አባይ ሚዲያ ዜና

በኦሮሚያ በተለያዩ ስፍራዎች ዜጎችን በድብቅ በማሳደድ እንዲገደሉ የማድረግ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘገበ።

ተጠርጣሪዎቹ በኦሮሚያ በሚገኙ የተለያዩ አከባቢዎች በመንቀሳቀስ ኢትዮጵያውያንን ሲገድሉ እና ሲያስገድሉ እንደነበረ የሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

በድብቅ ዜጎቻችንን በኦሮሚያ ክልል አስገድለዋል ከዚያም አልፎ ገድለዋል በሚል ክስ ተጠርጥረው የተያዙት ግለሰቦች “አባ ቶርቤ” ወይም “ባለሳምንት” በሚል ቅጽል ስም ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ እንደነበረም ተዘግቧል።

ቁጥራቸው ስድስት የሚደርሱ “አባ ቶርቤ” ወይም “ባለሳምንት” በሚል መጠሪያ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦች በሰላማዊ ዜጎቻችን እንዲሁም በጸጥታ ሃይሎች ላይ የግድያ ተግባር ሲፈጽሙ እና ሲያስፈጽሙ ነበረ በሚል ክስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የኦሮሚያ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አሳውቋል።

“አባ ቶርቤ” በሚል መጠሪያ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች የመንግስት ባለስልጣናትን ጭምር ኢላማቸው በማድረግ የመግደል እና የማስገደል እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ እንደነበረ ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና የመንግስት ባለስልጣናትን ደህንነት ለመጠበቅ እና ባለስልጣናቱ ተረጋግተው የተጣለባቸውን የህዝብ ሃላፊነት እንዲወጡ የሚያግዙ ከመከላከያ ሰራዊቱ የተውጣጡ ልዩ  የሪፐብሊኩ የጥበቃ ሃይል አባላት ለስድስት ወራት ሲያደርጉ የነበሩትን ስልጠና ዛሬ አጠናቀዋል።

ስልጠናቸውን ያጠናቀቁት እንዚህ የሪፐብሊኩ የጥበቃ ሃይል አባላት የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም ህዝቡን ከጥቃት ለመከላከል ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት ልዩ ትርኢት በማሳየት አረጋግጠዋል።