የክልሉ ምክር ቤት 5ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ በትላንት ውሎው በሰላምና ደህንነት ዙሪያ በዝግ ሲመክር ቆይቷል።

የምክር ቤቱን ውሳኔ አስመልክቶ የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሰማኸኝ አስረስ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የሁለቱ ክልል ህዝብ ለዘመናት በችግርና በደስታ በጋራ የኖረ ነው።

የትግራይና የአማራ ህዝቦች በባህል፣ በሃይማኖት፣ ሃገርን በጋራ ከጠላት በመከላከልና በመገንባት የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤቶች ናቸው።

“የሁለቱ ክልል ህዝቦች በመካከላቸው ምንም አይነት ፀብና ቂም የለም” ያሉት ሃላፊው “ይህም ትናንት የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ታሪካቸው ነገም ይኖራል”ብለዋል።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በለውጥ ፈላጊ ሃይሎች ለውጡ የመጣባቸው አንዳንድ አካላት ልዩነት በመፍጠር ሁለቱን ወንድማማች ህዝብ ወደ ግጭት ለማስገባት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ አለፍ ብሎም የግጭት ቅስቀሳ ማካሄድና መሰል አላስፈላጊ ድርጊቶች በማንኛውም መለኪያ ተቀባይነት እንደሌላቸው የክልሉ ምክር ቤቱ መወሰኑን ገልፀዋል።

በለውጡ ያልተደሰቱ አንዳንድ ሃይሎች የህዝቡን ሰላም ለማወክ የሚያደርጉትን ቅስቀሳ እንዲያቆሙ መምከር እንደሚገባም መግለጫው ጠቁሟል።

“በአማራ ክልል ያሉ አመራሮችም የሁለቱን ክልል ህዝብ ለግጭት የሚያነሳሳ ንግግር የሚያደርግ ማንኛውም አካል ከድርጊቱ እንዲቆጠብ አቅጣጫ አስቀምጧል” ብለዋል።

ምክር ቤቱ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደርና አካባቢው በቅማንትና አማራ ህዝቦች መካከል ማንነትን ምክንያት በማድረግ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሱን መገምገሙን ተናግረዋል።

“በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል የተካሄደው ግጭት አላማ የሌለውና አሸናፊም ተሸናፊም የሌለው እንደሆነ ተገምግሟል”ብለዋል።

“ግጭቱ እንዲባባስ አበክረው የሰሩ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን በመያዝ በህግ እንዲጠየቁ ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል” ብለዋል፡፡

በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ በማቋቋምና ወደ ቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ የተጀመረው የተቀናጀ ስራም በፍጥነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

“መሰል የመፈናቀል አደጋ እንዳይከሰትም በሰላም ወዳዱ ህዝቡ ውስጥ በመመሸግ የሚሰሩ ጽንፈኛ ሃይሎችን በመለየት እርምጃ እንዲወሰድ ታዝዟል” ብለዋል፡፡

በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች የተከሰተው አላማ የለሽ ግጭት መቃቃርና ቂም እንዳይኖር በህዝቦች ማካከል ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ተደጋጋሚ ውይይትና እርቀ ሰላም እንዲካሄድ አቅጣጫም አስቀምጧል፡፡

የክልሉ ህዝብ የሰላሙ ባለቤት እራሱ በመሆኑም የአካባቢን ሰላም ነቅቶ በመጠበቅ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ሳይስተጓጎሉ አንዲቀጥሉ የበኩሉን ማበርክት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ የክልሉን ያለፉት ስድስት ወራት የልማት ስራዎች ሪፖርት በማዳመጥ ይወያያል የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ ያፀድቃል፤ ሹመቶችንም ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡