ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ሃላፊ ጋር ተወያዩ

አባይ ሚዲያ ዜና

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ልኡካን ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ስለሚያደርገው የልማት ትብብሮች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ተወያየ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራምን በዋና አስተዳዳሪነት የሚያገለግሉትን አቺም ስታየነርን በጽህፈት ቤታቸው በመቀበል ውይይት አድርገዋል።

በአስተዳዳሪው አቺም ስታይነር የሚመራው የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ልኡካን ቡድን ከጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ  ጋር ባደረገው ውይይት ኢትዮጵያ ለልማቷ በሚያስፈልጋት ትብብር ዙሪያ መክሯል።

ዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን የመምራት ሃላፊነትን ከያዙ በኋላ በኢትዮጵያ እየታየ ባለው ለውጥ ዙሪያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አስተዳዳሪ አቺም ስታይነር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የዶ/ር አብይ አስተዳደር በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ለውጥ እንዲመጣ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም አስተዳዳሪው በዚሁ ውይይት ላይ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት የሚያደርገውን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ ትብብሩን እንደሚቀጥል አስተዳዳሪው አቺም ስታይነር አረጋግጠዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በበኩላቸው የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ ሲያደርግ የነበረው ትብብር የሚደነቅ እንደነበረ ተናግረዋል።