በኦነግ የሚደርሰውን እልቂት ለመቆጣጠር እርምጃ እንደሚወስድ የኦሮሚያ ፖሊስ ገለጸ

አባይ ሚዲያ ዜና 

በኦሮሚያ በተለያዩ ክፍሎች የተቀሰቀሰውን ውጥረት ለመቆጣጠር አስፈላጊውን  እርምጃ እንደሚወስድ የክልሉ ፖሊስ አስጠነቀቀ።

የኦነግ ታጣቂዎች በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች ባደረሱት ጉዳት በርካታ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አሳውቋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ባወጣው መረጃ መሰረት በኦነግ ታጣቂዎች የተገደሉት ንጽሃን ነዋሪዎች ወደ 26 እንደሚደርሱ ለመረዳት ተችሏል።

በኦሮሚያ በተለይም በወለጋ የንጽኋን ኢትዮጵያውያንን ሰላም እና ደህነት ለማስጠበቅ የተጣለባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት በስራ ገበታቸው ላይ የነበሩ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላት በኦነግ ታጣቂዎች መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጸዋል።

በወለጋ ጸጥታን ለማስከበር የተመደቡ 12 የኦሮሚያ ፖሊሶች በኦነግ እንደተገደሉ የፖሊስ ኮሚሽኑ በመግለጽ ፤ ሁለት የዞኑ የፖሊስ አመራሮችም በኦነግ ታጣቂዎች ህይወታቸው ማለፉን በተጨማሪ አሳውቀዋል።

ቁጥራቸው ከ 70 በላይ የሆኑ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በኦነግ በተሰነዘረባቸው ጥቃት መቁሰላቸውን የተጠቀሰ ሲሆን፤ የክልሉ የሚሊሻ እንዲሁም የጸጥታ አካላትም በኦነግ ጥቃት ሰለባ መሆናቸው ተዘግቧል።

በወለጋ የተለያዩ ክፍሎች በክቡር አቶ ለማ መገርሳ የሚመራው የመንግስት መዋቅር በኦነግ እንዲፈራርስ መደረጉን እና የመንግስት ንብረት መዘረፉን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ገልጿል።

የኦነግ ታጣቂዎች የግለሰቦችን ንብረት ከመዝረፍ ባለፈ ባንኮችን በመስበር ወደ ሶስት ሚሊዮን ብር እንደዘረፉ ሲጠቀስ፤ ታጣቂዎቹ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጣቢያዎችን ሰብረው በመግባት 2072 ክላሺንኮቭ ጦር መሳሪዎችን መዝረፋቸውን ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።

የክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ከወራት በፊት ባደረገው የሰላም ጥሪ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከመንግስት ጋር ወደ ለየለት ሰጣ ገባ መግባቱ ይታወሳል። ኦነግን በሊቀመንበርነት የሚመሩት አቶ ዳውድ ኢብሳ የጠ/ሚ ዶ/ር አብይ መንግስት እርምጃ የሚወስድ ከሆነ የኦነግ ታጣቂዎች ጦርነት በመክፈት አጸፋውን እንዲመልሱ አዲስ አበባ ከሚገኘው ቢሮዎቸው  ትእዛዝ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም። 

በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች ሰላምን እና ጸጥታን በማደፍረስ ለንጽኋን ኢትዮጵያውያን  እንዲሁም ለመንግስት የጸጥታ አካላት ህይወት መጥፋት በዋናነት ተሳታፊ የነበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ለፍርድ የማቅረብ ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በመግለጫው አሳውቋል። ህዝቡም ተጠርጣሪዎችን በማደን ስራ ላይ በመተባበር ጥቆማዎችን እንዲያደርግ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጠይቋል።