አባይ ሚዲያ ዜና 

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ በአዲስ አበባ በሚገኘው የራስ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር መወያየቱ ተገለጸ። 

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጨምሮ ከፍተኛ የንቅናቄው አመራሮች የተካተቱበት በመዲናዋ አዲስ አበባ የተደረገው ውይይት  በዋናነት ንቅናቄውን ወደ ፓርቲነት የማሸጋገር ሂደት ላይ ያተኮረ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዲሞክራሲ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም በህዳር 30 ቀን 2011 ዓ.ም በራስ ሆቴል  አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ ላይ ስለ ወደፊቱ የድርጅታቸው ቅርጽ እና ይዘት ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል። 

በዚህ በዋና ከተማዋ በአዲስ አበባ በተደረገው ውይይት ላይ አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ወደ ፊት በፓርቲነት ሲንቀሳቀስ  በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ራእይን እንደሚከተል አመራሮቹ በአጽንኦት ገልጸዋል። 

ንቅናቄው ወደ ፓርቲነት በሚለወጥበት ጊዜ ማህበራዊ ፍትህን በኢትዮጵያ ምድር ላይ  ለማስፈን በዋናነት አላማው አድርጎ እንደሚንቀሳቀስም የድርጅቱ አመራሮች አሳውቀዋል። 

ንቅናቄውን  ጠንካራ እና ታማኝ ፓርቲ ለማድረግ  በዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከወረዳዎች ጀምሮ አመራሮችን የመምረጥ እንቅስቃሴ እንደሚደረግ የንቅናቄው ከፍተኛ አመራሮች በስብሰባው አብራርተዋል።

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ለመወዳደር ባቀደባቸው ሁሉም ወረዳዎች በማህበረሰቡ እምነት የሚጣልባቸውን እንዲሁም የአመራር ብቃት ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደሚመርጥ ለመረዳት ተችሏል። ይህ ከወረዳ ጀምሮ ብቃት ያላቸውን እንዲሁም በህብረተሰቡ እምነት የሚጣልባቸውን ኢትዮጵያውያንን ለንቅናቄው አመራርነት የመምረጥ ሂደት ወደ ፊት የሚደራጀውን ፓርቲ ጠንካራ እንደሚያደርገው ተብራርቷል። 

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የውህደት አሊያም የትብብር ስራዎች ለማከናወን የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ከታች ከወረዳ ጀምሮ ባሉ መዋቅሮቹ እንጂ በማእከላዊ ደረጃ ብቻ እንደማይከናውንም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ጊዜያዊ  አደራጅ ግብረ ኃይል የነደፈውን  የሁለት ወር የስራ እቅድ አቅርቦ በስብሰባው ላይ  ውይይት ተደርጎበታል። 

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ እየታየ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ ወረዳዎች ማውረድ በሚቻልበት ዘዴዎች ላይም ምክክር ተደርጓል። 

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዲሞክራሲ ንቅናቄ እያደረገ ያለውን የጊዜያዊ አደረጃጀት ሥራ አጠናቅቆ ወደ ፓርቲ ምስረታ ምእራፍ በሚሸጋገርበት መንገድ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በቀጣይ ንቅናቄው መሰራት በሚገባቸው ርእሶች ላይ ከስብሰባው ተካፋዮች ለቀረቡ ጥያቄዎች በድርጅቱ አመራሮች ምላሾች ተሰጥተዋል።