ከኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ኤርሚያስ አመልጋን ጨምሮ 11 ተከሳሾች፣ አቅርበውት የነበረው የክስ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጎ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰጡ፡፡

በሜቴክ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የክስ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ የሪቬራ ኢንተርናሽናል ሆቴልና የፒቪሲ ፕሮፋይል ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዓለም ፍፁምና ዘጠኝ የሜቴክ የተለያዩ ክፍሎች ኃላፊዎች ተጠርጥረው የተከሰሱበት የሙስና ወንጀል እነሱን እንደማይመለከት ገልጸው ሰፊ መቃወሚያ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የመቃወሚያ መቃወሚያ ክሱን አጠናክሮ በመከራከሩ፣ መቃወሚያቸውን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎታል፡፡

ተከሳሾቹ የክስ መቃወሚያቸው ውድቅ ከተደረገ በኋላ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ድርጊቱን ስለመፈጸማቸውና ጥፋተኛ ስለመሆናቸው ተጠይቀው፣ ጥፋተኛ እንዳልሆኑና ድርጊቱንም እንዳልፈጸሙ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ድርጊቱን ክደው መከራከራቸውን ተናግሮ፣  ያቀረበባቸውን ክስ በሰውና በሰነድ ማስረዳት እንዲችል እንዲፈቀድለትና ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የዓቃቤ ሕግ ምስክሮችን ከመጋቢት 23 እስከ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ሌላ ያየው የክስ መዝገብ በሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የክስ መዝገብ የተካተቱና ከትራክተር ግዥ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ስምንት ተከሳሾች ክስ ሲሆን፣ በእነሱም ላይ ብይን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹ ለአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ትራክተሮች ግዥ ሲፈጽሙ፣ ሕገወጥ ግዥና ጥራት የሌላቸው ትራክተሮች ፍላጎት ሳይኖር በመግዛት ከ319.4 ሚሊዮን ብር በላይ በሕዝብና በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ክሱን ተሻሽሎ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

በተሻሻለው ክስ ላይ ክርክር ለማድረግም ለመጋቢት 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡