የአድዋ ድል፣ የኢትዮጵያዊ ብሄረተኛነትና የተሟላ አንድነት ድልና ፈተና ( አንዳርጋቸው ጽጌ )

0

ማርች 9 2019

በጀርመን ፍርንክፈርት

የ123ኛውን የአድዋ በአል ምክንያት በማድረግ የቀረበ ጽህፍ

ውድ ወገኖቼ!

በቅድሚያ ንግግሬን በምስጋና እንድጀምር ፍቀዱልኝ። ከእስር ተፈትቼ ዛሬ በፊታችሁ ለመቆም የበቃሁት በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ትግል እንደሆነ አውቃለሁ። ይህ ትግል፣ ዜጎች በህይወታቸው፣ በንብረታቸው፣ በኑራቸውን፣ በግዚያቸውና በገንዘባቸው  መስዋእትነት የከፈሉበት ነው። በሃገርና ከሃገር ወጭ እኔ እንድፈታ በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደ በየምነታቸው እንደጸለዩ እንደተማለዱልኝ ስለት እንደገቡልኝ ከእስር ከተፈታሁ በኋላ ማወቅ ችያለሁ። ይህ ለኔ ፈጽሞ ያልጠበቅሁት ነበር። ይገባኛል ብዬም አላስብም። ፍራንክፈርት በዚህ እኔን የማስፈታት ትግል የራሱን ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ያደረጋችሁትን የሆናችሁትን ሁሉ ሰምቻለሁ። ለዚህ ልቤ ተነክቷል። በዚህ በተነካ ልብ በከፍተኛ ትህትና አመሰግናችኋለሁ።

ይህን ካልሁ ተጋብዤ ወደ መጣሁበት እርስ ልመለስ፤

የዛሬውን የንግግር ርእሴን  የአድዋ ድል፣ ወደ የተሟላ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛነትና አንድነት ጉዞ ድልና ፈተና  የሚል ርእስ ሰጥቸዋለሁ። በእዚህ ርእስ ላይ አድማጮቼ  ግንዛቤ እንዲያገኙ ከአድዋ ጦርነት በፊት ከነበረው የሃገራችን ታሪክ  ትንሽ ቀደም ካለው ዘመን መጀመሩን መርጫለሁ። ከአጼ ቴዎድሮስ ዘመን፣

የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ በጥቅሉ በቋራው ቴዎድሮስ የበላይነት መረጋገጥ በተጠናቀቀው የዘመነ መሳፍንት ማብቃት የሚጀምር ነው፡፡ ይሁንና ቴዎድሮስ ከ1855 (እ.አ.አ) እስከ 1868 (እ.አ.አ) በዘለቀው ዘመነ መንግሥታቸው ሊፈጥሩት ሞክረው የነበረው ዘመናዊ አስተዳደር፤ ከውጭ እና ከውስጥ በገጠሙት ውጥረትና ግጭት በእንጭጩ ተቀጭቷል፡፡ ሃገር ዘመናዊ እንዲሆን፣ አጼ ቴዎድሮስ የወሰዷቸው የማሻሻያ ርምጃዎች ፣ የግብር ማሻሽያ፣ የመከላከያ ወይም የሰራዊት አደረጃጀት ማሻሻያና ከዛም አልፎ መሳሪያ በሃገር ውስጥ የመስራት ፍቅራቸው ጦረኛ ከመሆን፣ የአካባቢው መሳፍንትና ባላባትን ማስገበር የሚያስችል አቅም ለማግኘት አልነበረም። የቴዎድሮስ ሃገር የማዘመን ህልም በአፍሪካ ወስጥ እጃቸውን እያስገቡ ወደ ኢትዮጵያም እየተጠጉ ከነበሩ የውጭ መንግስታት መስፋፋትና ያ መስፋፋት ከወለደው ስጋት ጋር የተያይዘ ነበር። የቴዎድሮስ መሳሪያ በሃገር ውስጥ የመስራት ፍላጎት፣ ጃፓኖች ሃገራቸውን ለማሰልጠን ውሳኔ እንዲወስኑ ካደረጋቸው ምክንያት ጋር አንድ አይነት ነበር።

ጃፓኖች የታያቸውና ያሉት የሚከተለውን ነበር።

“ራሳችንንና ማንነታችንን፣ ባህላችንን፣ እምነታችንን ከጥፋት ለመከላከል፣ እንደ ሰለጠኑት ሃገሮች በሁሉም መልኩ ጠንካራና የተደራጀን ሆነን መገኘት አለብን።” ነበር። ጃፓኖች ይህን በማድረጋቸው ማንነታቸውን ባህላቸውን እምነታቸውን እንደጠበቁ ነገር ግን ታላቅ የዘመኑን ስልጣኔ የተላበሱ ሆነዋል። የስልጣኔ ትርጉም የነጭን ግሳንግስ ማግበስበስ ሳይሆን ከነጭ ስልጣኔ ማንነትን ለመከላከል የሚበጀውን ሁሉ ነቅሶ አውጥቶ መጠቀም ማለት እንደሆነ ጃፓኖች ለአለም ምሳሌ ሆነዋል።

የቴዎድሮስም እይታ ይኽው ነበር።

ዘመናዊ ስልጣኔ፣ ባህልን፣ እምነትን፣ ማንነትን፣ መከላከያ መሳሪያ አድርገው ነበር ያዩት። እንደነጮቹ መሳሪያ በሃገር ውስጥ የሚሰራ ስልጣኔ ደግሞ ቁልፉ ራስን መከላካያ ተደርጎ ነበር የታያቸው።

የቴዎድሮስ ባህል፣ የቴዎድሮስ እምነት፣ የቴዎድሮስ ማንነት፣ ዘመነ መሳፍንት ያደቀቃትን ኢትዮጵያ አንድ አድርጎ በሚያስቀጠል ግዛት ውስጥ የሚገኝ ህዝብ ባህል እምነትንና ማንነትን የሚመለከት ሊሆን ይችላል።  ዛሬ ኢትዮጵያ ወስጥ ያሉትን ማንነቶች፣ እምነቶች፣ ባህሎች ግምት ወስጥ ያላስገባ ሊሆን ይችላል። እውነት እንነጋገር ካልን ሊሆንም አይችልም ነበር። አላማው ግን  “ካልሰለጠንን፤ ዘማናዊና ጉልበተኛ ሃገር ካልሆንን፤ እንጠፋለን”  የሚል ነበር።

ከቴዎድሮስ በኋላም ንጉሰ ነገስትነቱን የተረከቡት የትግራዩ አፄ ዮሐንስ፣

ቴዎድሮስ በጠቆሙት የዘመናዊ አስተዳደር ራእይ መጓዝ የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። ቴዎድሮስን አሻጥር በመስራት የታወቁበት የታሪክ ምእራፍ ሊኖራቸው ይችላል። ከሰሩት በርካታ ቁም ነገር መሃል ግን ይህ እየተመዘዘ የሚነገርባቸውም ፍትሃዊ አይደለም። በዚህም አሻጥር ቢሆን ከእንግሊዞች ጋር የገቡበት ስምምነት አገር የመሸጥ ስምምነት አልነበረም። እንግሊዞች በቴዎድሮስ የተያዙባቸውን ሰዎች ካስለቀቁ በኋላ ኢትዮጵያን ጥለው እንደሚወጡ፣ በመሳሪያ ሰራዊታቸውን እንዲያስታጥቁላቸውና  ለሰራዊታቸው ዘመናዊ ስልጠና እንዲሰጡላቸው ብቻ ነበር። 

አጼ ዮሃንስ የነበራቸው አቅምና ማህበራዊ መሰረት ከየግዛቱ መሳፍንት እና መኳንንት ጋር ተግደራድሮ ሳይሆን ተደራድሮና ተስማምቶ ንጉሰ ነገስት ሆኖ መቀጠል እንጂ እንደ ቴዎድሮስ አንድ የተማእከለ አስተዳደር፣ የግብር ስርአት፣ ወታደራዊ ተቋም፣ ያለው ሃገር መፍጠር መሆን አልቻለም። ራሳቸውን ንጉሰ ነገስት ብለው የሸዋውን ምኒሊክንና ሌሎችንም ንጉሶች አድርጎ ለመቀበል የተገደዱት በዚህ ምክንያት ነበር።

ይሁንና አጼ ዮሃንስም ልክ እንደ ቴዎድሮስ ሃገሪቱ በዙሪያው ነጮችና ግብጾች በሚያደርጉት መስፋፋት አደጋ ላይ መውደቋን የተረዱ፣ ይህን ለመቋቋም ይቻላል ብለው ያሰቧቸውን እርምጃዎች ለመውሰድ ወደ ኋላ የማይመለሱ ለመሆናቸው ታሪካቸው ያስረዳል።  አጼ ዮሃንስ በእንግሊዞች ቢከዱም ኢትዮጵያን የባህር ወደብ እንዲኖራት ለማድረግ ያደረጉትን ጥረት፣ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ሊያጠቁ የመጡትን የውጭ ወራሪዎች፣ ግብጾችን እና ጣልያኖችን፣ በኢትዮጵያ ንጉሰ-ነገስትነታቸው ባሰለፉት የኢትዮጵያ የጦር ሃይል ማሸነፋቸው በዘመናዊ ታሪካችን ላይ ትልቅ ትርጉም ያለው ክንዋኔ ነው፡፡

(ልብ በሉ በዋንኛነት የአጼ ዮሃንስ ጦር ከዛሬዋ ኤርትራና ከዛሬዋ ትግራይ፣ ትግርኛ ተናጋሪዎች ቀደምቶች የተውጣጣና የተሞላ ጦር ነበር። በኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት ስር የተዋጋ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ጦር እንጂ የትግራይ ጦር አልነበረም። እነዛ ሁሉ ያ በአጼ ዮሃንስ ስር የተሰለፈ ኢትዮጵያዊ ሰራዊት ጣሊያኖችንና ግብጾችን ድል የመታባቸው ግዛቶች ዛሬ አንዳቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ የሉም። ቦታዎቹ  እነጉንዳ፣ እነጉራእ፣ እነደንጎሎ የኤርትራ፣ ታሪኩ የኢትዮጵያውያን ሆነዋል። ቦታዎቹን በባለቤትነት የያዟቸው ኤርትራውያን በነዚህ ቦታዎች ላይ የተገኘው ድል የነሱም ቀደምቶች የተሳተፉበት ድል ቢሆንም ፣ ኢትዮጵያ ከሚባል ሃገር ጋር የሚያገናኝ ታሪክ ስለሆነ እንዲተረክ አይፈለግም። አይዘከርም። አይታወስም። የታሪክ ምጽት ይሏል ይህ ነው።)

አጼ ዮሃንስ በአጭሩ የንግስና ዘመናቸው ዘመናዊ በሆነ መልኩ ኢትዮጵያውያዊ በሆኑ እና ባልሆኑ ኃይሎችና እና ሕዝቦች መሃል ያለውን ልዩነት በማጉላት፣ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ከሌሎች ሃገሮች፣ መንግሥቷንም ከሌሎች መንግሥታት የተለየና በራሱ የቆመ ህልውና ያለው መሆኑን በማሳየት፣ በታሪክ እየተጠናከረ ለመጣው የኢትዮጵያዊ ማንነት እና ሃገራዊ ስሜት መሰረት ጥለው አልፈዋል፡፡ ህይወታቸውም ያለፈው የተወለዱበትን ትግራይን ሲከላከሉ ሳይሆን ጎንደርን አቃጥሎና በዝብዞ የሄደውን የሱዳን የመሃዲ ጦር ለመወጋት መተማ ሄደው መሆኑ ማስታወሱ ተገቢ ነው።

(ያ የመሃዲ ጦር ደግሞ በአብዛኛው ሱዳን ሳይሆን ራሳቸው አጼው ክርስቲያን መሆን ወይም ሃገር ጥሎ መውጣት የሚል አስከፊ የምርጫ አጣብቂኝ ወስጥ የጨመሩትና በዚህ የተነሳ እምነቴን ከምቀይር ሃገር ጥዬ ብሄድ ይሻላል ባሉ በርካታ የሃገራችን የእስልምና እምነት ተከታዮች የተሞላ መሆኑ ሌላው የታሪክ ምጸት ነው። )

ታሪክን ያለዘረኛ መነጽር እንቃኘው ካልን አጼ ዮሃንስ በነዚህ ጦርነቶች ተሸንፈው ቢሆን ኖሮ ለአደዋ ጦርነትና ድል የምትተርፍ ኢትዮጵያ አትኖርም ነበር። እነዚህ የአጼ ዮሃንስ ድሎች ያንን ያህል ታሪካዊ እርባና የነበራቸው መሆኑ መዘንጋት አይገባም።

የእነዚህ ድሎች ውጤት ዘመነ መሳፍንት አዳክሞት የነበረውን የንጉሰ ነገስቶች ታላቅነት እና ገናናነት ማደስ፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያን አኩሪ የታሪክ ውርሶች፣ አዲስ ከተገኙት ሃገራዊ ድሎች ጋር ማዋሀድ እና ብሎም የዘመናዊ ሃገራዊ አመለካከት ማቆጥቆጥ ሆነ፡፡

ከሁሉም በላይ፣ ማለትም በሃገር ውስጥ አስተዳደርን፣ ሕግን፣ የጦር ኃይልን በሚመለከት ከተወሰዱ እርምጃዎች በላይ፣ ኢትዮጵያ በዘመኑ ከነበሩ የአለም ሀገሮች መሃል በሀገርነቷ፣ በአለም ከነበሩ መንግሥታትም መሃል በመንግሥትነቷ፣ አለም-አቀፍ እውቅና ያገኘችበት የታሪክ ወቅት መሆኑ የምኒልክ ዘመነ-መንግስት ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ወቅቱ ለረጅም ጊዜ መንግሥታት ትክክለኛነታቸውን ለማስረገጥ ጉልበትን በመጠቀም ሲንቀሳቀሱበት የኖሩበት ባህል፣ በመንግሥታት መሃል በተደረሱ ስምምነቶችና ሕጋዊ ውሎች መተካት የተጀመረበት ነበር፡፡ የምእራብ አውሮፓ መንግሥታት በመሃከላቸው የነበረውን የርስ በርስ የቅኝ ግዛት ሽሚያ እና ግጭት በስምምነት ለመፍታት ውልና ቃል ኪዳን የገቡበት፣ የየራሳቸውን መንግሥታት እና የግዛት ሉአላዊነት አይገሰሴነት የተቀበሉበት ወቅት ነበር፡፡

በዚህ ወሳኝ የታሪክ ወቅት እንደ ሃገር መቆም ወይም አለመቆም፣ እንደ መንግሥት መቆየት ወይንም መጥፋት፣ እንደ አንድ ሃገር ሕዝብ መኖር ወይም አለመኖር ብዙዎቹ የተፈተኑበት ወቅት ነበር፡፡ በአፍሪካ እና በእስያ፣ እንደ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን እድሜ የነበረው ነጻ መንግሥት እና ሃገር የነበራቸው ሕዝቦች በአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ስር የወደቁበት ወቅት ነበር፡፡ በተለይ፣ የአውሮፓውያኑ ኃያላን መንግሥታት አፍሪካን ለመቀራመት በበርሊኑ ከተማ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ገደማ የደረሱበት የበርሊኑ ስምምነት እየተባለ በታሪክ የሚጠቀሰውን ሰነድ ከተፈራረሙ በኋላ፣ የቅኝ ግዛት ማስፋፋት ተግባራቸውን በምድረ አፍሪካ አጣድፈው መላውን አፍሪካ በቅኝ ግዛት መዳፋቸው ሲያስገቡ፣ ኢትዮጵያ ብቻ፣ ዳር ድንበሯን እና የመንግሥቷን ሉአላዊነት ማስከበር የቻለች ነጻ ሃገር ሆና በታሪክ ፊት ወጣች፡

ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በምኒልክ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ እና የጦር ኃይላቸው ከኢትዮጵያ በሺህ እጅ ይበልጥ የነበሩትን የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት፣ የሃገራችንን መንግሥት እና የዳር ድንበሯን ሉአላዊነት እንዲቀበሉ ማድረግ ችሏል፡፡ ይህንን በይፋ እና በውስጠ-ታዋቂነት ከአውሮፓውያኑ ኃያላን ጋር የተደረሰን ስምምነት በመጣስ እና ኢትዮጵያንም በቅኝ ግዛቱ መዳፍ ውስጥ ለማስገባት የዘመተውን የጣሊያን የጦር ኃይል አድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት፣ በዓለም ላይ እየተከፈተ ለነበረው አዲስ ዘመን ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ጠንካራ መደላድል ላይ አስቀምጧቸዋል፡፡

ቅድመ ምኒልክ ከስሜን ወደ ደቡብ፣ ከድቡብ ወደ ስሜን ከምስራቅ ወደ ምእራብ ከምእራብ ወደ ምስራቅ፣ በሁሉም አቅጣጫ የሚደረጉ አንዱ በሌላው ላይ የሚዘምትበት የሚያስገብርበት የሚዘርፍበት ባሪያ የሚያደርግበት ማለቂያ የሌላቸው በሽህ የሚቆጠሩ አመታት የታሪክ ሂደት ታልፏል። ከአደዋ ጦርነት በፊት የተከናወነው የአጼ ምኒሊክ ግዛታቸውን ወደ ደቡብ የማስፋፋት እርምጃ ቀደም ብሎ የነበረው የታሪካችን ቅጥልጥሎሽ እንጂ አዲስ ነገር አልነበረም።  አዲስ፣ ልዩና ታሪካዊ ያደረገው ነገር ሌላ ምክንያት ነው።  ይህም ምኒሊክ እንደ ንጉስ የመጡበት ዘመንና ወቅት ከዛ ቀደም ከነበሩ ወቅቶች በሙሉ የተለየ መሆኑ ብቻ ነው።

የተለየ ያደረገው ቀደም ብዬ እንደጠቅስኩት  በአለም ላይ ሃገሮችን በተመለከተ አዲስ ከዚህ ቀደም ያልነበረ አተያይ ብቅ ያለበት ወቅት መሆኑ ነው። ይህ ዘመን ሃገሮች እርስ በርሳቸው እውቅና የሰጡት የግዛት ዳር ድንበርና ይህን የተመለከተ ስምምነትና ውል መግባት የጀመሩበት፣ ብዙ ሃገራትም ዛሬ ይዘው የምናያቸውን የግዛት ድንበራቸውን አለም አቀፍ እውቅና ያሰጡበት ዘመን መሆኑ ነው።

ጉልበት ያላቸው በጉልበታቸው፣ ጉልበት የሌላቸው ከጉልበተኞች ተጠገተው የታወቀ ግዛት ያላቸው ሃገር ሆነው ሲቆሙ፣  ጉልበት የሌላቸው ጉልበት ያላቸው ሃገሮች አካል ተደርገው በቅኝ ግዛትነት እንዲያዙ የጉልበተኞች አለም አቀፍ ስምምነት የተደርሰበት ዘመን መሆኑ ነው።   

በዚህ ታሪካዊ ወቅት ኢትዮጵያ ከዘመነ መሳፍንት ስር እንደነበረች፣ እንደተጨራመተችና እንደተዳከመች ተደርሶባት ቢሆን ኖሮ የዛሬው ሃጎስ ሃሪ፣ የዛሬዋ አበበች አቢጌል፣  የዛሬው ሌንጮ ኢታሎ ሆነን በሶስትና አራት የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ስር ወድቀን፣ ቋንቋችን ባህላችን ወይ የእንግሊዙ ወይ የፈረንሳዩ ወይ የጣሊያኑ ሆኖ፣  ዛሬ የምንጠበብለት የምጨነቅለት ያዙኝ ልቀቁኝ የምንልበት ማንነታችን ወድሞ፣ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ቀየ ተፈናቅለን፣ የገሚሶቻችን ቀደምቶች የነጮች ባሮች ሆነው ተግዘው፣ የቀሩት እንድ አሜሪካ ህንዶችና እንደ አውስታራሊያ አቦርጅኒዎች ነጭ በሚያመጣው በሽታ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አፈና አልቀው፣ የተረፍነውም በብዙ ሃገራት ተከፋፍለን ሌላ ፍጥረቶች እንሆን ነበር። 

ቴዎድሮስ የጀመረውን፣ ዮሃንስ ከቱርኮች፣ ከግብጾችና ከጣሊያኖች ጋር ተዋግተው በማሸነፍ ፈር የቀደዱለትን፣ ምኒሊክ በምስራቅ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ግዛታቸውን በማስፋት ያጠናከሩትን ሰፊ ግዛትና ብዛት ያለው ህዝብ በማካተት በአለም ላይ ወሳኝ ከሆነው የታሪክ ወቅት ጋር የተገጣጠምንበት ሁኔታ መፈጠሩ ነው፤ የሚኒሊክን ዘመን ልዩ የሚያደርገው።

በምኒሊክ የደቡብ ዘመቻዎች የኢትዮጵያ ግዛት ሰፈቶ እጅግ ከፈተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ባያካትትና በአንድ ላይ ሆኖ ጣሊያኖችን ባያሸንፍ ኖሮ ዛሬ በዚህ አዳራሽ ውስጥ ኢትዮጵያ በሚል ሃገር ዜጎች ስም ተሰባስበን መገኘት ባልቻልን ነበር። ምክንያቱም እስከዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ጥንካሬ ከህዝቧ ብዛት የሚመነጭና በሰራዊት ደረጃ ልታሰልፈው በመትችለው ተዋጊ ቁጥር ብዛት እንጂ በሰራዊቷ ዘመናዊነትና በትጥቁ ጥራት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ነው። 

ይህ ከንጉሰ ነገስት ምኒሊክ  ዘመነ መንግስት ጋር የተገጣጠመውን የግዛት መስፋፋትና የአድዋ ድል መገኘት ራሳችን ዛሬ ለምንገኝበት የታሪክ እድል ያበቃ ብቻ ሳይሆን የአለምን የታሪክ አቅጣጫ ያስቀየረ ነው። እኛ ግን ይህንን ታላቅ መሬት አንቀጥቅጥ፣ በሁላችንም ቀደምቶች የተሰራ የታሪክ ኩነት እርስበርሳቸን ስንናቆር አሳንሰን፣ አደብዝዘን፣ ከእናካቴው ልንቀብረው ስንሞክር እፍረት የለንም።

ወደ ወገኖቼ!

የሚገርመው ነገር ከእኛ በላይ የአድዋን ድል የተረዱት ሌሎች በመላው አለም የሚገኙ ጥቁሮች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናቸው። ኢትዮጵያ ለሚባል ሃገርና ኢትዮጵያውያን ለሚባሉ ሰዎች እነዚህ ጥቁር ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያሳዩት አድናቆትና ክብር እኛ ተሸንፈን ቢሆን እጣቸው ከመቼውም የከፋና አሰቃቂ  ይሆን እንደነበር ጠንቅቀው ሰለሚያውቁት ነው። ልብ በሉ እነዚህ ጥቁር ወንድሞቻችን የሚያውቁት በጋራ አድዋ ላይ ተሰባስቦ ጣሊያንን ድል የመታውን ኢትዮጵያዊ እንጂ ኦሮሞውን፣ አማራውን፣ ትግራዋዩንና ሌላውንም አያውቁትም።

ጥቁሮች ብቻ አይደሉም፣  ዘመን እያለፈ፣ ታሪክን በዘር መነጽር ሳይሆን  በታሪክነቱ ማየት የጀመሩ የነጭ ጸሃፊዎች መምጣት ከጀመሩበት ወቅት አንስቶ የአድዋን ድል ታልቅነት ያላመላከተ የነጭ ጸሃፊ አይገኝም።

ከእነዚህ ጸሃፊዎች አንዱ ሬይመንድ ጆናስ የተባለው የታሪክ ምሁር የዛሬ 6 አምት ገደማ “የአድዋ ውጊያ” በሚል ርእስ በጻፈው መጽሃፉ ላይ ምን እንደሚለን እንስማ፣

“ኢትዮጵያ በምናብ የምትሳል የኩራት ምንጭና መገኛ፣ አፍሪካ ማለት ኢትዮጵያ  የሆኑበት ሁኔታ ተፈጠረ” ይለናል። 

ለኛ ለኢትዮጵያውያን የአድዋ ድል ትርጉሙ በነጭ የባርነት ቀንበር ውስጥ አለመውደቃችን ነው። ለአድዋ ውጊያ መጽሃፍ ጸሃፊ ለሬይመንድ  ጆናስ አድዋ ከዛ በላይ ነው። 

“የአድዋ ድል የዓለምን የታሪክ አቅጣጫ የወሰነ ድል ነው” ይለናል።

“ታሪክ ጸሃፊዎች”

 ይላል ሬይመንድ

 “ታሪክ ጸሃፊዎች 20ኛውን ክፍለ ዘመን የአሜሪካ ከፍለ ዘመን ይሉታል። ምክንያቱም የአውሮፓውያን አንጻራዊ መዳከም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ኃይል ሆና መነሳት የጀመረችበት ስለሆነ፤ ያ ወቅት ትርጉም የተሰጠው ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፓዊ ኃይል የሆነ ሃገር በጦር በሌላ ኃይል፣ በአሜሪካ የተሸነፈበት ማለትም ስፔን  በአሜሪካ የተሸነፈችብት ስለሆነ፤ ቀጥሎም ራሽያ በጃፓን የተሸነፈችበት የ1905 ጦርነት መጣ፣ የዘርን (የነጮች የበላይነትን)፣ የታላላቅ ነገስታት ግዛትንና አሰላለፍን ያንገጫገጨ ዘመን መጣ ይሉናል። ከነዚህ ሁሉ ቀደሞ ግን አዲሱ ከፍለ ዘመን፣  (20ኛው ክፍለ ዘመን ማለቱ ነው ) ምን እንደሚመስል ያመላከተው ታሪካዊ ኩነት የተከናወነው በ1896 አድዋ በሚባል ቦታ ላይ የሆነው ነገር ነው” ይለናል ይህ የታሪክ ጸሃፊ።  

ይህ የአድዋ ውጊያ መጽሃፍ ጸሃፊ እኛ ተሸንፈን ቢሆን ኖሮ  የአለም ታሪክ እንዴት ይቀየር እንደነበር ሲያብራራ እንዲህ ይለናል።

መልእከቱን ግልጽ ለማድርግ በማሰብ የራሴን ማብራሪያ ጨምሬ እንደሚቀጥለው አቅርቤዋለሁ።

(አፍሪካ እንደ አውስትራሊያ፣  ኒዊዚላንድና  ሰሜን አሜሪካ የነጮች መኖሪያ ክፍለ አህጉር ትሆን ነበር። አብዛኛው አፍሪካዊ በበሽታ፣ በጦርነት፣ በባርነትና በማግለል በሌሎች ማህበራዊ ጥቃቶች ቁጥሩ ተመናምኖ እንደ አሜሪካን ህንዶችና የአውስትራሊያ አቦርጂኒዎች አይነት ይዞታ ውስጥ ይወድቅ ነበር።)

“ይህ የነጮች መስፋፋት ከአፍሪካም አልፎ ወደ እስያ ለመሄድ የልብ ልብ ይሰማው ነበር። እንዲህ አይነቱ አፍሪካን የነጮች አህጉር የማድረግና ከዛም አልፎ ነጮችን በዓለም ላይ ተስፋፍተው መላው አለምን የነጮች አለም የማድረግ ህልም፣ ህልም ሆኖ እንዲቀር ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ጣሊያንን አድዋ ላይ  በማያዳግም መልኩ በማሸነፋቸው ነው።” ይለናል ሬይመንድ። 

“የአድዋ ውጊያ” መፅሃፍ ፀሃፊ፣  “የአድዋ ድል አድዋ ለራሷ ለኢትዮጵያ ከነጮች የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ራሷን ተከላክላ ማትረፏ ብቻ ሳይሆን እንደማንኛው ዘመናዊ ሃገር ዳር ድንበር ያላት፣ አለም አቀፍ እውቅና ያገኘች ራሷን የቻለች ሃገር ብቻ ሳይሆን ራሱን የቻለ ኢትዮጵያዊ የሚባል ህዝብ ያላት ሃገር አድርጓታል” ይለናል።

እንዴት ለሚለው ጥያቂያቺን የሚከተለውን መልስ ሰጥቶናል።

“የአድዋ መልእክት ግልጽ ነው። ብሄራዊ ገድል ነው። የዘመናዊ ሃገር መሰረት ነው። ገዥው ሚኒሊክ ለኢትዮጵያውያን ጥሪ አቀረበ። ትግሬው፣ ሸዌው፣ ኦሮሞው፣ ወላይታው እና ሌሎቹም ልዩነታቸውን ወደ ጎን አድርገው የጋራ ጠላታቸውን ለይተው የጋራ ሃገር እንዳላቸው ተረዱ። ሃገራት እንደ ሃገር እንዲቀጥሉ ትርጉም የሚሰጣቸው ሃይማኖት፣ ዘር፣ ጎሳ፣ ሳይሆን በምን መጠን ነጻነታቸውን መከላከል መቻላቸው ነው። ወረራውን መመከት የሚቻለው በኢትዮጵያ ደረጃ ብቻ ነበር”።

ውድ ወገኖቼ

ሬይመንድ ይህን በማለት “እንደ ኢትዮጵያ በጋራ ባንቆም ኖሮ የኛ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣  የመላው ጥቁር ህዝብ ታሪክ ከዛም አለፎ የመላው አለም ታሪክ በነጮች ፍጹማዊ የበላይነት ቁጥጥር ስር በመውደቅ ይቀየር  እንደነበር’’ በማያሻሙ ቃላት ገልጾታል።

በጋራ በመቆማችን እራሳችንን እኛ ኢትዮጵያውያን፣ ሌሎችን እነሱ ሌሎች የሚል የልዩነት መስመር በውል ያሰመርነው አድዋ ላይ በጋራ ተዋግተን በጋራ በማሸነፋችን መሆኑን በመግለጽ የዛሬ 123 አመት በፊት ቀደምቶቻችን ያሰመዘገቡትን ድል ታሪካዊ ትርጉም የታሪክ ጸሃፊው ሬይመንድ አሳምሮ ገልጾታል።

 በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የካቲት 23 1888 ታላቅ ትርጉም ያለው አመት ነው፡፡ ይህ ወቅት ኢትዮጵያ ራሷን ከጥቃት ተከላክላ እንደሃገር ክብሯን እና ነፃነቷን አስከብራ መቆም መቻሏን ያስመሰከረችበት ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ በአንድነት እና በጋራ የተሳተፈበት የሃገር እና የነፃነት መከላከል እርምጃ የተወሰደበት ወቅት ነው፡፡ 

(ከዛ በፊት የአንድ አካባቢ ህዝብ ብቻ ነበር የውጭ ጠላት የሚመከተው። ቀደም ብዬ የጠቀሰኩ የአጼ የኋንስ ድሎች፣ በዛው በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ ወገኖቻችን ብቻ በተሳተፉበት ሁኔታ የተገኘ ነበር።

 አፋሮች በስዊሱ ቅጥረኛው በቨርነር ሙዚንገር  ይመራ በነበረው የግብጽ የወራሪ ጦር ላይ ያስመዘገቡት ድል ሌላው ምሳሌ ነው። አፋሮች ብቻቸውን የተሳተፉበት ድል ነበር። የአፋሮችን የኢትጵያዊነት ሰነሰለት ያጠበቀው፣ እንኳን እኛ ግመላችን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላም ያውቃሉ በሚል ትምክህት የሚያናግራቸው የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሀገር በመከላከል ያደረጉትን አስተዋጸኦ ስለሚዘክሩት ነው። “እኛም ከውጭ ሁላችንንም ሊወር የመጣን ወራሪ ለወሬ ነጋሪ እንዳይቀር አድርገን ከ2000 በላይ የወራሪውን ወታደሮች ገድለናል” ከሚል የአፋሮች አኩሪ ታሪክ የሚመነጭ ነው። ሬይመንድ “ነጻነትን ከውጭ ወራሪ ለመከላከል የተከፈለ መስዋእትነት የዜጎችን የጋራ ሃገራዊ ህሊና በመፈጠር ከምንም ነገር በላይ አስተዋጸኦ አለው ለሚለው አባባሉ ከዚህ በላይ ማስረጃ አይገኝም  

የንጉሱን የጦር ጥሪ ሰምቶ ወደ አድው የተመመው ሰራዊት፣ በባዶ እግሩ፣ የራሱን መሳሪያ፣ ጦርና ጋሻውን፣ የራሱን ስንቅ ይዞ ነበር። አንዳንዱ ከሩቅ ቦታ ተነስቶ አድዋ ለመድረስ ለወራት በእግሩ ተጉዞ ነው። አድዋ ላይ ደርሶ ከጣሊያን ጋር ተዋግቶ ከቅኝ ገዥዎች ያተረፈው መሬት የትግሬ መሬት አይደለም፤ ያተረፈውም ሰው የትግራይን ሰው አይደለም። ከሸዋ የዘመተው ኦሮሞና አማራ፣ ከድቡብ የዘመተው ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ከምባታና ሃድያ አድዋ ላይ የወደቀው፣ ሰላሌን፣ መንዝን፣ ወላይታን፣ ሲዳማን፣ ከምባታና ሃድያን ለመከላከል አይደለም። ከሚኖርበት ቦታ በሽዎች ከሚቆጠር ኪሎ ሜትሮች ርቆ አጥንቱን የከሰከሰው ደሙን ያፈሰሰው የተወለደበትን መንደር ለመከላከል አይደለም። ኢትዮጵያ የሚባልን ሃገር እንደሃገር ለመከላከል ነው። ይህ አይነቱ መስዋእትነት ለረጅም ጊዜ ሳያባራ እሰከቅርቡ የባድመና የዛላ አንበሳ ጦርነት የዘለቀ ነው። ጋምቤላውና ሱማሌው  በባድመ ጦርነት በአንድ ላይ ወድቀው በአንድ ላይ ትግራይ ምድር ውስጥ የተቀበሩት፣ የእነሱ ልጆች ወደዛላምበሳ ለመሄድ፣ በዛላምበሳ ለመነገድ፣ ቤት ለመስራት፣ ቢፈልጉ ሃገራቸው ነውና ከልካይ አይኖርብንም ብለው በማመናቸው ነው።

አድዋ ላይ ወላይታውና ከምባታው ከአማራውና ከኦሮሞው ጋር ተያይዞ ደሙን ያፈሰሰበት እለት ነው፣ አድዋ፣ የትግሬዎች ግዛት መሆኗ ያበቃው፤

 የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የከምባታና የወላይታ የሚባል ምድር ያበቃው አድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን በጋራ ወደቀው በጋራ የሁሉም የሆነችውን ሃገራቸውን መከላከል የቻሉ እለት ነው።

“ኢትዮጵያን ሃገሬ ናት የትም ቦታ በነጻነት እንቀሳቀስባታለሁ፣ እሰፍርባታለሁና እኖርባታለሁ” የሚል ሃገራዊ እይታና ታሪካዊ መብት በደም የተገኘ የአድዋ ድል ውጤት ነው። 

“የኔ” የሚል የክልል አስተሳሰብ በዛ ፈታኝ ወቅት ኖሮ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የኔ የሚባል ነገር ማንም አይተርፈውም ነበር። ሁሉም የነጮች ይሆን ነበር።

ውደ ወገኖቼ!

ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እኛ ተሸንፈን ቢሆን ኖሮ እንደተቀረው አፍሪካ ጊዜ ጠብቀን ከቅኝ አገዛዝ ነጻ የምንወጣበት ዘመን አይመጣም ነበር። ሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ዘመን ጠብቀው ከቅኝ ገዥዎች ነጻ የውጡት እኛ በጋራ አድዋ ላይ ቆመን በማሸነፋችን ብቻ ነው። ያ ባይሆን ኖሮ ነጻ የሚወጣ አፍሪካ ሳይሆን የሚጠፋ አፍሪካ ነበር የታሪክ ውጤት ይሆን የነበረው። ስለዚህ ነው “ምኒሊክ ባያስገብሩን በሰለጥኑት ነጮች የቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ወድቀን፣ በምኒልክ ቅኝ ግዛት ስር በመውደቅ ከወረስነው ኋላቀርነት ተላቀን በነጮች ሰልጥነን ነጻ እንወጣ ነበር” ለሚሉ ለራሳቸው ክብር ለሌላቸው ወገኖቼ “መሰልጠኑ ቀርቶ እናንተም እኛም አንኖርም ነበር፣ ያ አይነቱ የይሆን ነበር ትረካ ከተረት ልዩነት የሌለው ነው” የምላቸው።

ወድ ወገኖቼ!

ይህ ንግግሬ ወደ ብዙሃኑ አድማጭ መድረሱ ስለማይቀር አጋጣሚውን ተጠቅሜ ከአድዋ ድል ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸውን የዘመናችን ጉዳዮችም እየነካሁ አልፋለሁ። ታሪክ ለዛሬ ህይወታቸን ፋይዳ ከሌለው ስለታሪክ ማውራት ብዙም የምጥመኝ ሰው አይደለሁምና፣ በጥሞና አድምጡኝ።

እንኳን በአድዋ ዘመን ከአድዋ በኋላም የኔ የሚል ነገር ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ፣ ኢትዮጵያ የሁላችንም ሃገር መሆኗ ያበቃላታል የሚል ትንሽ ጥርጣሬ ይኖራል ተብሎ ታስቦ ቢሆን ኖሮ፣ በዙሪያው የተንጣለለ መሬት ሞልቶ ከሚገባው በላይ በህዝብ ብዛት የተጨናነቀው ወላይታ፣ ከምባታ፣ ሃድያ፣ ጉራጌና ሌላውም የደቡብ ወገናችን የህዝቡን ብዛት የሚመጥን መሬት በጉልበት ለመያዝ የሞት ሽረት ትግል ያደርግ ነበር እንጂ የበሬ ግንባር የምታክል መሬት ይዞ “እርሻ አለኝ” ብሎ ሲባዝን አይገኝም ነበር።

“ኢትዮጵያ የሚባል ሃገር የጋራችን ነው” ብሎ ባያምን ኖሮ ከሰሜን ሸዋ ሜዳዎች በወረራ ተፈናቅሎ  በሰሜን ሸዋ ድንጋያማ ተራሮች ላይ እንደጦጣ ተንጠልጥሎ የሚኖረው የሰሜን ሸዋ አማራ በወረራ የለቀቃቸውን የጥንት መኖሪያቸውን በሙሉ ታሪክ እያጣቀሰ ለመውሰድ መደረግ የሚገባውን ሁሉ ያደርግ ነበር እንጂ እጅና እግሩን አጣጥፎ በረሃብ አያልቅም ነበር። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ እየኖረም ከመሬት ጋር በተያያዘ እንደዚህ አይነት ማለቂያ የሌለው ግጭት ውስጥ ሳይገባ ለረጅም ዘመን በሰላም የኖረበት ምክንያት ኢትዮጵያ የሚባል ሃገር የጋራችን ናት ብሎ በማመኑ ብቻ ነው።  ይህ ህዝብ ይህን የጋራ እመነት ያጣ እለት ምን ሊከተል እንደሚችል የኔ የሚል አባዜ የተጠናወታቸው የዘመኑ አርቆ አላሳቢዎች ካሁኑ ሊረዱት ይገባል።

በአዲስ አበባ ወስጥ የአማራው ቁጥር ለምን በዛ ለሚለው ጥያቄ መልሱን ማወቅ ለሚፈልጉ የሰሜን ሸዋን አማራ በሰፈረበት ገደላማ አካባቢ ሊሸከመው ያልቻለውን  የህዝብ ብዛት ማስተንፈሻ አዲስ አበባ ስለሆነች እንደሆነ መዘንጋት አይገባም። አዲስ አበባ ይህም የማስተንፈስ ሚና የምትጫውት ከተማ ባትሆን ኖሮ ከተለያዩ የህዝብ ብዛት ካለባቸው አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የመጣው ህዝብ አማራጩ ምን ይሆን ነበር የሚል ጥያቄ ማንሳት ብልህነት ነው።

የመሬት የቦታ ሽሚያና የኔ ብቻ የሚል የባላቤትነት ስሜትና እብሪት ወስጥ መግባታችን ወደሲኦል እየወሰደን እንደሆነ ፍንጮቹን አይተናል እያየንም ነው። የዚህ ችግር መፍትሄ መሬት እየመተሩ ይህ ያንተነው ይህ የእሱ ነው የሚል ሊሆን አይችልም። ያ መውጫ የሌለው የሙት መንገድ ነው። ሃገር የተሰራችው በሁሉም ስለሆነ ሁሉም የሃገሪቱ መሬትና ሃብት የሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች መሆኑ መቀበል ይጠይቃል። ይህ ችግር በጊዜ መፍትሄ ካልተሰጠው ሁሉንም የሚበላ የሲኦል እሳት በመላው ሃገሪቱ እንደሚያነድ ለመናገር ጠንቋይ መቀለብ ወይንም ነብይ መሆን አይጠይቅም።    

 “ወገኖቼ! ወደ አድዋ ስመለሰ፣ በዛን ወቅት ምኒልክ አንድ ባያደርገን የዛሬው ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ከምባታ፣ ሃድያ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላና ወዘተ ቀርቶ አፍሪካ ራሷም አትኖርም ነበር። እንደ አውስትራሊያ የነጮች መፈንጫ ትሆን ነበር።” እላችኋለሁ

አዚህ ላይ ብዙዎቻችሁ ልታነሱት የምትፈልጉት ጥያቄ እንዳለ ይገባኛል። እንዴት  በሁሉም አቅጣጫ በመሳሪያ እንዲገብር የተደረገ ህዝብ፣  በተለይ ሃገሪቱ ችግር ላይ በወደቀችበት ወቅት አለምን ባስገረመ ደረጃ ለምኒሊክ የክተት ጥሪ ምላሽ መስጠት ቻለ? ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው። የዛሬ ጠባብ ብሄረተኞች እንደሚሉት ቢሆን ኖሮ የጣሊያንን ወረራ ሰበብ አድርጎ ሁሉም በየአቅጣጫው በንጉሱ ላይ በሸፈተ ነበር። ያ አልሆነም። ምክንያቱ ቀላል ነው።

የዛን ዘመን መሳፍንት፣ መኳንንትና ባላባቶች ከዛሬው ገድላቸውንና መስዋእትነታቸውን አሳንሶ ከሚያየው ከሃዲ ልጃቸው በላይ ብልህና አርቆ አሳቢዎች ነበሩ። በዘመኑ የተረዱት ሃቅ ነበር። ያ ሃቅ ነጮች እያጠመዱላቸው የነበረው ወጥመድና አሰከፊ መዘዙ ነበር። መጥፊያቸው ተቃርቦ እንደነበር ፍንትው ብሎ ታይቷቸው ነበር። በዚህ ላይ ብልሃትና ጥበብ የተሞላበትን የምኒሊክ አመራርና ሌሎችንም ነገሮች መጨመር ይቻላል።

(ከላይ ላነሳሁት ለምን ለሚለው ጥያቄ ዝርዝር ምላሽ የሚፈልግ “ነጻነትን የማያውቅ ነጻ አውጭ” የሚለውን መጽሃፌን የመጀመሪያውን ምእራፍ ማንበብ ይችላል። )

የሚቀጥለው የንግግሬ ክፍል የሚያተኩረው በአድዋ ድል የተነሳ በኢትዮጵያውያን የጋራ መስዋእትነት ተጠናክሮ የወጣው ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛነት በሂደት የገጠሙትን ችግሮች ነው።  

ቅድመ አድዋንና  ራሱን አድዋን መነሻው ያደረገው ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት፣ ፖለቲካዊ መሠረቱ፣ ከአመት ወደ አመት እየተዳከመ የሚሄድ የመሳፍንት እና የባላባት ሥልጣን፣ በእዚያው መጠን ከአመት ወደ አመት የሚጠናከር የማዕከላዊ መንግሥት ስልጣን ነበር፡፡ የእዚህ የማእከላዊ መንግሥት ቁንጮ ነገስታቶቹ ሆነው ስልጣናቸውንም የሚተገብሩት በቀጥታ በሚያዙት የጦር ኃይል እና በሂደት እየተጠናከረ በመጣው የመንግሥት ቢሮክራሲ አማካይነት ነበር፡፡

ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረቱ፣ ከባሪያ ጉልበት አንስቶ በገባርና በጭሰኛ ጀርባ ላይ የቆመ የጉልት እና የባላባት ስርአተ-ማኅበር ነበር፡፡

ይህ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛነት እጅግ ኋላ በቀረ የኢኮኖሚና ማህበራዊ መሰረት ላይ መቆሙ የታወቀ ነው። በዚህ የተነሳ የተሟላ እንከን የለሽ ብሄረተኛነት አልሆነም። የየትኛውም ሃገር ብሄረተኛነት ተመሳሳይ ችግሮች ተጣብተውት የጀመረ ቢሆንም የኛ ችግር በእኛው የተለዩ ሁኔታዎች እንከን የለሸ ጉዞው በድልና ፈተና የተሞላ ሆኗል ።

የኛ ሃገራዊ ብሄረተኛነት ከአውሮፓውያኑና ከአሜሪካኖች ጋር ሲወዳደር በጣም በብዙ ነገሮች ወደኋላ በቀረ ሃገር ላይ የተተከለ በመሆኑ ፈተናዎቹ የበዙ ሆነዋል። ፈተናዎቹን ለማለፍ ተቸግረን እየተንደፋደፍን ነው።  የሰሞኑ አዲስ አበባ የማናት፣ ከወልቃይት ጠገዴ፣ ከራያና ከመተከል እንዲሁም ከሌሎች ተመሳሳይ ከሆኑ በመላው ሃገሪቱ ከሚታዩ “የመሬት ይገባኛል” ጉዳዮች ጋር የገባንበት ችግር የመንደፋደፉ ምሳሌዎች ናቸው።

ይህ መንደፋደፍ የተወሳሰበ መነሻ ያለው መሆኑን ለማስረዳት ታሪካችንን ትንሽ ሰፋ አድርጌ ማቅረብ እሻለሁ። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት ይችላል። እዚህ የማነሳው ጠባብ ብሄረተኞች ቢሰሙት ደስ የሚላቸውን ብቻ ነው። ይህን የምለው ታሪክን እነሱ ማንሳት ከሚፈልጉት በላይ በከፋ መልኩ ማንሳት እንደምንችል እንዲያዩት ነው። ታሪኩ የእነሱ ብቻ ሳይሆን የኛም ታሪክ እንደሆነና እንደማንደብቀው እንዲያውቁት ነው።  በዚህ አስከፊ በሆነ ደረጃ ታሪካችንን አይተንም መጨረሻ መደምደሚያችን ግን የአድዋን ድል ታላቅነት የሚያስረገጥ ነው።  

ፊት ለፊት ላስቀምጠው።

እኛ የአድዋን ድል በጣሊያን ላይ ስንቀዳጅ አድዋ ድረስ ጌቶቻቸውን ተከትለው የሄዱ፤  በጦር ሜዳው ቀላል የማይባሉ አገልግሎት የሰጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ባሮች ነበሩ።

በዛሬው ቀን እነዚህን እናስታውሳቸዋለን።

ከነዚህ መሃል የአንዷን ስም ጠቅሼ ከአባት፣ ከእናቴና ከልጆቼና ከባለቤቴ ስሞች ጋር አዲስ በሚወጣው “እኛም እንናገር ትውልድ አይደናገር” በሚለው መጽሃፌ ላይ እሷን በስሟ ያወቅኋትንንና በስማቸው ለማይታውቁ  ሌሎች ባሮች በማስታወሻነት ሰጥቸዋለሁ።

እንዲህ ይላል፤ ማታወሻነቱ

“እንዲሁም ለእንኮዬ ወለተማሪያም ልጅ፣ ለወለተአማኑኤልና ለሌሎችም፣ ስቃያችሁና መስዋእትነታችሁ ላልተተረከው፣ ሃውልት ላልቆመላችሁ፣ የኩራታችንና የነጻነታችን ቤዛ ለሆናችሁት የአድዋ ድል እመቤቶች፣ የሃገራችን  የሴት ባሪያዎች በሙሉ!

ትጠይቁኝ ይሆናል። “ወለተአማኑኤልን ከየት አገኘሃት” ብላችሁ!

ወለተማሪያም ማን ነበረች? ፊታውራሪ ተክለ ሃዋርያት ተክለ ማሪያም፣ “የህይወቴ ታሪክ” በሚለው መጽሃፋቸው ይችን የአባት ስም የሌላትን እንደማንኛውም ባሪያ በእናቷ ስም የምትታወቀው፣ “ወለተ አማኔል ”  እንዲህ ብለው ይገልጿታል።  “ላብዩ (ለፊታውራሪ ተክለ ሃዋርያት ወንድም)፣ ከራስ መኮንን ጋር አድዋ ሲዘምት፣ ሰራዊቱ ከሃረር  ተነስቶ ሸዋ ላይ “ሳያደብር” ከሚባለው አካባቢ ባረፈበት ወቅት፣ ከጭነት አጋሰስ ጋር ከአጎቱ የተሰጠች “የቤት ውልድ” ባሪያ ነች።

ፊታውራሪ ስራዋን ሲገልጹት ደግሞ እንዲ ብለዋል።

“የቤት ውልዷ ወለተ አማኔል፤ የእንኮዬ ወለተ ማሪያም ልጅ፣ ከእኛው ጋር ያደገች ነች።  የአድዋ ጦርነት ዘመቻ ላይ በጣም አገለገለች፤ ከቶ  እሷ ባትኖር እንዴት እሆን ኖሯል፣ እያልኩ ሳስበው ይደንቀኛል። እቃ ተሸክማ ስትሄድ ትውላለች፤ ከሰፈርን በኋላ ውሃ  ቀድታ፣ እንጨት ለቅማ፣ ቂጣ ጋግራ፣ ወጥ ሰርታ ታበላናለች። ወዲያው እንደዚሁ ለማታ ታሰናዳለች። እንደዚህ የወለተ አማኔልን አገልግሎት እያሰብኩ ስደነቅ ደግሞ፣ በየሰፈሩ እንደዚህ እንደርሷ ስንት ሴቶች እንደሚያገለግሉ ይታሰበኛል።

የሴቶቹን (የባሪያዎቹን) አገልግሎት ስገምት፣ ደግሞ የበቅሎች አገልግሎት ይታወሰኛል። በመጨረሻው ድምሩን ስገምተው፣ የአድዋ ድል የተገኘው በሴቶች አገልጋዮችና (ባሪያዎችና) በበቅሎች ብርታት መሆኑ ይታወቀኛል። ሁሉንም አያይዤ በደምሳሳነት ስመለከተው፣ የኢትዮጵያን መንግስት ነጻነቱን ጠብቀው፣ እዚህ አሁን አለንበት ኑሮ ላይ ያደረሱት፣ እነዚህ የዘመቻ ሃይሎች መሆናቸውን አልስተውም” ብለዋል።

የባርነት ጉዳይ ጣሊያንን አድዋ ላይ ከአሸነፍነው ከ40 አምት በኋላም ከኢትዮጵያ አልጠፋም። በተጨባጭ መረጃ አስደግፎ ማቅረብ የሚቻል ሃቅ ነው።

በዚህ የአድዋ መታሰቢያ ቀን የተለየ ማስታወሻ የምናደርግላቸው ሌሎች ወገኖቻችን ከወሎ ከዘመቱ 70000 ፈረሰኞች መሃል የነበሩ የእስልምና እምነት ተከታይ ተዋጊዎችን ነው። እነዚህን በተመለከተ የአድዋ ውጊያ መጽሃፍ ጸሃፊው ጆናስ ሬይመንድ ያለውን ስንሰማ ለምን በተለየ ልናስታውሳቸው እንደሚገባን እንረዳለን። የራሴን አስተያየት ጨምሬ እንደሚቀጥለው ጨምቄ አቅርቤዋሁ። ’

ስለ አድዋ ሲነሳ ብዙዎቻችን የምንስማማበት ጉዳይ ይኖራል። አድዋ ትልቅ ድል ነው። ቀደምቶቻችን ባገኙት ድል እኛ ብቻ ሳንሆን የጥቁር ዘር በሙሉ ኮርቶበታል። የአድዋ ታሪክ ግን ሲተረክ ምን ያህል መረጃ እየጠለለ እንደ ተተረከልን ከዚህ የታሪክ  መምህር ከሬይመንድ መፅሃፍ ማየት ችያለሁ።

በአድዋ ጦርነት ስለተሳተፉ የኦሮሞ ፈረሰኞች ብዙ ሰምተናል። ምን ያህል ወሳኝ ሚና እንደነበራቸውም ተተርኳል። ስለእምነታቸውግን የተጻፈ ነገር አላየሁም። ጊዮርጊስ ከነታቦቱ አድዋ መሄዱን ሰምተናል። የጣልያንን ወታደር አሳደው መውጫ መግቢያ ስላሳጡት፣ የፍራቻና የድንጋጤው መንስኤ ስለነበሩት የእስልምና  ዕምነት ተከታይ ኦሮሞዎች ታሪክ አለመስማታችን የሚገርም ነው። ይህ አነስተኛ አግራሞት ሊጭርብን ይችላል። ሌላው ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘው የታሪክ ጭብጥ የአግራሞት ብቻ ሳይሆን የሃዘንም ምንጭ ሆኖብኛል።

ጦርነቱ በድል ከተጠናቀቀ በኋላ ትልቁ ስራ በጦር ሜዳ የተሰውትን እየሰበሰቡ በስነሥርዓት መቅበር ነበር። አገር ሊወሩ የመጡ የጣሊያን ወታደሮችም አስከሬን ከጣሊያን ወታደራዊ መሪዎች ጋር በተደረገ ስምምነት ጣሊያኖቹ እንዲቀብሯቸው ተደርጓል።ሌሎችም ኢትዮጵያውያን በሚያረካ መንገድ ባይሆንም እንደነገሩ በዘመኑ ሥርዓት ተቀብረዋል። በእምነታቸው የተነሳ አጥንታቸው ሰብሳቢ ያጣው በየወደቁበት ያለቀባሪ የቀሩት የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ብቻ እንደነበሩ ይህ ጸሃፊ በመጽሃፉ ገልጾታል።

እስከ ዛሬ ስለ አድዋ ድል ሲነገረን፣ ደማቸውን አፍሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ነጻነታችንን ለማስጠበቅ የወደቁ የሙስሊም ቀደምቶቻችን አስከሬን፣ በእምነታቸው የተነሳ ቀባሪ እንዳጣ አናውቅም ነበር። በተለይ በአድዋ ተራሮች ላይ ሌላው ሁሉ ቀባሪ ሲመደብለት፣ ከጅብና ከጥንብ አንሳ  የተረፈው የሙስሊም ጀግኖቻችን አጥንት በአድዋ ተራራ ላይ ተበትኖ ቀርቷል።

ከክርስትና ዕምነት ተከታዮች ቤተሰብ የተገኘሁ ብሆንም በአድዋ ተራሮች ላይ ያለ ቀባሪ ተበትኖ  የቀረው የሙስሊሞችም አጥንት የአያቶቼና የቅድመ- አያቶቼ አጥንት እንደሆነ አድርጌ እንዳላይ አልከለከለኝም። የሃገሬን የእስልምና ዕምነት ተከታዮች አሳዛኝ ታሪክ ስለማውቅ፣ ይህን አዲስ የታሪክ ጭብጥ ሳነብ ሃዘኔን የበረታ አድርጎታል። አሳዛኝ ታሪክ ያልኩት ደርግ ስልጣን ይዞ የሃይማኖት እኩልነት እሳካወጀበት ድረስ የሃገራችን ሙስሊሞች በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ፣ ከንግድ እንቅስቃሴ ውጭ በየትኛዎቹም ወሳኝ የሃገሪቱ ህይወት የመሳተፍ እድል የማይሰጣቸው ነበሩ። አድዋ ላይ ግን እንደ ክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጣሊያንን ድባቅ በመምታት የዜግነት ምባቸውን ከፍለዋል።

ግን ልብ እንበል። ሃገርን ሃገር የሚያደርጋት ከዘር ከቋንቋና ከእምነት በላይ ዜጎቿ በጋራ ለነጻነታቸው የከፈሉት መስዋእትነት ነው የሚለወን የሬይመንድ አባባል እዚህም ላይ ማስታወሱ ተገቢ ነው። አፋሮችም ሆኑ የወሎ ሙስሊሞች ለኢትዮጵያ ቀናኢ ሆነው የቀሩት ለዚች ሃገር ነጻነት ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር በከፈሉት መስዋእትነት እንጂ ሁሉ ነገር ተሟላቶላቸው አይደለም።    

የአድዋ ጦርነትና ከዛም የቀጠለው ታሪካችን እጅግ አስከፊ የሆነ የአብዛኛው ህዝብ የገባርነትና የጢሰኛነት ህይወት ላይ የተመሰረተ ነበር። ይህ የጢሰኛ ህይወት የአጼ ሃይለስላሴን የአጎት ልጅ ራስ እምሩን ሳይቀር ያሰቀቀ ነበር። ከሰማሁትና ከየሁት በሚለው የግል ህይወት ማስታወሻቸው ላይ ግብርን በተመለከተ የሃረር የግብር አይነትን ዋቢ አድርገው የጻፉትን እንይ።

 1. የወር ግብር –
 • በገባር የማገዶ እንጨት ውፍረቱና ቁመቱ በ3 ክንድ ተለክቶ፣ በገንዘብ አራት መሃለቅ
 • በገባር 2 ቁና እህል መፍጨት፣  በገንዘብ ሁለት መሃለቅ
 • ሁለት ገባር አንድ በቅሎ ያበላል፣ በገንዘብ በገባር 15 መሃለቅ
 1. የበአላት ግብር – ለገና  ለፋሲካና  ለመስቀል በየበአሉ
 • በአምስት ገባር በላይ ያለው በገራዳ ወይም በመላቃ ለፍየል መግዣ 2 ብር
 • ከአምስት ገባር በታች ገራዳን መላቃ 1 ብር
 • በገባር አንድ ቀረዋ (ሁለት ቁና ጌሾ) ሰባት መሃለቅ በቀረዋ (በጥቅሉ 4 ቁና ወይም 14 መሃለቅ
 1. የአመት ግብር
 • በገባር አንድ ልክ ወይም 4 ሊትር ማር በገንዘብ 4 ብር
 • በገባር ሁዳድ የማያርሰው የእህል ቀለብ 24 ቁና እህል በገንዘብ 6 ብር
 • ሁዳድ የሚያርስ ሲሶ
 • ቀን ተቆጥሮ በጉልበት የሚያርስ ቀለብ አይከፍልም
 • ያረፋ በአል 1ብር ከአራት መሃለቅ (በግብጾች ዘመን የነበረ ወደ መንግስት የሚገባ)
 • አስራት እህል ተሰፍሮ ከአስር አንዱን
 • ስለ ሁዳድ በገባር 4 ቁና
 • ባውድማ እንቋ ሁለት ቁና በገባር
 • ስለ ቀላድ ግቢ በገባር 2 ቁና
 • ሶ ስት ጊዜ በአመት የሶስት ቀን መንገድ በጠቅላላው የ9 ቀን መንገድ መላላክ የሚጫን ካለ መጫን አለበት
 1. በ3 4 እና 5 አመት
 • ሹም ሽር ለገቢው ተሿሚ በአምስት ገባር በላይ ያለው በገራዳ ወይም በመላቃ 4ብር
 • ከአምስት ገባር በታች ገራዳን መላቃ 2 ብር ለተሿሚ
 • ዘመቻ ከአካባቢው ወታደሩ ወጥቶ የሚሄድ ከሆነ፣ የወደል ጋዝ ግብር ለመልከኛው የከብት መግዣ በገባር 7 ብር
 • የከተማ ቤት ይሰራል አጥር ያጥራል ያረጀ ያድሳል

በየወሩ የሚከፍለው ባላገሩን የጎዳው መስፈሪያው እያደገ እየታመቀ  የሚሰፈረው ጭቅጭቅና  ጉቦ  ነው” ይሉናል ልኡሉ። ይህ ግብር በዛን የጨለማ ዘመንም እንኳን ከልክ ያለፈ መሆኑ የሚስተው ይኖር ይሆን ? አይመስለኝም።

በዚህ ላይ በሃረር ውስጥ ቀላል ቁጥር ያልነበረው ባሪያ እንደነበር መዘንጋት አይገባንም። 40 አመት አድብቶ የአድዋ የሽንፈት ቁስሉን ሲያክ ከርሞ የመጣው ሌላው ዙር ወራሪ የጣሊያን ጦር ቅስቀሳም “ከገባርነትና  ባርነት ነጻ  ላወጣህ የመጣሁ የፈጠሪ ወኪል ነኝ” የሚል እንደነበር አይዘነጋም።

ወደ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ስንሄድ ተመሳሳይ ችግር እናያለን።

አርብቶ አደሩ ላይ ይደርስ የነበረው ስቃይም ከሌሎቹ ያልተናነሰ ነበር

ፊታውራሪ ተክለ ሃዋርያት ተክለ ማሪያም፣ “የህይወቴ ታሪክ” በሚለው መጻሃፋቸው ይህን አስፍረዋል። በ1920ዎቹ ውስጥ ወደ አፋር ግዛት አርብቶአደሮችን ለማስገበርና ለመቅጣት እንደተንቀሳቀሱ በመናገር በቅጣት ስም ከአንድ ባላባት ስር ከነበረ አንድ አነስተኛ ጎሳ ብቻ “አርባ ሺህ ፍየል፣ አስር ሺህ ጊደርና ላም፣ ሶስት ሺህ ግመሎች” እንደወሰዱባቸው ይናገራሉ።

አፋሮች ይህን ያህል ከብት ተወስዶባቸው ምን ተረፋቸው የሚያሰኝ ነው። በአፋሮች ላይ ይደርስ የነበረው ግፍና በደል ብዙ ነበር። ይህን የበደል ታሪክና የአፋሮችን ኢትዮጵያዊ ቀናኢነት አንድ ላይ ማጤኑ መልካም ነው።

ይህ የአድዋ ድል በዋንኛነት የፈጠረው ብሄረተኛነት ቀደም ብዬ እንደገለጽኩ ልክ እንደኛው ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ካለፉ ሃገሮች ብሄረተኛት ጋር ተመሳሳይነት አለው። አሜሪካኖች ለነጻነታቸው ከእንግሊዞች ጋር ሲዋጉ በሁለቱም ወገን በባርነት ይገዟቸው የነበረውን አፍሪካውያንን በውጊያ አሳትፈው ነው።

ዊሊያም ጀፈርሰን የመሰለ የአሜሪካ የዴሞክራሲ አባት እየተባለ በታሪክ የሚወደሰው ፕሬዚደንት የባሪያ ገዥ ነበር። አሜሪካ ለጥቁሮች የተሟላ መብት የሰጠችው የዛሬ 54 አማት ገደማ ነው። የእንግሊዝ ብሄረተኛነት ለማመን ከሚቸግር የባላገር መፈናቀልና እጅግ አሰቃቂ በሆነ ህይወት በፋብሪካዎች ተቀጥሮ በሚኖር የፋብሪካ ሰራተኛ ስቃይ ላይ የቆመ ነበር ። የጀርመን የጣሊያን የፈረንሳይ ነገስታት የዛሬ  ዜጎቻቸው ቀደምቶች የሚኖሩባቸውን የተበጣጠሱ ግዛቶች በእሳትና በብረት ቀጥቅጠው ነው ሃገር የመሰረቱት። ሁሉም ሃገራዊ ብሄረተኛነት መነሻው እልቂት፣ ጦርነት፣ መጋዝ፣ መዘረፍ ደምና መግል ጋር የተያያዘ ነው። ስፋት ያለውን የማህበረሰባችንን ክፍል ህይወት ከሆነ የምናየው የኛም ከሌሎች የተለየ አልነበረም። ጠብብ ስናደርገው ግን በጦርነት ተማርከው በባርነት ቀንበር ወስጥ የወደቁ ግለስቦች ሳይቀሩ ችሎታው ካላቸው የሀገር ሚኒስቴር፣ የጦር መሪ፣ ከነገስታት ልጆች የሚዳርላቸው፣ ንጉስ መፍጠርና ማፍረስ የሚያስችል የግል ሰራዊት እንዲኖራቸው እድሉ ክፍት የሆነበት ሃገር ኢትዮጵያ ብቻ እንደነበረች መዘንጋት አያስፈልግም። ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የዚህ ሃቅ እውነተኛ ምሳሌ ናቸው። የአንድ አካባቢ ህዝብ በጦርነት እየተሸናነፈ በባርነት የወደቀበት ሂደትና በነጮች ወራሪዎች እጅ በቀለም ልዩነት ላይ በተመሰረተ የወረራ ሂደት ባሪያ መሆን ያላቸውን ልዩነት ለመረዳት ለማይፈጉ ወገኖቼ ማሳሳሰቢያ እንዲሆን ነው ይህን የጠቀስኩት።

ወደ ቁም ነገሩ ስመለስ፣

አሜሪካኖች እየመሰረቱት የነበረው ሃገር ችግር ያለበት መሆኑ በመረዳት  የዛሬ 200 አመት በፊት የአሜሪካ ህገ መንግስት አርቃቂዎች በህገ መንግስቱ መግቢያ ላይ ያሰፈሩት የህገ መንግስቱን አላማ ከሚገልጹት ስንኞች አንዱ አሜሪካንን  “to a more perfect union ወደ እንከን የለሽ አንድነት ለመውሰድ ነው” ይላል። ከ200 መቶ አመት በኋላ፣ ስንት መከራ ካለፉ አፍሪካዊ አሜሪካን ወገኖቻችን መሃል አንዱ ባራክ ኦባማ፣ በምርጫ አሸንፎ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆኖ ሲመረጥ ለአሜሪካ ህዝብ ፔንሰልቫኒያ ላይ ያደረገው ንግግር፣ ቀደም ብዬ የጠቀስኩትን በአሜሪካ ህገ መንግስት መግቢያ ላይ የተጻፈውን “ወደ እንከን የለሽ አንድነት” ( a more perfect union ) የሚለወን ስንኝ  በርእስነት ተጠቅሞበታል።

 እኛ በምኒሊክ ዘመን የወጣ ህገ መንግስት አልነበረንም። በአጼ ሃይለ/ስላሴ ዘመን የወጣው ህገ መንግስትም ሃገሪቱ ችግር እንዳለባት በመገንዘብ “እሱን ለማቃለል ነው” የሚል ሰንኝ የለበትም። ግን ታሪካችንን በደንብ ካጠናነው እኛም ያላወጅነው ወደ እንክን የለሸ አንድነት እየወሰደን የነበረ ታሪክ ጉዞ ጀምረን ነበር። አድዋን መሰረቱ ያደረገው ብሄረተኛነት በአብዛኛው በአዝጋሚ ሂደት፣ በጥቂቱ ደገሞ በስር ነቀል አብዮት እየተደገፈ ወደተሟላ አንድነት እየሄደ ነበር።

ባርነትን በተመለከተ አጼ ምኒሊክ ከመሳፍንቱና ከባላባቱ ቀድመው ባሪያ መግዛትና መሸጥን በተመለከተ አዋጅ አስነግረዋል። እራሳቸውም እጅጋየሁ ከምትባል የቤት አገልጋይ መወለዳቸውን አንርሳ። በዛን ዘመን የቤት አገልጋይ የሚል ስም ለነማን እንደሚሰጥ መመርመር ተገቢ ነው። ኦሮሞ እንደነበረችም አንዘንጋ።

ከአንድ ሚሊዬን በላይ ኦሮሞችን በባርነት ለሸጠው ዛሬ በስሙ “አባጅፋር” የሚል የእግር ኳስ ቡድን የዘመኑ ኦሮሞዎች ያቆሙለት የአረብ ዝርያ፣ “ይህን ባሪያ መሸጥክን ካላቆምክ ማሪያም ምስክሬ ናት አይቀጡ ቅጣት እቀጣሃለሁ” የሚል መልእከት፣ የዛሬዎቹ የሃጋራቸን  ጠብብ ብሄረተኞች የቅኝ ገዥ አድርገው ከሚስሏቸው ከታላቁ ንጉስ ከምኒሊክ ተላላፎ ነበር።  

አጼ ሃይሰላሴም ዘርማንዘራቸው ሲመረመር ኦሮሞነት የሚያይልባቸው ንጉስ ነበሩ። ብሄረተኛነታቸው ግን ኢትዮጵያዊ ነበር። ሌላ አይነት ብሄረተኛነት እከተላለሁ ብለው ሞክራው ቢሆን ኖሮ ሃገር ይፈርስ ነበር እንጂ አይሳካላቸውም ነበር። አማርኛ ቋንቋ የሃገሪቱ ቋንቋ በመሆኑ የአጼ ሃይለስላሴንና ሌሎችንም መንግስታት የአማራ ብሄርተኞች አድርጎ የሚያቀርበው እይታ እፍ ቢሉት ብን የሚል የእውቀት ገለባ ላይ የቆመ መሆኑ ለማሳየት አዳጋች አይደለም። ባላፈው 27 አመት አማርኛ የሃገሪቱ ኦፊሳሊያዊ ቋንቋ ሆኖ ቀጥሏል። ባለፈው 27 አመት የነበረው የበላይነት የአማራ ነበር የሚል እብድ ብቻ ነው።  ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ስማቸውን ወደ ግእዝ ስም እንዲቀይሩ ሳይገደዱ (ስም መቀየር ግዴታ ነው የሚል ተደጋጋሚ ክስ ከዘውጌ ብሄረተኞች ስለሚሰማ ነው የጠቀስኩት) በአጼ ሃይለስላሴ መንግስት ወስጥ ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው ሰው ነበሩ።  በቅርቡ ስለ ንጉሰነገስቱ መንግስት ዘረኛ አለመሆን የሰጡት ምስክርነት በሃገራችን ታሪክና ተረት እየተምታታ እንደሆነ በቂ ማስረጃ ነው። ክቡር አቶ ቡልቻ እንደነገሩን አጼ ሃይለስላሴ ችሎታህን እንጂ ዘርህን አይመከቱም። ብቃት አለው ብለው ካመኑ በየትኛውም ስልጣን ላይ ይመድቡሃል” ብለዋል።

 አጼ ሃይለ ስላሴ ባርነትን ለማስቀረት ከማሳፍንቱ፣ መኳንንቱና ባላባቱ ጋር ታግለዋል።፣ እነዚህ ነገስታት በመሰረታዊ ባህሪያቸው የተነሳ ያላቃለሏቸውን ችግሮች እንዲቃለሉ የኢትዮጵያ ምሁራን በዘርና በእምነት ሳይለያዩ በአንድነት ትግል አድርገዋል መስዋእትነት ከፍለዋል። ገባርነትና ጢሰኛነት እንዲያበቃ የሁሉም ዘር ተማሪዎችና ወጣት ምሁራን በተለይ ደግሞ በዛሬው የዘር መነጽር ቢመረመሩ አማራ ሊባሉ የሚችሉ በርካታ ተማሪዎችና ምሁራን ከማንም የላቀ መስዋእትነት ከፈለዋል።

በመጨረሻም ደርግ ጭሰኛነት የሚያስቀር አዋጅ አወጣ።  የቋንቋ፣ የባህል፣ የእምነቶች ጉዳይ አስከፊ ከሆነ አድሎኛነት ወደ እኩልነት የሚወስደውን መንገድ ጀምረው ነበር። ደርግን በብዙ ነገር ልናወግዘው ብንፈልግም የሃገሪቱ የተለያዩ ማህበረሰቦች የቋንቋ የባህል የእምነት እኩልነት እንዲኖራቸው ስር ነቀል እርምጃዎች ወስዷል። እንደሌሎቹ መንግስታት እሱም ከባህርይው ተነስቶ የኢትዮጵያን ብሄረተኛነት እንከን የለሽ ደረጃ ላይ ማድረስ አልቻለም። የደርግ መንግስታዊ ስርአት ከየትኛውም ዘመን በተሻለ በሲቪሉም ሆነ በወታደራዊ ተቋሞቹ ውስጥ ብዙሃኑን የሃገሪቱን የዘውግ ስብጥር ያቀፈ ተቋማት መስርቶ ነበር። ሌሎቹንም ነገስታት በዚህ ብዙ ማማት አይቻልም። እንዳልኩት አዝጋሚ እርምጃዎችና አብዮታዊ እርምጃዎች የጠይቁ ቢሆኑም ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛነትና ኢትዮጵያዊ አንድነት እንከን የለሽ ጉዞውን ጀምሮ ነበር። ወደ እዛ እየተጓዝን ነበር።

አዎ ነበር። የወያኔ ዘመን ይህን የሃገሪቱን ህዝብ እንደሙጫ ያስተሳሰረውን ብቸኛ ሃገራዊ እሴት ላይ ዘመተበት። የጎደሉት ምንድናቸው እንደማለትና የጎደሉትን እንደማሟላት እንዳለ ሃገራዊ ብሄረተኛነት መናድ ተያያዘ። በመከራ ለመቶ አመታት የተገነቡ ሃገራዊ ተቋማትን አወደመ። ሌሎችም ጠባብ ብሄረተኞች የወያኔ ሚዜ በመሆን ያንን የአለም የጥቁር ዘር የኮራበትን እኛንም ከነጮች ባርነት ያዳነን ሃገራዊ ብሄረተኛነት ለማዳከም ምኒሊክን ከቅኝ ወራሪ ጎራ የሚደርብ ትረካ ቀረበ። ምን ያህል ታሪካዊ ሃቅ ላይ የተመስረተ ነው የሚል ጥያቄ ግን እንዲቀርብ፣ ስልጣኑን በጠመንጃ ሃይል የተቆጣጥሩትና ሚድያውን በሞኖፖል የያዙት ሃይሎች አልፈቀዱም።

በሃገር ምስረታ ወቅት የተደረጉ ጦርነቶችን በዛን ውቅት ሌላ አማራጭ የነበረ ይምስል  ትልቅ ስቃይ ያደረሱ መሆናቸው የሚተርከው ትርክት ዋናው የታሪካችን ቋሚ ትረካ ሆነ። የራስን የሃገር ክህደት ታሪክ፣ የራስን ጭካኔ ለመደበቅ የተፈበረኩ የሌሎች ጭካኔ የሚያሳዩ ድርሰቶች ተጻፉ። የጭካኔ ሃውልቶች ቆሙ። ሌላው ለዚህ ትርክት በሃቅ ላይ የቆመ ምላሽ መስጠት ሲችል

 (በሃገር ወስጥ ወረራ ማ ማንን አፈናቀለ? ማ የት ነበረ ዛሬ የትነው ያለው? በአድዋ ሆነ በማይጨው ከዛም በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ ደሙን ባፈሰሰባቸውና አጥንቱን በከሰከሰባቸው የሃገር መከላከል ጦርነቶች ማን ከየት ተንስቶ የት ወደቀ፣ ማን ደግሞ ለውጭ ወራሪዎች መንገድ መሪ፣ እንቁላል አቀባይ፣ ወዶ ገባ ተዋጊ ሆኖ ከወጭ ወራሪዎች ጋር ወግኖ ወጋው? መሬት ላይ እያጋደመ  ህጻናቱንና ሴቶችን እንደከብት አረደ? ማን የአርበኞችን ብልት ሰለበ?)  

አለመስጠቱ  ሌላው የሚለው ነገር የሌለው የመሰላቸው ብልጣብልጦች ይህንን እኩይ ትረካ አሁንም አጠናክረው እየቀጠሉበት ነው። በዛን የጨለማ ዘመን የነበረው አማራጭ ምን ነበር? የእናንተ ንጉስ ወይም መስፍን ወይም ባላባት ስልጣን ይዞ ቢሆን ሰብአዊ መብት ያስከብር ነበር? ዴሞክራሲ ያሰፍን ነበር? የምርጫ ሳጥን እያዞረ ትልቅ ሃገር ለመፍጠር ስለምፈልግ አባል ለመሆን የምትፈልጉ ድምጽ ስጡ ይል ነበር። ለነዚህ ጥያቄዎች አዎን የሚል መልስ የሚሰጥ ደፋር እንደማይኖር እናውቃለን።  

የዛን ዘመን መንገድ አመጽ ብቻ መሆኑን ከተማመንን፣ ታሪካችን አስከፊ መሆኑን ከተስማማን፣ የጎደሉን ብዙ ነገሮች እንዳሉን ከተግባባን፣ እና ከዛ በኋላስ። ስላለፈው እናልቅስ፣ በታሪክ እስርቤት ወስጥ ታስረን ክስ ስንወራውር ዛሬ ሃገርና ህዝብ የጎደላቸውን በርካታ ነገሮች ሳናሟላ ለነገ ትውልድ መከራና ችግር እናውርስ?  በዚህ ጓዳይ ላይ ከምሩ የሚያስብ ጠፍቷል።

ውሎ አድሮ የደረስንበት አዘቅት ኢትዮጵያን፣ ዜጎቻ በመራራ ጦርነትና ትግል፣ በየግላቸው መሳሪያ፣ ስንቅና መጓጓዣ ሃገር አድርገው እንዳልፈጠሯት ሁሉ የብሄር ብሄረሰቦች የውልና የስምምነት ውጤት ሆና ቀረበች።

ይህ ትረካ ለ27 አመት በመንግስት ተሰበከ እና በሲስተም ደረጃ ተተከለ።

ይህ ስብከት መጨረሻው ሁሉንም የሃገሪቱን ዜጎች ከሲኦል አፋፍ ላይ አድርሶ አስቀምጦ ነበር። ለግዜው ከአፋፉ ላይ የተመለስን ቢመስልም ወደ አፋፉ የማንመልስበት እድል ዝግ አይደለም። እኔ እስር ላይ በነበርኩበት ወቅት ባለፉት 4 አመታት የሆነውን ስሰማ፣ ተፈጥሮ የነበረው ሲኦል ሰለባዎች መሃል የዚህ የሃሰት ስብስከቶች ዋንኛ ባለቤቶች የሆነው ወያኔ፣ እቆረቆርለታለሁ የሚለው  የትግራይ ህዝብ መሆኑ አሳዝኖኛል። (27 አመት ሙሉ ሲፈናቀል ሲገደል የኖረው አማራ ከአንድ ሚሊየን በላይ ከሱማሌ ክልል የተፈናቀለ ኦሮሞ ጉዳይ እንዳሳዘነኝ ማለቴ ነው)  ይህ ህዝብ  “ትግራይ የኢትዮጵያ ቅኝ ነበረች የሚለውን የወያኔን ትረካ፣ እኛው ራሳችን በራስችን ሳናውቀው ቅኝ እንገዛ ነበር እያላችሁን ነወይ? በሚል ጥያቄ የራሱን  ኢትዮጵያዊነት አልክድም ብሎ የወያኔን የቅኝ ተገዥነት የሃሰት ትረካ ያስቀየረ የትግራይ ህዝብ ውሎ አድሮ እንደሌሎች ወገኖቹ የዘር ፖለቲካውና የጸረ ኢትዮጵያ የወያኔ ትረካ መዘዞች ዋናው ገፈት ቀማሽ ሲሆን፣ የጸረ ኢትዮጵያ ብሄረተኛነት ማሃንዲስ ባለራእይ መሪዎቹን እንዴት ይታዘባቸው ይሆን? ሌላውም በተመሳሳይ የዘረኛነት መንገድ ለመጓዝ የሚፈልግ ሃይል ከወያኔ መማር ይገባዋል። እኩይ የዘራ መልካም አያፍስምና። 

እየሰማንና እያየን ያለው ዛሬም በሃገሪቱና በህዝቧ ጫንቃ ላይ የሚፈነጩት  ህዘብ ለጋራ ማንነቱ የከፈለውን ታሪካዊ መስዋእትነት የሚያራከሱ፣ ህዝቡን በዘር ከፋፋለው አፋጠው ሊያፋጁ  የተነሱ ሃይሎች ናቸው።

የሚገርመው እነዚህ ጠባብ የዘር አጀንዳ የሚያውለበልቡ ልሂቃን ለምን ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛነት ዋናው ጠላታቸው አድርገው ያዩታል የሚል ጥያቄ ብታነሱ ሁሉም ይህ ብሄረተኛነት በሚገነባበት ወቅት በክህደት የቆመ የጀርባ ታሪካ ያላቸው የልጅ ልጆች መሆናቸውን በድፍረት ልነግራችሁ እችላለሁ። በሁለቱም የጣሊያን ጦርነቶች እነማን ሃገርንና ህዝብ ከነጭ ባርነት ለማዳን ደማቸውን በመላው የሃገሪቱ ግዛቶች ሲያፈሱ እንደነበር እነማን ሃገር ሊወሩ ከመጡ ጣሊያኖች ጋር በመሆን የገዛ ወገኖቻቸውን ሲወጉ እንደነበር ይታወቃል።

በታሪክ ዙሪያ ትረካ እያቀረቡ ወደ ፖለቲካ መግባት አይበጀንም የምንለው ለዚህ ነው። ለእያንዳንዱ በታሪክ ስም፣  በተለይ በፈጠራ ላይ ተመስርቶ ለሚቀርብ ክስ ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን የከፋ ታሪካዊ ክስ ማቅረብ ይቻላል። ታሪክን አጣቅሶ ይገባኛል ለሚል ጥያቄ ሌላው በተመሳሳይ አይገባህም የሚል ምላሽ ታሪክን አጣቅሶ ማቅረብ የሚችልባት ሃገር ናት ኢትዮጵያ።

የታሪክ ምጸት ሆኖ የዛሬውን የኢትዮጵያን ብሄረተኛነት ችግር የፈጠሩት ይህን ብሄረተኛነት የተሟላና እንከን የለሽ እንዳርጋለን ብለው የተነሱ የአርበኞች ልጆች ናቸው። በኢትዮጵያ ብሄረተኛነት ተቃጥለው፣ “የነጭ ቅኞች የነበሩ አፍሪካውያን ያገኙትን ነጻነት እንኳን እንዴት የአደዋ ድል ልጆች እንዲጠማቸው ይደረጋል” በሚል ቁጭት የሄዱበት ጥንቃቄ የጎደለው ስርነቀል የለውጥ  መንገድ ነው የፈጠረው ክፍተት ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛነትን ለማዳከም ለሚፈልጉ፣ እዚህ ግቡ ለማይባሉ ሽህ አመት ቢፋትቱ ማከናውን የማይችሉትን ሃገር የመናድ እድል የከፈተላቸው። ከሁሉም የሃገሪቱ ማሀብረሰቦችና እመነቶች የተውጣጣው ለውጥ ፍላጊ ሃይል በሚገባ ያለሰበበት የለውጥ አቅጣጫ የራሱን  እልቂት ጋብዞ ሃገሪቱን የኢትዮጵያ ብሄረተኛነት ጥላቻ እንደውርዴ በሽታ ከዘር ዘር ሲተላለፍላቸው በኖሩ በባንዳ ልጆች እጅ ጣላት።

ወገኖቼ! የአደዋ ትርጉም ድብዝዞ አፍሪካውያንና ሌላው የጥቁር ዘር በሙሉ እንዳልኮራብን ዛሬ በዘር ተከፋፍለን በዘር ስንባላ እያዩ ምን ያህል እንደሚያፍሩብን ሲነግሩን መስማት ውርደት ነው። የአፍሪካ አንድነት መሰረት ትሆናለች ተብላ በመላው የአፍሪካ ህዝብ ተስፋ የተጣለባት ሃገር የራሷንም አንድነት ማስጠበቅ የተሳናት ደረጃ ላይ መገኝቷ አሳዝኝ ነው።

የአድዋን ድል ስንቁ አድርጎ የተጀመረው የኢትዮጵያ ብሄረተኛነት ሞት የውርደታችን ብቻ ምንጭ አይደለም። የሁሉንም የሃገሪቱ ዜጎች ሞት የሚያፋጣን ነው።

አድዋ ያረጋገጠው እንደሃገርና እንደህዝብ ካልሆነ እንደሌላ ነገር መትረፍ የምንችል እንዳልነበረ ነው።

ዛሬም ሌላ አማራጭ የለንም። እንደ ሃገር እና እንደህዝብ መትረፍ የምንችለው እንደ ሃገርና ህዝብ በጋራ ስንቆም እንጂ በሃገርና በመላው ህዝብ ኪሳራ ሁሉም የየጎጡን ጥቅም በመግፋት አይሆንም። የኢትዮጵያ ብሄረተኛነት አሁንም የጎደሉት ነገሮች አሉ። እነዚህን ጉድለቶች ማስተካከል የሚቻለው ኢትዮጵያ የሚባል ሃገር ኢትዮጵያዊ የሚባል ህዝብ መኖሩን በመቀበልና በዚህ አተያይ ማእቀፍ ብቻ ነው። ፈረንጆች እንደሚሉት የተያያዝነው ህጻኑን አጥበን ህጻኑን ከቆሻሻው ጋር መድፋት የሚመስለ የጅሎች ጨዋታ ነው። እንዲህ አይነቱ አደገኛ ጨዋታ ብዙ የሚያስከፍለን እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል።

ባለንበት ወቅት የታሪክ መታጠፊው መስመር  የተሰመረ ይመስላል።  

ለእኛ በእድሜ ለገፋነውና ለዚህ መከረኛ ትውልድ ሃገራችን እንደ ቀደምቶቻችን የአርበኛነት ጥሪዋን እያቀረበችበት ያለችበት ሰአት ነው። መስዋእትነቱ ሊከብድ ይችላል።

 በዚህ አይነቱ የድልና የደስታ ቀን ገና ስለሚከፈል መስዋእትነት ማውራት እጅግ አሳዛኝና አሰከፊ ስሜት ወስጥ ሊጨመረን ይችላል። ሆኖም ግን አብዛኛዎቹ የሃገሪቱ ዜጎች ከአርበኛነት ጋር የተያያዘ ታሪክ ያላቸው የአያቶቻችው ልጆች ናቸውና ሃገር ለምታቀርበው ጥሪ የሚያኮራ ምላሽ መስጠት እንደሚችሉ ለአንድ ደቂቃም አልጠራጠርም።

ሰለአዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !

ፈጣሪ ህዝቧንና ኢትዮጵያን ይባርክ!