ክቡር አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ ሌንጮ ለታ ፓርቲያቸውን ለማዋሃድ ተስማሙ

አባይ ሚዲያ ዜና

ክቡር ርእስ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ ሌንጮ ለታ ድርጅቶቻቸውን በማዋኋድ ለመስራት ያስችላል ያሉትን የስምምነት ሰነድ በይፋ አጸደቁ።

አቶ ለማ መገርሳ በምክትል ሊቀመንበርነት በሚመሩት በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና አቶ ሌንጮ ለታ በሊቀ መንበርነት በሚመሩት በኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ድርጅቶች መካከል የተደረሰው የመግባቢያ ሰነድ ሁለቱ ድርጅቶች ተዋህደው የሚሰሩበትን መንገድ ቀያሽ እንደሆነ ተዘግቧል።

የውህደት ጥያቄው ከኦሮሞ ማህበረሰብ የመጣ እንደሆነ የጠቀሱት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ ሁለቱ ድርጅቶች ሲያራምዱ የነበሩት ፕሮግራሞች ተመሳሳይ ስለሆኑ በጋራ ለመስራት ውሳኔ ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

የዛሬውን የውህደት መግባቢያ ሰነድ መፈራረምን ተከትሎ በቀጣይ ሁለቱ ፓርቲዎች በሚሰሩበት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ኮሚቴ ተዋቅሮ ውይይት እንደሚደረግ አቶ አዲሱ በተጨማሪ ገልጸዋል።

በአቶ ሌንጮ ለታ ከሚመራው  የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ጋራ በመዋሃድ ለመስራት ስምምነት ላይ የደረሰው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በቀጣይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተመሳሳይ ሂደት ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ (አዲሃን) በመዋኋድ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መድረሳቸው ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል።