ቀን፡ 26 ኖቬምበር 2018

                                                                                ቁጥር፡ GCLTR/007/18

ዓለም ዓቀፍ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር ጣና ሀይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ከተቋቋምበት ጊዜ አንስቶ የተቀናጀ ተግባር ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ማህበሩ ከሚሰጣቸው ድጋፎች ዋና ዋናዎቹ፡- የአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ አረሙን ለመቆጣጠር የሚያግዙ መሳሪያዎችን መለገስ፤ እንዲሁም የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ የቁጥጥርና ክትትል ድጋፍ መስጠት ይጠቀሳሉ።

ማህበሩ ቀደም ሲል ከለገሰው የአረም ማስወገጃ ማሽን በተጨማሪ በተለያዩ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ከተሞች ያሰባሰበውን ገንዘብ በመጠቀም ሁለት H-9 905 የተሰኙ እያንዳንዳቸው 75 የፈረስ ጉልበት ያላቸውና በአንድ ጊዜ 26.2 ኪውቢክ ሜትር አረም ማጨድ የሚችሉ ማሽኖችን ከነሙሉ መለዋወጫቸው ካናዳ ከሚገኘው አኳማሪን ከተሰኘ ኩባንያ ግዥ ፈጽሟል። ማሽኖቹ በድምሩ 359,490 የአሜሪካን ዶላር (ወይም 10 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር) ወጭ ተደርጎባቸዋል። የማህበሩ የሳይንስ ኮሚቴ እንዳረጋገጠው ማሽኖቹ ከፍተኛ የማጨድ ጉልበት ያላቸውና በአሁኑ ወቅት እየተደረገ ያለውን የአንቦጭ ማስወገድ ርብርብ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያግዘውም ይታመናል። አዲሶቹ ማሽኖች ከዚህ በፊት ከተገዛው H5-200 ማጨጃ ማሽን ጋር ሲነጻጸሩ እያንዳንዳቸው በአምስት እጥፍ አረም የማስወገድና የመሸከም አቅም እንዳላቸው የማሽኖቹ መመዘኛ ያሳያል፡፡

machines

ማሽኖቹን ለመግዛት የዋለው ገንዘብ የተገኘው በዋሽንግቶን ዲሲ፤ ዳላስ፤ ቺካጎና ለንደን በተደረጉ የገቢ ማሰባሰቢያ መረሃ ግብሮች ሲሆን ማህበሩ እነዚህን ፕሮግራሞች ላስተባበሩ እና ለተሳተፉ የጣና ሀይቅ ወዳጆችን እና ቤተሰቦች በሙሉ ከፍ ያለ ምስጋናውን ማቅረብ ይወዳል፡፡ በተጨማሪም በዋሺንግተን ዲሲ የኢት/ኦ/ተ/ ደብረገነት መድሃኒያለም ቤተክርስቲያንም 70,000 /ሰባ ሽህ/ የአሜሪካ ዶላር ለማህበሩ በመለገስ ጣናን ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት እንደምተደግፍ በተግባር አሳይታለች።

የማሽን ግዥው ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በገንዘብ በጉልበትና በሃሳብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስታደርጉ ለቆያችሁ የጣና ወዳጆች በሙሉ ምስጋናችንን እያቀረብን በቀጣይም ጣናን ለመታደግ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንደማይለየን ባለሙሉ ተስፋ ነን።

ደረሰኝኙን ከዚህ በታች ይመልከቱ

receipt

ያለ ምንም ልዩነት ለጣና ጤንነት!!

እሸቴ ምስጋና የዓለማቀፉ ጣናን መልሶ ማቋቋም ማህበር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር