የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ የቤንሻንጉል ጉምዝ አመራሮችን በቁጥጥር ስር አዋለ

አባይ ሚዲያ ዜና 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተዘገበ።

በቁጥጥር የዋሉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች በክልሉ በተፈጠሩ ግጭቶች በመጠርጠራቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ባሳለፍነው ሰኔ 17 ቀን 2010 ዓም በአሶሳ ከተፈጠረው ግጭት በስተጀርባ እነዚህ ተጠርጣሪዎቹ እንዳሉበት ፖሊስ በተጨማሪ አሳውቋል።

የቀድሞ አሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባን ጨምሮ  በቁጥጥር ስር የዋሉት የቤኒሻንጉል አመራሮች በኦሮሚያ ክልልም በተፈጠሩት ግጭቶችም እጃቸው እንዳለበት የፌደራል ፖሊስ ገልጿል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ እና በተጎራባች የኦሮሚያ አከባቢዎች ተፈጥረው በነበሩት ግጭቶች የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) ስሙ በተደጋጋሚ ቢነሳም ኦነግ በበኩሉ ክሱ ከእውነት የራቀ ነው በማለት ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል። በአከባቢው በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ሺ ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለው በስደት እንደሚገኙ ተዘግቧል።

አምስቱን የቤንሻንጉል ጉምዝ ከፍተኛ እንዲሁም መካከለኛ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ያዋለው የፌዴራል ፖሊስ ግብረ ሃይል ሌሎች ከግጭት ጋር ንኪኪ አላቸው ተብለው በሚጠረጠሩ የክልሉ አመራሮች ላይ ዘመቻው እንደሚቀጥል አሳውቋል።