የአፋር ክልል አዲስ ርዕሰ መስተዳደር መረጠ

አባይ ሚዲያ ዜና
የአፋር ክልል ምክር ቤት ባካሄደው ጉባኤ ክልሉን በርእሰ መስተዳድርነት እንዲመሩ አቶ አወል አርባን መረጠ።

የክልሉ ምክር ቤቱ በጠራው አስቸኳይ ጉባኤ የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ምክትል ሊቀ መንበር ሆነው በማገልገል የሚገኙትን አቶ አወል አርባን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾሟል።

ከርዕሰ መስተዳደር ሹመት በተጨማሪ ምክር ቤቱ ወይዘሮ አሚና ሴኮን አፈ ጉባኤ ሆነው እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል።

ወ/ሮ ሃዋ ኮሎይታ በምክትል አፈ ጉባኤ የስራ ዘርፍ ተመድበው ክልሉን እንዲያገለግሉ ምክር ቤቱ ባደረገው በዚህ ጉባኤ ሾሟቸዋል።

አዲሱ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ አወል አርባ በጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አስተዳደር እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት ስኬታማ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ለውጡ እንዳይቀለበስ እንዲሁም የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከማህበረሰቡ፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከጎሳ መሪዎች እና ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋርም ምክክር እንደሚደረግ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት አቶ አወል አርባ ገልጸዋል።