የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅሬ ሙሉጌታ እንደገለጹት ምክር ቤቱ12ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከየካቲት 26 ቀን እስከ 29 ቀን 2011ዓ.ም ድረስ ያካሂዳል።

በመጀመሪያው ቀን የምክር ቤት አባላት በመወያያ ሰነዶቹ ላይ በንባብና በቡድን ከተወያዩ በኋላ የካቲት 27 ቀን 2011 በሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት ያደርጋሉ።

ከየካቲት 28 ቀን 2011 ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ደግሞ የስድስት ወራት የአስፈፃሚ አካላት የተጠቃለለ ሪፖርት በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት እንደሚደረግበት ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

የክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትና የክልሉን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እንደገና ለማሻሻል የተዘጋጁ ዓዋጆች ቀርበው በምክር ቤቱ ውይይት ይደረግባቸዋል ብለዋል።

እንዲሁም የአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባዔ ቻርተር ማፅደቂያ ዓዋጅ በምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

ለአራት ቀናት የሚካሄደው ጉባዔ አዳዲስ ሹመቶችን ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ወይዘሮ ፍቅሬ ገልጸዋል።