ያስገባሪ ስርዓትና ፤ጎሰኝነት በመስኮት ወጥቶ በበር… (በጌድዮን በቀለ )

0

በጎሳ ልክፍት የተያዙ ጢነኞች አይን ፤ የልሳኑም፤ የቀለሙም፤ የዘሩም፤ ሁሉ ተሸካሚ የሆነውን ግዙፉን ሰው እንዳያዩ ይካትርባቸውዋል ። ከጎሳቸውም መሃል የሚያዩት እየመረጡ ነው፤  የሚታያቸው እንደበቀቀን እነሱን አጅቦ የሚተመውን እንጅ እንደሰው በራሱ አይምሮና አንደበት የሚናገረውን የጎሳ አባል ከመ ሰው አይቆጥሩትም። ስለዚህ በጎሳ ልክፍት የተተበተቡ ቡድኖች ስሙን ለቡድናቸው መጠሪያነት ከሚጠቀሙበት ውጭ በዚያ ልሳን ተናጋሪ ለሆነው ህዝብ እንኳ ዴንታ የላቸውም። ስለዚህም ነው በጎሰኝነት ሽፋን የተነሱ አያሌ ጽንፈኛ ድርጅቶች ፋሽስታዊና አፓርታይድ ባህሪ በእጅጉ የሚጠናወታቸው ። የሰሞኑ አነጋጋሪ ወሬ ከጊዜው ቀድሞ የፈነዳው የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄ ነው። ባለርስት ነን የሚሉ ቡድኖች መነሳታቸውን ከሰማሁ በኋላ ቀድሞ ትዝ ያለኝ የሽሮሜዳው ዘመዴ ነበር።

 ከትውልድ ቀየው መንዝ ሰላ-ደንጋይ ተነስቶ የራስ አበበን ጦር በመቀላቀል አምስት አመት ሙሉ በዱር በገደል ከወራሪው የፋሽስት ጦር ጋር ሲተናነቅ የልጅነት እድሜውን የፈጀው ዘመዴ ወራሪውን የኢጣልያ ፋሽስት ከጀግኖች አርበኞች ጋር ሆኖ ካባረረ  በኋላ ያኔ ከትልቅ መንደርነት እምብዛም በማትሻለው አዲስ አበባ ላይ መቀመጫውን አድርጎ የቦሌ ቡልቡላ ባላባት ከሆነችው የኦሮሞ ተወላጅ ጋር ትዳር መስርቶ  ወልዶና ከብዶ የልጅ ፤ልጅ ፤ልጅ አፍርቶ በሞት ሲለይ፤ በህይወት ያሉት ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ከናትና አባታቸው በወረሱት ሽሮሜዳ መሬት ላይ ሰፍረው እስከዘንድሮ ይኖራሉ። ለአብነት ዘመዴን አነሳሁ እንጅ አዲስ አበባ እንደኔ ዘመድ፤ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር በመጡ  ኢትዮጵያውያንና ፤በንግድና በልዩ ልዩ ምክንያት ወደኢትዮጵያ ገብተው አዲስ አበባ ላይ የከተሙ አርመኖች፤ ጣሊያኖች፤ ግሪኮች-፤ አረቦችና ሌሎችም የውጭ ሀገር ዜጎችም ጉልበት፤ላብና ሃብት የለመለመች ከተማ ነች።

ከነገረ ቀደም አዲስ አበባ የማነች? የሚል የጅል መሰል እሰጥ-አገባ ውስጥ የገባነው እያንዳንዳችን የራሳችን የሆነውን ሁሉ ትተን ፤ አንደበታችንን፤ ሰው በመሆናችን ብቻ የተሰጠንን ሰርቶ ፤አፍርቶ በነጻነት የመኖር መብታችንን ሳይቀር  “ተቧድነው ለመጡ” አጉራ ጢነኞችና ማን አለብኞች አሳልፈን ከመስጠት አልፈን የምንተነፍሰውን አየር ጭምር እንዲፈቅዱልን መማጸናችን በመብዛቱ ነው።

ላለፉት ሃያሰባት ዓመታት በጎሳ ስም የተቧደኑ ባለጊዜዎች በነጻ አውጭነት ስም የቤተ መንግስቱን ቅጥር ሰብረው ገብተው በተንሰራፉበት ዘመን አስብተው እስኪያርዱን ድረስ፤ በማሽበልበል፤ በማስመሰል፤ እንዲያ ሲልም በሃይልና በማስፈራራት በላያችን ላይ የጫኑብንን “የጎሳ ትርክት” የተቀበልን እለት ለዘመናት የኖረውንና በዘመን ሂደት ተቀዳጅተነው የነበረውን ሙሉ ሰውነት አስነጥቀናል።

 አንተ ከዚህ “ጎሳ” ስለሆንክ ክልልህ 1፤2፤3፤4፤… ብቻ ነው ሲሉን “እሺ ብለን የተቀበልን እለት ወደ ትትንሽ ማንነት ተዘቃዝቀናል። መርጠው የቀቡንን ቀለም ትንፍሽ ሳንል የተቀበልን ዕለት የውነተኛው ማንነታችንን ገጽታ በማጥፋት ተባብረናል። በመጀመሪያ ከምሉእ ማንነታችን መሃል አንዷን ሰበዝ መዘው ሲያድሉን፤ አብዝሃኛውን እኛነታችንን ጉድጓድ ምሰው በመቅበር ገለውናል። ዛሬ የምንጯጯኽውና የማንደማመጠውም ካንደበቱ በቀር የሰራ ጅስሙ በቁሙ የተቀበረበት ሙት በመሆናችን ነው። እነሆ እኛ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በቡድነኞች ሶፍትዌር የተገጠመለት በሰሪዎቻችን እሳቤና እይታ ተለክቶ የሚሰጠንን እንድናስፈጽም፤ ሰሪዎቻችን በፈቀዱልን መጠን ተለክተን የተሰራን ስጋ ለባሽ ተንቀሳቃሽ ሮቦቶች ተደርገናል።

እንደዚያ ባይሆን ትላንትና ከሶማሌ፤ ከሃረር፤ ጋምቤላ ቤንሻንጉል፤ ጎንደር፤ሽሬ፤አክሱም፤ወልቃይት፤ራያ፤ ወዘተ… የተፈናቀሉና የተሳደዱ ሰዎች፤ ዝቅ ሲልም ኢትዮጵያውያን፤ ከፍ ሲልም ከራሳቸው መንደርና ቀዬ በግፍ እንዲሳደዱ የተደረጉ የሰው ልጆች ማለቱን ትተን በዚያው 27 ዓመት በተበጀልን “የጎሳ” መነጽር  ለክተን በደላቸውን ባላሳነስነው፤ሰባዊ ክብራቸውን ባላኮሰስነው፤ ምሉእ ሰብ ዕናቸውን አኮሳምነው በሰጧቸው የጎሳ መነጽር ሲፈርጇቸው አብረን ተባብረን ባልመዘናቸው፤ የተነጠቁትን የሀገር ባለቤትነት፤ ሰው በመሆንና በመፈጠር ያገኙትን የመኖር መብት ዝቅ አድርገን አውርደን ዳረጎት ተቀባዮች ፤ የባላባት ነን ባዮቹ ፈቃድና ይሁንታ እንዲሰጣቸው የሚማጸኑ ምንዱባን ባላደረግናቸው ነበር።

 ይህን ሁሉ በማድረጋችንም የጥቃቱ ሰለባ እንዲሆኑ አውቀው ለፈጠሩት ወንጀለኞች ተባባሪ በመሆን አጋልጠን መስጠታችንን ልብ አላልነውም። ይሄው ስራችንና፤ ሊያስከትል የሚችለውን ባለማስተዋላችን፤ ይሄው የተባባሪነት ድርጊታችን ሲድህ ሲድህ ከርሞ አዲስ አበባ ደረሰ። በህዝብ መስዋዕትነትና ደም የተሰባበረው የጭሰኛና ገባር ስርዓት “ የጎሳ ካባ” ተከናንቦ ሲሻው እያስፈራራ፤ እንዲያ ሲልበት እያባበለና፤ እያዋዛ፤ አስብቶ፤ ለማረድ መዝጋጀቱን አበሰረ። ”ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም”

ማንም ይሁን ማን፤ ቡድንም ይሁን ግለሰብ ፤ በነጻነት ስም የሌሎችን ህዝቦች ነጻነት ሲጋፋ፤ በመብት ስም የሌሎችን መብት ሲጥስ ፤ አደብ ቅራ የሚል የህግ ስርዓት ከሌለ፤  መንግስት አለ፤ ወይም ፍትህ አለ ማለት ፈጽሞ የማይቻለውን ያክል፤ የድርጊቱ ዋና ተዋናይ ደግሞ ራሱ “መንግስት ነኝ “ የሚለው አካል ሆኖ ሲገኝ አገር በጢነኞችና በጉልበተኛ የጎበዝ አለቆች እጅ መውደቋን ለመረዳት ጊዜ ማጥፋት ቡልሃነት ነው። “የበለስ ጫፍ ሲያቆጠቁጥ በጋ እንደደረሰ ዕወቁ…” እንዲል መጽሐፉ።

ላለፉት 27 ዓመታት በፋሽስታዊ አገዛዝ ረግጦ ሲገዛን የነበረውን ወያኔን ለማውረድ መስዋእትነት የተከፈለው ሰዎቹ “ከትግሬ ጎሳ የተወለዱ “ በመሆናቸው አልነበረም ፤  የሃያሰባቱ ዓመት የወያኔ ግፍ አገዛዝ አረመኔና በፋሽስታዊ ባህሪ የተቃኘ ለመሆን የበቃው በመለስ ዜናዊ፤ ወይም ባቦይ ስብሃት ወይም በአባ ዱላ ፤ በሽፈራው ሽጉጤ ስለተመራ አይደለም ፤ በፍጹም።

ዋናው ጉዳይ የግለስቦቹ ማሰቢያ የተቃኘው በጎዶሎና በሰንካላ ማንነት ዙሪያ በመሆኑ ነው። የተንሸዋረረው ልቦናቸው ወፍ እንኳ ሰልጥኖና ተምሮ ሊደግመው ከሚችለው የመግባቢያ ልሳን ላይ በመለጠፉና ሌሎቹን ምሉእ ሰው የሚያደርጉትን ማንነቶች ሁሉ አራግፎ በጣለ ፍልስፍና ላይ መመርኮዙ ነው።

በእንዲህ ያለ ስንኩል እይታ ላይ የተመሰረተ ፍልስፍናም፤ ከመነሻው የጨነገፈ በመሆኑ ፤ እንኳን ሌላውን ሰው ይቅርና አብዛኛውን ራሱን ገድሎ በመነሳቱ ሸውራራና ፍርደገምድል እርምጃ ላይ ያተኩራል።  አስቀድሞ የማሰቢያ ማእከሉን አጨንግፎታልና  ሚዛኔ ባለው የጎሳ መለኪያ እየሰፈረና  እያነጣጠረ ጥቃት ይፈጽማል፤ ለሁሉም ጉዳዮች መነጽሩ “ ቆሜለታለሁ የሚለው ዘር ፤ ጎሳ፤ ሀይማኖት ወዘተ” ይሆናል፤  አስቀድሞ ህሊናውን በመረጠው ቅርጫት ውስጥ በማመቁ የማንነቱም ዳኛ፤ ሿሚና ሸላሚም እራሱ ብቻ የሆነ ስለሚመስለው የጎሳ አባልነትን ፈቃድና መታወቂያ የማደልንም ስልጣን  የራሱ እስኪመስለው ድረስ ይንሸዋረራል።

ስለሆነም ከእሱ የተለየ ሃሳብ ያላቸውንም ጎሳ አባላት ሳይቀር የበትሩ ሰለባ ያደርጋቸዋል፤ ይህንን ሂትለር አድርጎታል፤ ዩጎዝላቪያ፤ ሩዋንዳ፤ ትናንትናና ዛሬም በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ይገኛል። በጎሰኝነት መርዝ ከተለከፈ ጥቃት ለመዳን የዚያ ጎሳ ወይም ሀይማኖት ወይም ዘር አባል መሆን ብቻውን አያስጥልም። በቀቀን መሆን፤ እልፍ ሲል አጉራሽ አጎንባሽ መሆን ፤የአረመኔአዊው ድርጊት ተሳታፊ መሆንንም ይጨምራል። አዲስ አበባ ይህ አይነቱ ፍርደገምድል ፤ጽንፈኛነት ያስከተለው ግፍ ፍንትው ብሎ ማሳያና ፤ማስለበሚያ ሆነች እንጅ ላለፉት 28 አመታትና ዛሬም በሌሎቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲፈጸምና እየተፈጸመ የቀጠለው በደል ምንም ጭማሪና ቅናሽ ሳያስፈልገው መንስኤው ይኼው ነበር።

በየትኛውም ጊዜ፤ በማናቸውም ሁናቴ ፤ ከመኖሪያ ቀያቸው የተሳደዱና በደል የተፈጸመባቸው ወገኖቻችን ህመምና ስቃይ እንበለ ቀለማቸውና፤ የዘር ምንጫቸው፤ ቋንቋቸው፤ወይም  እምነታቸው ሳያሳስበን  እንዲካሱና ፍትህ እንዲያገኙ ለመታገል ፤ የዚያ ወይም የዚህ ዘር ፤ጎጥ ፤ ጎሳ አባል መሆንን ባላስፈለገን ነበር፡፡ ባንድ ወገን ላይ የሚፈጸም ማናቸውም አይነት ጥቃት የሁላችንም ሆኖ ህመሙ ካልተሰማን ነገን መመዘን የሚቻለው ማሰቢያችን ላይ አደጋ ደርሶበታል ማለት ነው። ምክንያቱም በማናቸውም መለኪያ  አንድን ሰባዊ ፍጡር ለባርነት እንዲዳረግ ከፈቀድን ሁላችንም በባርነት እንድንኖር ፈቅደናልና።

ዛሬ አዲስ አበባን በግል እርስትነት እየጠየቁ ያሉ ወገኖች ጥቂት ተግ ብለው በማሰቢያቸው ለመጠቀም ቢተጉ ፤ ባንድ ሀገር ላይ “ጢሰኛና ገባር “ ስሬት ሊተከል ይገባል እያሉ መሆናቸውን ማዳመጥ በቻሉ ነበር። ትላንት ከባርነትና ከዘር መድሎ አገዛዝ ለመላቀቅ በጋራ የተደረገውን የሞት ሽረት ትግል፤ ትላንት ከጣራ በላይ ጮኽው  በዘርና በጎሳ ስም ሸንሽኖና ሸብቦ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በፋሽስታዊ ጭካኔ ሲረግጥ የነበረን ዘረኛ ቡድን ያደረሰውን ግፍ አውግዘን፤  ከህዝቡ ጎን ተሰልፈናል ያሉ መሪዎች፤  ከበደል ፈጻሚው ወገን መሀል የወጡ መሆናቸውን እያወቅን ፤ በይቅርታ እንድንሻገር ፤ እነሱ በሚያዩበትና ባደጉበት የዘር፤ ጎሳና ሀይማኖት መነጽር ሳንመነዝራቸው ኢትዮጵያን፤ አብሮነትን ፤ነጻነትን ፤ በፍትህ ላይ የተመሰረተ እኩልነትን ለማረጋገጥ “እናምናቸዋለን” ብለን ያለምርጫ ብናነግሳቸው ከምኔው ተወርውረው የዘረኝነት ነጋሪት በመጎሰም  ከዚያው የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ የገቡበት ፍጥነት አስገራሚ ነው።

ከዚህ ደግመን ደጋግመን የምንማረው ማንም ቢሆን፤ አባይ ጸሃየም ይሁን፤ ደብረጽዮን፤ ገዱ አንዳርጋቸው ይሁን አምባቸው፤ አብይ ይሁን ለማ፤ ሞፈርያት ትሁን ሽፈራው ሽጉጤ ፤ አገርን፤ ህዝብን ወገንን፤ ፍትህንና ነጻነትን ፤እኩልነትንና ዴሞክራሲን የሚያዩበትን መነጽር በልክ ከተሰፋ ዘርና ቀለም ፤ ከብዙ ማንነት መሃል በተመረጠ ነጠላና ሥስ ምርኩዝ ላይ ካንጠለጠሉት የጊዜ ጉዳይ እንጅ ወደ ጎጥ መለስ ፍርደ ገምድልነት መቀየራቸው አይቀሬ መሆኑን ነው።

ከሁሉም በላይ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” የሚለውን አማላይ መፈክር ባደባባይ ያሰማ መሪ በተናገረውና ባሰማው ጩኽት ብቻ የአብዝሃኛውን ቀልብ ስቦ የልዩነትን ካብ አፍርሶ፤የአንድነትን “መደመር” ድልድይ አበጀሁ ባለበት አንደበት ፤ ለድጋፍ ሰልፍ የወጡ ሟቾች አይን ሳይፈስ፤ ተበዳይ ፍትህ ሳያገኝ፤ የማለዳው ግፍና ሰቆቃ ገና ከህሊናችን ሳይጠፋ፤  ያለቀሱትን እምባ ለማበስ አዲስ ስርአት ለማዋለድ ሽርጉዱ በቅጥ ሳይከወን ፤ የማለዳውን የሚያስንቅ ግፍ በድፍን አገሩ እንዲናኝ ተባባሪ ሆኖ ማየት አንገት የሚያስደፋ ሰብእና ኪሳራ አመላካች ነው።

 ዜጎች እትብታቸው ከተቀበረበት ምድር የማያውቁትና ያልተረጋገጠው አጥንታቸው እየተቆጠረ፤ ታርጋ እየተለጠፈባቸው በግፍ ሲሳደዱ ፤ ማንም ከተወለዳችሁበት ፤እትብታችሁ ከተቀበረበት ሀገራችሁ የማፈናቀልም ሆነ የማሳደድ መብት የለውም ሊኖሮውም አይችልም ብሎ በመቆጣት የዜጎቹን መብት የሚያስከብር ጋሻ ይሆነናል ብለን የጠበቅነው መንግስት፤ “ በሱሷ ሰክሬአለሁ” ያለበት አንደበቱ ምራቅ ሳይደርቅ “ ከሶማሌ አካባቢ የደረሰውን መፈናቀል በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለንን የኛን ወገን የበላይነትና ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ መልካም አጋጣሚ ነው……” በማለት 500 ሽዎቹን ተፈናቃዮች ለማስፈር እየሰራን ነው ማለት፤ የቆሙበት የጎሳ እርካብ ከትዝብትም በላይ ያለፈ የኢትዮጵያዊነትን መለኪያ በመረጡትና የኔ ባሉት ጎሳ ላይ አንጠልጥሎና አሳንሶ እንዳሳያቸው አመላካች ነው።

ይህ ደግሞ በሰብእና ክስረት ከሚደርሰው የህሊና ክስ በላይ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀሬ ነው። እንበለ ዘርና የጎሳ ጭንብል ሳይሸፋፈን “ ባንተ መጀን “ ያላቸው ህዝብ፤  ምሉዕ ሰብናውን አሟልቶ የሚወክልነትን ኢትዮጵያዊነት በማወደሳቸው የሰጣቸውን ይሁንታና የጣለባቸውን አደራ መልሶ ለመቀበል የማይችል መስሎአቸው ከሆነም “ ንጉስ በሰራዊቱ ብዛት አይድንም” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍ ጥቅስ ዘንግተውታል ማለት ነው።

ለዘመናችን “ባለጉልቶችና ባላባት ነን ባዮች “፤

ላለፉት አርባ አመታትና ከዚያም በላይ የጢሰኛና ገባር ስሬትን ለማስወገድ ብዙሽህዎች የማይተካ ነፍሳቸውን መስዋዕት አድርገዋል፤ የተከፈለው መስዋእትነት የባለጉልትን ስራት አውርዶ “የዘር ካባ ያጠለቁ የጎበዝ አለቆችን” ለመተካት አልነበረም። ትግሉ ኢትዮጵያን የሁላችን ፤ የጋራችን ለማድረግ ነበር። ብትወዱትም ብትጠሉትም በዘመን ሂደት ፤ በጊዜ ርቀት የተሸራረፈውን ሳይጨምር፤  ተሸራርፎ በቀራት ድንበር ፤ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ ፤ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፤ በየብስ፤ በባህርና በጠፈሩ ላይ የሚገኘው ሀብትም ሆነ ንብረት በውስጧ የሚኖሩት ዜጎቿ የጋራ ንብረት ነው።

 በኢትዮጵያ ላይ ማንም ያነሰ ወይም የበለጠ ባለቤትነት መብት የለውም፤ ዜጎች ሁሉ በፈለጉትና በፈቀዱት የኢትዮጵያ ምድር ተንቀሳቅሰውና ተዟዙረው ሀብት አፍርተው ፤ ቤት ሰርተው ለመኖር የማንም ጎሳ ወይም እምነት፤  ወይም ዘር አባል መሆን አያስፈልጋቸውም፤ የሚለውን ትክክለኛ እምነት እውን ለማድረግ ሌላ ተጨማሪ ሞት የሚጠይቅና የሚያስከፍልም ቢሆን እንኳ አገሩን የሚወድ፤ ነገ ለሚወለዱት ልጆቹ የተመቻቸ አገር እንዲኖረው የሚሻ ዜጋ ሁሉ ከፍ አድርጎ በመጮህ፤ እነዚህ መብቶች በህግ እስኪረጋገጡ ድረስ የመቅለስለስና የመለማመጥ ፖለቲካውን አቁሞ እስከመጨረሻው በቁርጠኝነት ለመታገል መዘጋጀቱን ሊያውቁት ይገባል።

ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ የምንለው ፤ ከስሟ  የተጣበቀ ፍቅር ስላለን ብቻ አይደለም ። በዘመናት አብሮነት የማይነጣጠል ማንነት ተጋምዶ ያቆላለፈን እጣፈንታችን ፤ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ከመኖር ውጭ ሌላ ምንም ተስፋ የሌለን ሚልዮኖች ዜጎች በመኖራችንም ጭምር ነው። ለእኛ፤  ኢትዮጵያን ማጣት የቅንጦት ጉዳይ አይደለም ፤ የህልውና እንጅ። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ወሰን የለንም፤ የጎሳ፤የሀይማኖት፤የዘር ወይም የቀለም ድንበር ስለማያግደን የኢትዮጵያ በተባለው ቦታ ሁሉ ሰርተን ለፍተን ጥረን ግረን ሀብት አፍርተን፤ ወልደን ከብደን ለመኖር የማንንም ፈቃድ አንጠይቅም ፤ ስለዚህም ነው ትግላችን በጎሳ አውራ ጢነኞች የተነጠቀውን  ነጻነታችንንና ሰባዊ ክብራችንን እስክናስመልስ ድረስ ጸንቶ ሊቅጥል የሚገባው። ከኢትዮጵያ ላይ አንዲት ሰበዝ እንኳ እንዳይቀነስ የምንታገለውና አብረን እንሁን የምንለውም አብረን ከመጥፋት ለመዳን ነው።

አሁንም ደግመን ያለምርጫ በላያችን እንዲሰለጥኑብን የፈቅድንላቸውን “የለውጥ አሸጋጋሪ መሪዎች” እንዲሰሙን እንጠይቃቸዋለን፤ ለምን እንደደገፍናችሁ፤ ስለምን እንዳከባበርናችሁ ገና ሳይመሽ ከዘነጋችሁት “ሰው” መሆናችሁን ረስታችሁታል ማለት ነው። ገና ዶሮ መልሶ ሳይጮህ ባደባባይ ለገባችሁልን ቃል መታመን ካቃታችሁ ከእናንተ በፊት የነበሩ በመስኮት ወጥተው መቀሌ የከተሙት ቀንዳም፤ቀንዳም ጎሰኛ አምባገነኖች ከደረሰባቸው እጣ-ፈንታ በቂ ትምህርት አልገበያችሁም ማለት ነው። የጊዜ ጉዳይ እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ደጋግሞ ከሚደርስበት የነጻነት ሾተላይ ተላቆ አምጦ የወለደውን ልጁን ከሞት ለመታደግ ስር ምሶ ቅጠል በጥሶ መዳኒቱን የሚቀምምበትና የሚተባበርበት  ጊዜ እንደቀረበ ለማወቅ ነብይ መሆንን አይጠይቅም። ስለሆነም ጨርሶ ሳይመሽ ሚናችሁን ለዩ፤ ከኢትዮጵያ ወይስ ከምሉዕ ሰብእና መሀል ተመንዝሮና ተመዞ ከወጣ ጎሰኝነት?