንግሥት ደርጃ ከፍ ትላለች። እኔም የቀጣሪዎቼ አሜሪካውያን ቀጣሪ ወደ መሆን ከፍ እላለሁ። ያርግላቸው።  የሰላምና የዕርቅ ጥሪያቸው የባለጌዎቹን የህወሀት መሪዎችን እብሪት ማሙዋዋሸሽ ግን ተስኖታል። ጠቅላይ ሚ\ሩና ጉዋዶቻቸው እየሠሩ ያሉትን ሠርተው ሲጨርሱ፥ አገር አይፈርሥም የሚለውን እምነታቸውን (conviction) ወደተግባር ሲቀይሩ ግጭት መፈጠሩ አይቀርም የሚል ፍራቻ ያድርብኛል። በሌላ ጊዜ ዳተኛ መስሎ የሚታየው ኢትዮጵያዊ ሁሉ፥ አገርህ ተደፈርች በተባለ ጊዜ ሞትን እየናቀ በሚንቀለቀል እሣት ውስጥ እራሱን ለመጨመር ሁለት ጊዜ የማያስብ መሆኑን፥ ከቅርቡ ጊዜ የባድመ ግጭት የተማርነው እውነት ነው። ጠቅላዩ ሌላ አማራጭ ሲጠፋቸው ይህን ጥሪ ማድረጋቸው አይቀርም። ጥሪያቸውም ሰፊ ጆሮ ማግኘቱም አይቀርም። የኢትዮጵያ አንድነት መጠበቁም አይቀርም። ግን ግጭቱና የደም መፋሰሱ እንዳይከሰት፥ ከወዲሁ ህወሀትን የሚመክር ሽማግሌ እንዴት ጠፋ? ስለ ሽምግልና ሳስብ ፕሮፌሠር ኤፍሬም፥ ሻለቃ ኃይሌና ፓስተር ዳንዔል በምናቤ ውልብ አሉ። ለአዲስ ሽምግልና ከጅያቸው አይደለም። ኧረ ምን በወጣኝ። ሽምግልናን ገድለው የቀበሩት እነሱ ይሆኑ የሚል ጥያቄ ብልጭ ብሎብኝ እንጂ። ለትውልድ የተረፈ ሸፍጥ!

መለስ በምርጫ  1997 ማግስት ከገባበት አጣብቂኝ ለመውጣት፥ ሰማይ ቢወድቅ እንኩዋን ከማድረግ ሊቆጠብ የማይችላቸው ሁለት ጉዳዮች ነበሩ። እነዚህም የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ግዛትን መውረርና የቅንጅት መሪዎችን መፍታት። እነዚህ ጉዳዮች መፈፀም የነበረባቸው የመለስ ታላቅነት የበለጠ ከፍ ማለት እንደተጠበቀ ሆኖ ነበር። የአሜሪካ አሽከርነቱን ለመሸፈን የሌሎች ክብር መዋረድ የግድ ነበር። ለዚህም ተዋናይች አስፈለጉ። ልደቱ አያሌው የሶማሊያን መወረር አስፈላጊነት ሽንጡን ይዞ ሲከራከር፥  የቅንጅት መሪዎችን ለማስፈታት ፕሮፌሠር ኤፍሬም፥ የሩጫውን ንጉሥ ሻለቃ ኃይሌንና ፓስተር ዳንዔልን አስከትለው ከተፍ አሉ ወይም እንዲሉ ተደረጉ። የሶማሊያ መወረር የዛሬው ጉዳያችን ስላልሆነ በሽምግልናው ላይ እናተኩር። ዶር ዓቢይ በዲሲ ምሁራንን ባነጋገሩበት አዳራሽ ፕሮፌሠር ዔፍሬምን አይቻቸው ነበር። የአገሪቱን ታላቅ ችግር የፈታ ሽማግሌን ክብር የተጎናፀፉ አልነበሩም። በጉዋሮ በር ሹክክ ብለው ሲገቡ እጅ የነሳቸውም ሆነ ኖር ያላቸው ሰው አልነበረም። ሁሌም እንደሚደርቡዋት ነጠላቸው፥ ነጠላ ነበሩ። ሲድ (SEED) የተባለ ማኅበር ሽልማት የሰጣቸው ይመስለኛል። ድፍረት አግኝቶ እንደገና ካሰበበት ሽልማቱን መልሱ ማለት አለበት ብዬ አስባለሁ። አለዛ ወደፊት በሚሰጠው ሽልማት ተሸላሚዎቹ እንዳይኮሩ ያደርጋቸዋል። ያሳሰበኝ የእሳቸው ጉዳይ አይደለም። በአሁኑ ወቅት አብዝተን የምንፈልገውን ሽምግልና ገድሎ በመቅበር እጃቸው ይኖርበት ይሆን የሚል ጉጉት ያዘኝና የሰጡዋቸውን ቃለመጠይቆች መመልከት ጀመርኩ።

ከመለስ ሞት በሁዋላ ከተፈራ ገዳሙ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አዳመጥኩት። የመለስ አጭበርባሪነት (የሞተን መውቀስ ነውር መሆኑን አጥቼ አይደለም። በኢትዮጵያ ክፉ የዋለባትን ይቅር ማለት ከባድ ነው። ግራዝያኒን ከሞተም በሁዋላ ይቅር አላልነውምና አንባቢ ችግሬን ይረዳል ብዬ አስባለሁ።) ለውጭ አገር ሰዎች በቀላሉ ባይገለጥ አይገርመኝም። ካለፈም በሁዋላ በረከት ስምዖን ላይ የሚታየውን የመለስ ጣዖትነት፥ ትምህርት በጠገቡት፥ ብዙ የከተማ ነዋሪነት ልምድ ባለቸው፥ ያውም አይሁዱ ፕሮፌሠር ዔፍሬም ላይ ስመለከት አጃኢብ ብያለሁ።

ተፈራ ገዳሙ እንዴት ተዋወቃችሁ? ብሎ ላነሳላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ህወሀት ሥልጣን ላይ ሳይወጣ በፊት በ1977 ድርቅ ወቅት ለበርካታ ጉዳዩ ያገባቸዋል ብለው ላመኑት (በወቅቱ ሥልጣን ላይ ለነበሩም ላልነበሩም ወገኖች) የሕዝብን ከረሀብ እንታደግ ጥያቄ ለፃፉት ደብዳቤ መልስ ያገኙት ከአቶ መለስ ብቻ እንደነበር በማንሳት አቶ መለስ ታላቅ ኢትዮጵያዊ እንደነበሩ ይገልፃሉ። በወቅቱ በበረሀ ውስጥ ሌሊት ከአቶ መለስ ጎን የሚተኙት፥ ቀን ከአቶ መለስ ትዕዛዝን ይቀበሉ የነበሩት፥ አቶ ገብረመድኅን ደግሞ አቶ መለስ አሽዋ የተሞላን ጆንያ ማሽላ እያሉ የሚሸጡ ተራ ቁጭ በሉ እንደነበሩ ከሚያቀርቡት ገለፃ ጋር የሚጋጭ ሀሳብ ያቀርባሉ።

“መለስን እንዴት ይገልፁዋቸዋል?” ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ እጅግ በጣም ትሁት ሰው እንደነበር ያወሳሉ። ትሁት የሚለው ቃል በጣም አጠቃላይ በመሆኑ ቁልጭ አድርገው እንዲገልፁት ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ የሚከተለውን ምሳሌ ሰጡ። ወሮ ብርቱካን አሉ (ወ\ት አለማለታቸው ቅን ስህተት ነው ብለን እንለፈው) በታሰረችበት ወቅት የልጅዋ፥ የእናትዋና የራስዋም ስቃይ እንቅልፍ ስለነሳቸው እንዲፈታት የሚለምን ደብዳቤ ለአቶ መለስ ይፅፉለታል። መለስም ከለሊቱ 9 ሠዓት ላይ (እሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ በኢትዮጵያ ከቀኑ 5 ሠዐት የሚሆን ይመስለኛል። የመልዕክት ልውውጡም በemail ይመስለኛል።) በጉዳዩ እንቅልፍ በማጣታቸው እጅግ እንደሚያዝን ገልጾ ሕግና ደንብ ለማክበር ሲባል ወሮ ብርቱካንን እንደማይፈታ እንደገለፀላቸው ይጠቅሳሉ። ትሁት መሆኑ ምኑ ላይ እንደሆነ ሲጠይቃቸው፥ ለአንድ ተራ ዜጋ ጥያቄ ጊዜ ወስዶ መልስ መስጠቱ የመለስን ታላቅነት እንደሚመሰክር ትንታኔ ይሰጣሉ። አፌን ያዝኩኝ። ሌላ ምን ማድረግ እችላለሁ? የመለስን ታላቅነት Moral Man and Immoral Society በሚል ርዕስ ‎Reinhold Niebuhr የሚባል ፀሀፊ የፃፈውን መፅሀፍ በመጥቀስ መለስን ሰማይ ሰቅለው የኢትዮጵያን ሕዝብ በአፍጢሙ ይደፉታል። በቅርቡ ቅንነቱን በእጅጉ የምጠራጠረውን ያሬድ ጥበቡ “ውነት አቢይን እንመጥነዋለን ወይ?” ሲል ካቀረበልን ጥያቄ የሚመስል ሀሳብ ያቀርባሉ። መለስ በምን ሊታወስ እንደሚገባ ላነሳላቸው ጥያቄ የሰላምና የዕርቅ አርበኛ እንደነበር ሲገልፁ፥ ይሄ ሽማግሌ አብዶዋል ወይስ የሚያወራው ስለ አቢይ ነው ያስብላል። ዓለም ስላወቀው የአፍሪካ ቀንድ በጥባጭ የሚያወሩ አይመስልም። ፕሮፌሰር ዔፍሬም፥ ክቡር ዶ\ር ሩዋጭ ኃይሌ ገ\ሥላሤ፥ ፓስተር ዳንኤል ምንም እንኩዋን በየማዕረጋቸው መጨረሽ “አር” ቢኖራቸውም የመለስን ማዕረግ ከፍ ሲያደርጉ የራሳቸውን ክብር አውርደው ፈጥፍጠዋል። ይሄ እኛን አያሳስበንም። የሚያሳስበን እነዚህ ሰዎች ገድለው የቀበሩትን ሽምግልና እንደገና አደልበን እንዴት የአገራችንን ችግር በመፍታት የለውጥ ኃይሉን እንደግፍ የሚለው ጥያቄ ነው።

በቅርቡ አባይ ፀሀዬና ክንፈ ዳኘው በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ ክህደት የተፈጥሮ ባህርያቸው በመሆኑ ግልፅ ሆኖ መታየቱ ባይቀርም፥` ዕብሪታቸው መተንፈሱም ጎልቶ ይታያል። ጎበዝና ጠንካራ ሽማግሌ ቢገኝ ከተያያዙት የጥፋት መንገድ ሊታቀቡ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ህወሀት በታሪክ ክህደቱ የጥበብ መጀመሪያ አድርጎ የወሰደው ከትግራይ ሽማግሌዎችንና ታሪክ አዋቂዎችን ሰብስቦ ማጥፋት ነበር። ከአገር ውጪ ያላችሁ የትግራይ ተወላጅ ምሁራንና ገለልተኛ ነን ብላችሁ የምታምኑ አዋቂዎች እባካችሁ የሚፈሰው የድሃ ደምና ዕምባ ነገ ይወቅሳችሁዋልና ተነሱ። ለሚፈሰው ደም ሁሉ የዓቢይን መንግሥት መውቀስ የትም አያደርስም። ማንንም አይጠቅምም። ህወሀትን ከጥፋት መንገዱ ለማቆም የምትችሉ ሁሉ የማንንም ጥሪ ሳትጠብቁ በጉዳዩ ግቡበት። በንግግርና በይቅርታ የሚያምን መንግሥት ተገኝቶዋል። እንጠቀምበት! ዐዋቂና ታዋቂዎች የሆናችሁ እባካችሁ ተነሱና መቀሌ የመሸጉ ጥጋባኞችን ከፌደራሉ መንግሥት አደራድሩ። በዚህ ሁኔታ መቀጠል አይቻልም።የትግራይ ሕዝብም የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ካገኘው ነፃነት ይቁዋደስ። ሰው ከነፃነቱ በላይ በዚህች ዓለም ላይ ምን ሀብት አለው!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቅ!