ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲሽከረከር በነበረ ሚንባስ ላይ የፈንጂ አደጋ ደረሰ

አባይ ሚዲያ ዜና

በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ በሆነ አከባቢ የተቀበረ ፈንጂ ፈንድቶ የሰው ህይወት መጥፋቱ ተገለጸ።

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሚገኝ አከባቢ ተቀብሮ በፈነዳው ፈንጂ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 10 መድረሱ ተሰምቷል።

ፈንጂው ቶንጎ ጉሬ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ተቀብሮ እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፤ በአከባቢው ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲሽከረከር በነበረ ሚንባስ ላይ ፈንጂው መፈንዳቱ ተዘግቧል።

በሚንባሱ ተሳፍረው ከነበሩት ሰዎች መካከል የአስሩ ህይወት ማለፉ ሲገለጽ ቀሪዎቹ ላይ ጉዳት ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አደጋው የደረሰበት የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ከአሶሳ ወደ ሞኦ ኮሞ ሲጓጓዝ እንደነበረ ለመረዳት ተችሏል።

ፈንጂው ተቀብሮ የነበረበት ቦታ ጠጠራማ መንገድ ላይ እንደሆነ ሲገለጽ፤ አደጋው በደረሰበት ስፍራ የስደተኞች ካምፕ እንደሚገኝ የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ይሁን እንጂ ፈንጂውን በዚህ ስፍራ ላይ ማን እንደቀበረው የሚያትት መግለጫም ሆነ መረጃ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰአት አልተሰጠም።

በፈንጂው የተጎዱ ሰዎች ለህክምና እርዳታ ወደ ቤጊ ሆስፒታል መወሰዳቸው ሲታወቅ፤ የሞቾቹ ቁጥር ግን ሊጨምር እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል።

በአደጋው ህይወታቸውን ባጡ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው እና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።