ለህወሀት በአፍጢሙ ውድቀትና አሁን ላለንበት ለውጥ መምጣት ቴዲና ሀጫሉ የፋና ወጊነትን ሚና ተጫውተዋል።

የ1997 ምርጭ በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ወደሁዋላ መመለስ የማይቻልን ለውጥ አስርፆ አልፎዋል። የቅንጅት ምሁራን ካፈሰሱት ምርጥ ዲስኩሮች በእጥፉ የቴዲ አፍሮ ሁለት ስንኞች የህዝብ የሥልጣንና የአገር ባለቤትነትን አስተምረው ቀስቅሰውና አስርፀው አልፈዋል።
…..ለለውጥ ያጎፈረው ሥልጣን ላይ ሲወጣ፥
እንዳምናው ባለ ቀን ያምናውን ከቀጣ፥
አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?….
የሚለው ስንኝ ሕዝብ ነፃነቱን ሳያገኝ እንቅልፍ እንዳያሸልብ ረብሸውታል። ለነዚህ ስንኞች ብቻ ቴዲ ምንም እንኩዋን አሁን ቢኮራበትም በወቅቱ ብዙ ፍዳ አይቶባቸዋል። አንዲት እናት ልጅ ለማግኘት የምትከፍለውን የምጥ መከራ ያህል ቴዲም ዋጋውን ከፍሎዋልና ይህ ለውጥ የቴዲም ልጅ ነው። በአሁኑ መሪዎች የሚቀነቀነው “ፍቅር ያሸንፋል!” ብሂልም የቴዲ ትምህርት ነው። እነዚህ የቴዲ ትምህርትና ቅስቀሳዎችን በቅጡ ያደመጡት ለማና አቢይ አዲስ ንጉሥ ላለመሆንና በፍቅር ለማሸነፍ ሲታትሩ፥ ሌቦችና ግፈኞቹ አምልጠው አሁን አገሪቱን የምትገኝበት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንድትዘፈቅ ሆኖዋል። የቴዲ ትግል ለውጡን ያመጣውን ያህል መሪውቹን ያስተማረው የፍቅር ቃላትም አዘናግተዋቸው ጅቦቹ ማጥቂያ መደላድል እንዲያገኙ ረድቶዋል።

ሀጫሉ በወገኖቹ ላይ የሚፈፀመው ሰቆቃ አንገሽግሾት ራሡን እንቅልፍ ነስቶት ለሎችንም እንቅልፍ ሲነሣ ቆይቶዋል። ሲታሰር፥ ሲደበደብ፥ ሲፈታ። መልሶ ሲቀሰቅስ፥ ሲታሰር፥ ሲደበደብ ሲፈታ ኖሮዋል። ጦሱ በሱ ሳያበቃ በዘፈኑ የአሁኑን መሪዎች ህሊና እየሸነቆጠ ለዛሬው ድላቸውና ለህወሀት በቁሙ መጠውለግ ትግሉን ጠንስሶዋል። በተለይ በሚሊኒየም አዳራሽ የአሁኑን መሪዎች ፊትለፊቱ አስቀምጦ እያቅራራ ህሊናቸውን የፈተነበትን አጋጣሚ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነት ትግል ታሪክ ሲዘክረው የሚኖር ክስተት ነው።

እነዚህ ከያኒዎች የለውጡን ኃይሎች በለኮሱት እሳት ውስጥ ከከተቱዋቸው በሁዋላ ገሸሽ ያሉ ይመስላል። አሁን ያለውን ረብሻና ውጥንቅጥ በማርገብ ሊጫወቱት የሚገባቸውን ሚና ልብ ማለት ተስኖዋቸዋል። ቆስቁሰው ማንከባለል ያስጀመሩትን ፈጣን ካሚዮን ለማርገብ ልጉዋሙ በእጃቸው መሆኑን ዘንግተውታል ወይም ግድ አልሰጣቸውም። ሙዚቃ ምን ኃይል እንዳለው አይተን ከታዘብነው በላይ ፕላቶ የሚከተለውን ብሎዋል።

“Music is a moral law. It gives a soul to the universe, wings to the mind, flight to the imagination, a charm to sadness, gaiety and life to everything. It is the essence of order, and leads to all that is good, just, and beautiful, of which it is the invisible, but nevertheless, dazzling, passionate, and eternal form”

ከአንድ ሺህ የአቢይ ዲስኩሮች በበለጠ ቴዲና ሀጫሉ በጣት የሚቆጠሩ ኮንሰርቶችን በአገሪቱ ዙሪያ ቢያደርጉ ሰላምን ያሰፍናሉ። የህወሀትን ጥፍሮች የመቡዋጠጥ አቅም ያመክናሉ። አለዛ የለውጥ ኃይሉ ግድ ሆኖበት ሠይፉን ከነሳ ሌላ ዙር የጥቁር ደም ታሪክ እንዳንገነባ ያስፈራል። ይህ ለቴዲና ሀጫሉ ውዴታ ብቻ ሳይሆን የውዴታ ግዴታም ነው። የአባት አደራ አለባቸው። የኮሩበት የአድዋ ድል በነሱ ዘመን ሊመክን መፍቀድ የለባቸውም። አብረው የሞቱና አብረው የገደሉ ጀግኖች ልጆች ስለምን አብረው መዝፈን ያቅታቸዋል። ዘፈን አገርን ካዳነ ዘፈን ሕዝብን ካወደደ ይህን አለማድረግ ፀጋውን ካከናነባቸው አምላካቸው እንዳያጣላቸው ቢያስቡበት ይሻላል። ወይኔ ለኔ ድምፅ በሰጠኝ ኖሮ!!