መጋቢት ፭ ቀን ፪፻፲፩ ዓ. ም

 በሀገራችን ኢትዮጵያ የክልል ልዩነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች መበራከታቸውና በዚህ ምክንያት የሕይወት መጥፋት፣ የህዝብ ጉስቁልናና መፈናቀል እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ለድርጅታችን ለኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማዕከል (CREW ) በእጅጉ አሳሳቢ ሆኗል።። ላለፉት በርካታ ወራት ያለመማቋረጥ በአብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ያለው ክልል ተኮር የእርስ በእርስ ጥቃት የሀገሪቱን አንድነት እየተፈታተኑት ይገኛል። ለሰሚና ለታዛቢም የሥነ ልቦናና የህሊና ጭንቀት ሆኗል።

 አሁን በቅርቡ የመንግሥት ባለሥልጣናት በሕግ እናስከብራለን ስም ሆን ብለው በለገጣፎ ነዋሪዎቹ ላይ ቤት በማፍረስ በሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን፣ ሕፃናትን አረጋውያንንና ሴቶችን ያለመጠጊያ ማስቀረት እጅግ የከፋ ግፍና ኢሰብአዊ ድርጊት መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ከዚህ ቀደም ሲል በሱማሌ፣ በጉራጌ፣ በጋምቤላ፣ በአማራ፣ በቤንሻጉል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች በቅርቡ በአዋሳ፣ በጌዶ እየተካሄደ ያለው ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለው የህዝብ 2ሚሊዮን በላይ መድረሱን ሕዝብ ለተባበሩት መንግሥታት ገልፅዋል። ይህ መፈናቀል በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ በሕዝባችን ላይ የሚደርሰው እልቂትና መከራ ሥጋታችንን በጣም ከፍ አድርጎታል።

 ይህ ብሔር ተኮር ግጭት ሕዝቡን እርስ በእርሱ እንዲፈራራ ፣ እንዳይተማመን ከማደረጉም በላይ ሀገሪቷ ለጀመረችው ተስፋ ሰጪ ለውጥ እንቅፋት ሆኗል። ስላም ሲደፈርስ ፣ ድህነት፣ በሽታ፣ ድንቁርና በሀገሪቱ ላይ ይንሰራፋል። ከማሳቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ ውስጥ በረሃብ የሚሰቃዩት የጌዶ ወገኖቻችን ሁኔታ ለዚህ ዓይነተኛ ምስሌ ነው። አሁን በቅርቡ የመንግሥት ድርጅት መገለጫ በአገራችን ኢትዮጵያ ከ8ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የረሃብ አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ ይጠቁማል። በዚህ ሁሉ አለመረጋጋትና ቀውስ የመጀመሪያዎቹ ተጠቂዎች ሴቶች፣ ሕፅናት፣ ወጣቶችና አረጋውያን መሆናቸው በተግባር እያየነው ነው። አንድ ዓመት ያልሞላው የጠቅላይ ሚኒስቴር ዶር አብይ አህመድ መንግሥት ሰብአዊ መብትን ለማክበርና በሕግ የበላይነት ብቻ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር ቃል ሲገባ ለድርጅታችን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ የምስራች ነበር። የተገኘውን የዴሞክራሲ እንቅስቃሴና አንፃራዊ የሰላም በመጠቀም እራሱንና ወገኑን ከድንቁርና ከእርዛት ለማላቀቅ ስደት ይብቃ ብሎ ለእድገትና ለብልፅግና እንነሳ በማለት ለሕዝባችን እፎይታ ለሀገራችን ተስፋ ለመሆን የህብረት ክንዳችንን በማንሳት ፋንታ በተለይ ወጣቱ መናቆር ላይ ማተኮሩ የራሱን ዕድል ከማጨናገፉ በላይ የዴሞክራሲ ተስፋውን ያጨልማል የሚል ስጋት አሳድሮብናል።

 ስለዚህ ይህ ሁኔታ እንዲለወጥ ኢትዮጵያ የጀመረችው የመልካም አስተዳደር ሕልሟ እንዲቀጥል ለኢትዮጵያ መንግሥት ፣ ለዴሞክራቲክ ኃይሎችና ለማህበረሰቡ አጠቃላይ ክፍሎች የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማዕከል የሚከተለውን ማሳሰቢያ ያቀርባል።

 ፩ኛ) የኢትዮጵያ መንግሥት በግድያው፣በማፈናቀልና ግጭቶች እንዲባባሱ የሚያደርጉትን ለይቶ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን።

 ፪ኛ) በይገባኛል ጥያቄ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚያናቁረውን ህገ መንግሥት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንዲያሻሽለው እንጠይቃለን።

 ፫ኛ) የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሕዝባዊ እንቅስቃሴ መሪዎች ይህ ቀውስ እንዲረግብና ሀገሪቱ የጀመረችውን የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ ግቡን እንዲመታ የበኩላችሁን ሀላፊነት በብቃት እንድትወጡ እንጠይቃለን።

 ፬ኛ) የኢትዮጵያ ሴቶች እናቶች ወጣት ሴቶች የሕዝባችሁ ስቃይ እንዲያበቃ የኢትዮጵያ ተስፋ እንዲለመልም ችግራችን በሰላም እንዲፈታ ግንባር ቀደም ሚና እንድትጫወቱ እንጠይቃለን።

 ፭ኛ) የኢትዮጵያ ወጣቶች ሆይ! የነገይቱ ኢትዮጵያ የእናንተ ናትና ዛሬ በስሜታዊነት የነገውን ሕይወታችሁን ለመከራና ለችግር እንዳትዳርጉት፣ ዛሬን በሰከነ መንፈስ ችግራችሁን በመወያየት እንድትፈቱት ለእውነተኛው ዴሞክራሲ፣ ለፍትህ፣ ለሰብአዊ መብት መከበር እንድትቆሙ እንጠይቃለን።

 ፮) የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች የማህበራዊ መገናኛዎችን ጨምሮ የሀገራችንን ሰላምና አንደነትን ለመጠበቅ፣ የዴሞክራሲ ሥራዓትን ለመመሥረት ትልቅ ሚና አላችሁና በከፍተኛ ኃላፊነት እንድትዘግቡ በአፅንኦት እንጠይቃለን።

 ፯ኛ) የአገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣ የሕዝባዊ ማህበራት፣ ማህበራዊ ድርጅቶችና ምሁራን ኢትዮጵያን ለማዳን የሚጠበቅባችሁን ታላቅ ሀገራዊ ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግሥት ብቻ ሳይጠብቅ ሰላሙንና አንድነቱን ለማስከበር ዘብ እንድትቆሙ እንጠይቃለን። ኢትዮጵያን የምትሉ ሁሉ የዜግነት ግዴታ እንዳለባችሁ ተርድታችሁ ለስላምና ለአንድነት ተንቀሳቀሱ። ኢትዮጵያን ለማዳን ዛሬ ነው ቀኑ ዝም አትበሉ።

          ኢትዮጵያ በሐቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኑር።

          የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማዕከል ዋሽንግተን ዲሲ