የእውቅና ፓለቲካ በኢትዬጵያ ( በሳሙኤል ፍቅረስላሴ )

በሳሙኤል ፍቅረስላሴ

ሀገር ምድሩ በስሜትና በቡድን ተከፋፍሎ መሀል ገብቶ አስታራቂ በጠፋበትና ሁሉም ፈራጅ፣ እራሱን በእውቅና ጫፍ ላይ ለማስቀመጥ በሚሮጥበት በዚህ ግዜ ሙያንና ስነምግባርን ያጣመረ እንደ ፂሆን ግርማ አይነት ሰው ማየት በጣም ያስደስታል። ዛሬ ፂሆን ግርማ (የአሜርካ ድምፅ የሬድዬ ፕሮግራም አዘጋጅ) ከአቶ ጀዋር መሐመድ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ ስመለከት የአለም ችግር መጠኑና ጥልቀቱ ቢለያይ እንጂ በአይነቱም ቢሆን በይዘቱ አንድ አይነት ነው ብዬ አሰብኩ። በምዕራባውያን የደረሰ የአየር ንብረት መቃወስ መጠኑ ቢለይ እንጂ ኢሲያውያንንም ቢሆን አፍሪቃውያንን ማጥቃቱ፤ በኢሲያውያን የደረሰው የኢኮኖሚ ቀውስ አሜሪካውያንንም ሆነ አውሮፓውያንን ማዳረሱ፤ በሶሪያ የተካሄደ ጦርነት ከምድራፍ ጫፍ ያሉ ሀገራትንና አህጉራትን፤ ኒውዝላንድንና አውስታራሊያን እንዲሁም አውሮፓንና አሜሪካን በስደተኛ ማጥለቅለቁ፤ በአውሮፓና በአሜሪካ እየታየ የመጣው የብሔርና የቀለም ፓለቲካ ኢትዬጲያንና መሰል ሀገራትን ሊያመሳቅል መቃረቡን የሚያሳይ ይመስለኛል።

በአለማችን ለባለፉት ከአምስት እስከ ስምንት የሚደርሱ አመታት በተለይ ደግሞ “ሰለጠኑ፣ ዲሞክራሲን ተገብሩ” በምንላቸው ሀገራት ላይ ለዘመናት በታሪክ ትምህርትና በመገናኛ ብዙሀን ሲወገዝ የኖረውን የብሔርተኝነትና የቆዳ ቀለም ፓለተካ በአዲስ መልክ “politics of popularity” “የእውቅና ፓለቲካ” የሚል አዲስ ስም ሰጥተው ካመጡት ሰነባብተዋል። እነዚህ የዘመን አመጣሹ ፓለቲካ አራማጆች ከሚታወቁባቸው ዋና ዋና ባህሪያት መካከል አብላጫ ድምፅ ያለውን ህብረተሰብ ችግር በማጋነንና ችግሩን አጉሉቶ በማውጣት በሰዋች ላይ ስጋትን መፍጠር፤ ይህ ህብረተሰብ የሚጠቀምበትን ማናቸውንም አይነት ባህላዊ ይሁን ሀይማኖታዊ እሴቶችን ለምሳሌ ቋንቋ፣ ዘር፣ ማንነትንና ሀይማኖትን በመጥፋት ላይ እንዳለ ወይም በጨቋኞች እየተበረዘ መሆኑን የሚይሳይ መረጃዋችን ማዘጋጀት፤ በተቃራኒው ደግሞ አብላጫ ድምፅ የሌለውን ወይም ደግሞ የሀሳብ ልዩነት ያለውን ከላይ ለተጠቀሱት ስጋቶች መንስኤ በማድረግ ኢላማ ውስጥ ያስገቧቸውን ሰዋች በፍርሀት አሽመድመደው ለበቀልና እራስን ለመከላከል በአንድነት እንዲቆሙ ማድረግ፤ በማስቀጠል ይህንን ስጋት ለማጥፋት ህይወታቸውን እንደሚሰውና ከእነርሱ በስተቀር ሌላ ሰው መፍትሄ እንደሌለው ማስመሰል፤ በተለያዩ መድረኮች በመገኘት ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጬ ንግግሮችን በማድረግና በሰዋች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሰዋች በመሳደብና በማዋረድ በጥሩም ቢሆን በመጥፎ ነገር እራሳቸውን ታዋቂ በማድረግ የሚዲያ ሽፋንን ማግኘት፤ ብዙ እውቅት ባይኖራቸውም ስለራሳቸው ሌሎች ሳይሆን እራሳቸው በመናገር የሰውን አስተሳሰብ መቀየር ናቸው። በዚህ መልክ ስልጣን ላይ ካሉ የዚህ እሳቤ አራማጆች መካከል የአሜሪካው ትራምፕ፣ የቱርኩ ኤርዶጋና የሩሲያው ፑቲን ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው። ለትራምፕ የሜክሲኮ ስደተኞችና የአክራሪ ሙስሊም ማህበረሰብ፤ ለኤርዶጋን የኩርዲሽ ህዝብና ምእራባዊያን ለፑቲን አሜሪካና -በስታን የሚያልቁ በአቅራቢያ የሚገኙ የሙስሊም ሀገራት ዋና ዋና የስልጣን በትሮች ሲሆኑ፤ በኢላማ ውስጥ ያለውም ህዝብ እነርሱ የሚያደርሱትን ጥፋት በጠላትነት ከተፈረጀው ቡድን ጋር በማወዳደር ድጋፉን ሲቸራቸው ይስተዋላል።

ይህን ሁሉ ከላይ የዘረዘርኳቸውን ምሳሌዋች ወደ ሀገራችን ብንመልሳቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ግለሰቦች መጥቀስ ብንችልም፤ ለዚህ ፅሁፍ ያነሳሳኝን እንዲያው ለነገሩ ከላይ ካሉ ሰዋች ጋር ላውዳድረውም ሆነ ቦታ ልሰጠው ባይገባም ከቃለመጠይቁ ያስተዋልኩትን የጅዋርን የእውቅና ፓለቲካ አራማጅትነት በትንሹ ልዘርዝር። በመጀመሪያ ፂሆን እየጠየቀችው ያለው የሙያዊና ስነምግባራዊ ጥያቄዋች አንድ የሚዲያ ትምህርት ለሚያጠና ሰው እንደመግቢያ ከሚማማራቸው የትምህርት ዘርፎች ውስጥ “. Journalism and politics” በሚለው ክፍል ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው። ነገር ግን ጃዋር ለነዚህ ጥያቄዋች የመለሳቸው መልሶች አንድ በሙያው ብዙ አመት አገልግያለሁ ብዙ ሀገራትንም ሳማክር ኖሬያለው እንዲሁም አንድ ትልቅ ሚዲያን አስተዳደራለሁ ከሚል ሰው የማይጠበቁና ስሜትን እንጂ እውቀትን የማያሳዩ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። በቃለመጠየቁ ወቅት መልሶቹ ሚዛን አለመድፋታቸው ብቻ ሳይሆን ጥያቄዋቹንም በአግባቡ መረዳት ስላልቻለ ጋዜጠኛዋ ምሳሌን እንድትጠቅስለትና ህጉን እንድታነብለት ሲያደርግ ተስተውሏል። በማስቀጠል ከፂሆን መስቀለኛ ጥያቄዋች ተነስተን ይህ ሰው ሙያውንና ማንነቱን በአግባቡ የማያውቅ ነገር ግን ከላይ እንደጠቀስናቸው ሰዋች ስጋቶችንና ሁከቶችን በመፍጠር እንደሙሴ ከባርነት አወጣችዃለሁ እያለ ‘ብሬን ዋሽ’ ካደረጋቸው ጥቂት የኦሮሞ ተወላጆች በስተቀር ሌላ ‘ታርጌት’ ግሩፕ እንደሌለው ያስታውቃል። በስተመጨረሻም ጥያቄውን እየመለሰ ሳይሆን ከጎኑ ያሉትን ሰዋች አለሁላችሁ እኔ ምንም ስህተት አልሰራም የሚል አንደምታ ባለው መልኩ በአዲስ አበባ ኮንደሚኒየም ጉዳይ የተናገረውን በመድገም የሚዲያ አጠቃቀሙ ልክ ከላይ እንደጠቀስናቸው ሰዋች መሆኑን እንድናስተውል ይረዳል።

ከላይ የጠቀስናቸው ግለሰቦች አንድ ከሚያደርጋቸው ነገሮች ውስጥ በስራቸው ከፈጣሪ ቃል በማስቀጠል የእነርሱን ትዕዛዝ የሚፈፀሙ ጀሌዋችን ማፍራታቸው። ለዚህም ይመስላል ብዙ ጊዜ መንግስትም ሆነ ሌላ አካላት እነዚህን ሰዋች በቀላሉ ማሸነፍ የሚከብዳቸው። ነገር ግን አንዳንድ የፓለቲካ ልሂቃን እነደነዚህ ያሉ የእውቅና ፓለቲካ አራማጆችን አንገት ለማስደፋት የሚጥቅሙ ቀላል ቀመሮችን አስቀምጠዋል፦
፩. በእነዚህ ሰዋች የሚመሩ ማናቸውንም የኤሌክትሮኒክስ ሆነ የህትመት ሚድያዋች አለመገልገልና ስለእነርሱ በጥሩም ይሁን በመጥፎ የሚወጡ መረጃዋችን ወደ ሶስተኛ ወገን አለማስተላለፍ።
፪. እነርሱ በመገልገያነት የተጠቀሙትን ህዝብ ከማግለልና ጥላቻን ከማሳየት ይልቅ እውነቱን የሚያውቅበትን መንገድ መፈለግ።
፫. በተቻለ አቅም የግለሰብ ፓለቲካን ከማራመድ ይልቅ የፓርቲ ፓለቲካ እንዲስፋ በማድረግ ለሚደርሱ ጥፋቶች አንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን የተለያየ ሀሳብ ያላቸው ቡድኖችን ተጠያቂ ማድረግ።
፬. በመጨረሻም በቂ የሆነና የተሟላ መረጃ በማሰባሰብ ግለሰቦቹ ያላቸውን የግልም ይሆን የቡድን ጥፋትና ድክመት በመፈለግ በመጀመሪያ ኢላማ ውስጥ በገባው ህዝብ ተቀባይነትን ማሳጣት በመቀጠለም ሀገሪቷ ባላት ህግ ተገቢውን ፍርድ እንዲሰጥ ማድረግ የሚሉ ናቸው።