ጎንደር በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአፄ ፋሲለደስ እንደተቆረቆረች ይነገራል። ይሁን እንጂ ከአፄ ፋሲለደስ ንግሥና 300 ዓመታት ቀድማ በምንጮችና በተራሮች የተከበበች መንደር ነበረች ሲሉ የሚሞግቱም የታሪክ አዋቂዎች አሉ።

ጎንደር ለ200 ዓመታት የኢትዮጵያ መናገሻ ሆና አገልግላለች። ባሏት ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች እንዲሁም ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ትታወቃለች።

የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል በዓለም የቅርስ መዝገብ የሰፈረው የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት በግምባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። ጎንደርን ከፋሲል ግንብ ነጥሎ ማየት ይከብዳል። ስለ ጎንደር የተዜሙ ሙዚቃዎች የሚነግሩንም ይህንኑ ነው።

ዛሬ ዛሬ ግን የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት ስም የሚነሳው በአስደናቂነቱ፣ በታሪካዊነቱና የኪነ ህንፃ ጥበቡ ብቻ ሳይሆን አደጋ የተጋረጠበት ቅርስ በመሆኑ ነው። ቤተ-መንግስቱን  ለመጎብኘት ወደ ቦታው የሚያቀኑት  ቱሪስቶች ግን የፋሲል  ግንብ  አደጋ እንደተደቀነበት ተናግረዋል፡፡

በአጼ  ሱሱኒዮስ ልጅ እንደተገነባ የሚነገርለት የፋሲል ግንብ ለዘመናት እድሳት ተደርጎለት አያውቅም በዚህም ምክንያት ቅርሱ  አሁን ላይ  የመሰነጣጠቅ አደጋ እያጋጠመው ይገኛል  የፋሲል  ኪነ-ህንጻ  ኢትዮጲያን  በበጎ  ከሚያስጠሩ  አበይት ቅርሶች መካከል  አንዱ ነው፡፡