አባይ ሚዲያ ዜና

በአዲስ አበባ የተጠራው እና በርካታ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ህዝባዊ ውይይት በሜክሲኮ የመብራት ሃይል አዳራሽ ክበብ አዳራሽ ተደረገ።

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ከፍተኛ አመራሮች በዚሁ ህዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ በመገኘት በኢትዮጵያ እየታየ ስለሚገኘው የለውጥ ጉዞ እንዲሁም ስለ ንቅናቄው የወደፊት አቅጣጫ ገለጻ ሰጥተዋል።

ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩበት በነዚህ ጥቂት ወራቶች ውስጥ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ተስፋ ሰጪ የዲሞክራሲ ጎዞ ሳይጨናገፍ በሚቀጥልበት ወቅታዊ አጀናዳዎች ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ከፍተኛ አመራሮች ከተሳታፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

የንቅናቄው ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አዳራሹን ግጥም አድርጎ ለሞላው ታዳሚ ባደረጉት ንግግር በጥቂት ወራቶች ውስጥ በኢትዮጵያ የመጣውን አበረታታች ለውጥ አደጋ ላይ ለመጣል የሚዳርጉ እኩይ እንቅስቃሴዎችን በዘለቄታዊነት ለመግታት ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን እና በዜግነት ላይ የተመረኮዘ ፖለቲካ ዋንኛ ቁልፎች እንደሆኑ አስረድተዋል።

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአገራችን ኢትዮጵያ  ተስፋ ሰጪ ለውጦች እንዳሉ ሁሉ  ለውጡን ለመቀልበስ የሚያስቡ አካላት የሁላችን የሆነችውን አገራችንን ስጋት ውስጥ  እየከተቱ እንደሚገኙም ንቅናቄው እንደሚገነዘብ በዚሁ ስብሰባ ላይ ተገለጿል።

የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ባህሉ እና ቋንቋው ሊጠበቅለት እንደሚገባ  ድርጅታቸው እንደሚያምን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በንግግራቸው በመጠቆም፤ በጋራ ስለምንኖርባት ኢትዮጵያ ግን አጽንኦት ተሰጥቶት ማሰብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የዜግነት ፖለቲካን በማራመድ ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን እንዲሁም ለአገራችን ኢትዮጵያ በቅንነት መስራት ወደፊት በአዲስ መልኩ የሚደራጀው የድርጅታቸው ዋና ግቦች እንደሆኑ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።

ከንቅናቄነት ወደ ፓርቲነት ተቀይሮ ወደ ስራ ስለሚገባው ድርጅታቸው ተጨማሪ ገለጻ የሰጡት የንቅናቄው ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ንቅናቄው ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋራም በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሱንም ጠቅሰዋል።

የስያሜ እና የመዋቅር ለውጦችን በማድረግ ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋራ በጋራ በመስራት በየወረዳዎቹ አባላትን በማደራጀት አዲስና ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የመፍጠር እንቅስቃሴዎች ንቅናቄው እያደረገ እንደሆነ ዋና ጸሃፊው አስረድተዋል።

ከሰማያዊ፣ ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ከአንድነት ፓርቲ ጋራም በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ስምምነት እንደደረሰም ተጠቅሷል።

በንቅናቄው የአደረጃጀት፣ የወደፊት እንቅስቃሴዎቹ እንዲሁም አገራችን ኢትዮጵያ እያስተናገደች ያለውን የተስፋና የስጋት ሁኔታዎች ዙሪያ ታዳሚዎች ላቀረቡት ጥያቄዎች የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ሰጥተውበታል።

በመዲናዋ አዲስ አበባ እየተደረገ ያለው ህዝባዊ ውይይት በነገው እለት በመገናኛ ኮከብ አዳራሽ እንደሚቀጥል ፕሮግራሙ ያመለክታል።