ለክቡር የኢፌዴሪ ጠ/ሚኒስትር ዶር አብይ አህመድ

ከስምንት ወራት ወዲህ የጠ/ሚኒስትርነቱን ቦታ ከያዙ ጀምሮ የወሰዷቸውን ናእርምጃዎች በአድናቆት እንከታተላለን፣እንደግፋለንም። ባለፉት መሪዎች ያልተለመደ እንደዚህ ሕዝብ መካከል ተገኝቶ፣ከሕዝብ ጋር ለመወያዬት የሚያደርጉት ቀና ፍላጎት በመሪና በተመሪ መካከል የነበረውን የእሩቅ ግንኙነት እንደሰበረው ማስረጃ ነው።በመቀራረብና በግልጽነት የአገርን ጉዳይ አንስቶ መወያዬቱ ለይስሙላና ለዝና ሳይሆን የሚቀርቡት አስተያዬቶች ቦታና ትርጉም ይኖራቸዋል ብለን እናምናለን።

  ኢትዮጵያ አገራችን ለአያሌ ዘመናት ስርዓት መሥርታ ስትተዳደር የቆዬች አገር ነች።የቀድሞ መሪዎቿ የተመሩበት የአስተዳደር ስልት አገራዊ አንድነትን፣የሕዝቧን ክብርና ትስስር በሚያጠናክረው የክፍላተሃገር አወቃቀር ዘዴ ነበር። የክፍላተሃገር አወቃቀሩ መልካም ሆኖ ሳለ አስተዳደሩ ሕዝባዊ ተሳትፎ ስላልነበረውና በዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ አሠራር ስላልተቀናጀ  ሊሠጥ የሚችለውን ጥቅም ለመስጠት አልቻለም ነበር።

ይህ ማለት ግን የክፍላተሃገር አወቃቀር ጽንሰሃሳብ መጥፎ ነው ማለት አይደለም።አንድ መድሃኒት በአግባቡ ካልተጠቀሙበት ጉዳት እንደሚያመጣ ሁሉ የነበረውም የክፍላተ ሃገር አወቃቀር ምንም እንኳን ዜጋ ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖርና ሃብት የማፍራት፣ ከወደደው ጋር ትዳር መስርቶ የመኖር መብት የተረጋገጠበት ቢሆንም ሕዝብ  በአገሩ ጉዳይ ላይ ወሳኝና ባለቤት አልነበረም።ያም በመሆኑ ከሃያ ስምንት ዓመት ወዲህ በኢሕአዴግ  ለሰፈነው የጎሳ ፖለቲካና የክልል አስተዳደር መነሻ ምክንያት ሆኗል።

ላለፉት 28 ዓመታት በኢሕአዴግ የሰፈነው የጎሳ ፖለቲካና የክልል አስተዳደር በየቦታው ለተከሰቱት የሕዝብ መፈናቀል፣ስደት፣እስራትና ግድያ፣ለእርስ በርስ ግጭትና  ለአገራዊ አንድነት ስጋት ምክንያት ሆኗል።የተፈጠሩት ክልሎች  ከታሪካዊ መልክዓ-ምድር ገደባቸው አልፈው የሌላውን ክ/ሃገር ለም መሬት በመንጠቅ ኗሪው ሕዝብ እንዲፈናቀልና ግጭት እንዲነሳ አድርጓል።ይህንንም ወንጀል ሕዝቡ አጥብቆ መቃወም ብቻ ሳይሆን በመታገል ላይ ነው። እርሰዎንና ሌሎቹንም የሥርዓቱ አባላት ለለውጥ የገፋፋው የሰፈነው ስርዓት ያመጣው ችግር ነው ብለን እናምናለን።ጎሰኝነትና የጎሳ ፖለቲካ አገር ያፈርሳል፣ሕዝብ ያጫርሳል።ለሕብረተሰብ የካንሰር በሽታ ነው።ከዚያም በላይ ጸረ ሰብአዊ ለሆነው ፋሽዝም መፈልፈያ ቀፎ ወይም ማህጸን ነው።ጎሰኝነትንና የጎሳን ፖለቲካ በለዘብተኛ መነጽር በማዬት በዴሞክራሲና በመደመር ሂሳብ መንከባከብ ስህተት ከመሆኑም በላይ ለሚያደርሰው ጥፋት ተባባሪ መሆን ነው።   

ለለውጥ የተነሳ ትውልድና ዜጋ ይህንን እውነታ መቀበልና አገራችንና ሕዝቡ ከገቡበት መቀመቅ ለማውጣት የኢሕአዴግን የጎሳ ፖለቲካና የክልል አስተዳደር አሶግዶ እንደሰለጠነው ዓለም በዴሞክራሲ ስርዓት ለሚመሠረተው ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ  የክፍላተሃገር አስተዳደርና ፌዴራሊዝም ስርዓት ድጋፉፋቸውን እንዲሰጡ የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት ጥሪ ያደርጋል።

 የክፍላተሃገር አወቃቀርንና አስተዳደርን አሁን በስልጣኔ የገሰገሱት አገራትም ማለትም የአሜሪካ፣የኔዘርላንድ፣የጀርመንም ሆኑ የእስካንዲኔቪያና ሌሎቹም አገሮች የሚገለገሉበት የአስተዳደር ስልት ነው። የክፍላተሃገር አስተዳደር መኖር ሕዝቡ በቅርበት መሪዎቹን እንዲከታተልና በጋራ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን፣ሙስናና ስርዓተ-አልበኝነት እንዳያንሰራራ ቁጥጥር ከማድረጉም በላይ በፌዴራል  ትስስር  ሁሉም የማእከላዊ መንግሥት አካል በመሆን ጠንካራ አገራዊ አንድነት  እንዲኖር ያደርጋል።

የክፍላተሃገር አስተዳደር ሌላው ጥቅሙ የመካከለኛውን መንግሥት የሥራ ጫና መቀነስና ለሚቀርበው የሕዝብ ጥያቄ ፈጣን መልስ ለመስጠትና ችግር ቢከሰት በጊዜው ለመፍታት ይረዳል።የከባቢውን ሰላምና ደህንነት፣ልማትና እድገትም በቅርበት ይቆጣጠራል፣ ያረጋግጣል።   

በዚህ የክፍላተሃገር አወቃቀር ማንኛውም ዜጋ ከፈለገበት ክፍለሃገር የመኖር፣የመሥራትና ሃብት የማፍራት መብቱ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በሚኖርበት ቀበሌ፣ወረዳ፣አውራጃና ክፍለሃገር ብሎም በአገር አቀፉ ሁለገብ ጉዳይ፣ የፖለቲካ፣የኤኮኖሚና፣የማህበረሰብ መስኮች ላይ ተሳታፊና ወሳኝ ይሆናል። ይመርጣል፣ይመረጣል። የሚናገረው ቋንቋ፣የጎሳ ማንነቱና የሚከተለው ሃይማኖት መለኪያ አይሆንም።

ክቡር ጠ/ሚኒስትር!

 ከሃያ ስምንት ዓመት በፊት የተወለደው ትውልድ እርሰዎን ጨምሮ የዚሁ የክፍላተሃገር አወቃቀር ፍሬ መሆኑ አይካድም።ስለሆነም ይብዛም ይነስም የነበረውን ጥቅም ይረዳዋል ብለን እናምናለን።ዜጋ መጤና ሰፋሪ፣ባዳና እንግዳ፣ክርስቲያን ወይም እስላም እዬተባለ የማይፈናቀልበትና የማይሸማቀቅበት፣በኢትዮጵያዊነቱ እንጂ የጎሳ ሰሌዳ ለጥፎ የማይታወቅበት ጊዜ ነበር።

አሁን የሰፈነው ኢሰብአዊና ዃላ ቀር የሆነው የጎሳ ፖለቲካና የዘመነመሳፍንት የክልል አስተዳደር በዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ የክፍላተሃገር አስተዳደር እንዲለወጥ ተደራጅቶ የሚንቀሳቀሰው የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ ያደርጋል።

ክቡር ጠ/ሚኒስትር!

ከሶስት ወራት በፊት በአሜሪካን አገር ባደረጉት ተመሳሳይ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የክፍላተሃገር ህብረት ተወካዮች ተገኝተው ተመሳሳይ ጥያቄ ያዘለ ደብዳቤ እንዳቀረቡ አይዘነጋም።አሁንም የዚያ አካል የሆነው የአውሮፓው ቅርንጫፍ ከዚህ ደብዳቤ ጋር በማያያዝ የሚከተለውን ጥያቄ ያቀርባል። ለለውጥ ተነስቻለሁ የሚለው እርሰዎ የሚመሩት መንግሥት የክፍላተሃገርን አወቃቀር እንዴት ያዬዋል?ህብረቱ  በአገር ቤት ገብቶ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚያስፈልገውን እርዳታና ድጋፍ ለማበርከት ፍቃደኛስ ነወይ?  

ጎሰኝነትና የጎሳ ፖለቲካ፣ከፋፋይ የሆነው የክልል አስተዳደር ከአገራችን ይወገድ!

ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ ተከብሮ የሚኖርበት ዴሞክራሲያዊ የክፍላተሃገር አስተዳደር ይመስረት!!

ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!!

የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት የአውሮፓ ቅርንጫፍ

ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓም(31-10-2018)

ethiopianhibret@gmail.com