” ድሉን ማንም ወደ ኋላ አይመልሰውም ” ጠ/ሚ ዶክተር አብይ አህመድ

አባይ ሚዲያ ዜና

ጠቅላይ ሚንስትር  ዶክተር  አብይ አህመድ የድርጅታቸውን የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲን (ኦዴፓ) 29ኛ የምስረታ በአል አከባበር በማስመልከት መልክት አስተላልፈዋል።

የድርጅቱን የምስረታ በአል አከባበር ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንንም ተካፍለዋል።

በጠቅላይ ሚንስትር  ዶክተር  አብይ አህመድ  ጽህፈት ቤት የተከበረው የኦዲፒ 29ኛ አመት የምስረታ በአል የድርጅቱን የ6 ወራት የስራ አፈጻጸም መገምገሙም ተዘግቧል።

በዚሁ የአክበባበር ስነስርአት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር  ዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረውን የለውጥ እና የድል ጎዳናን ማንም ሊቀለብሰው እንደማይችል ገልጸዋል።

በኢህአዴግ ውስጥ የሚገኙ እህት ድርጅቶችም በመተባበር ኢትዮጵያን ለተሻለ ደረጃ ማብቃት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚንስትሩ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሊቀ መንበርነት ለሚመሩት ድርጅታቸው (ኦዴፓ) ባስተላለፉት መልክት የድርጅታቸው የትግል ውጤት የትኛውም ሃሳብ በነጻነት የሚንሸራሸርበትን ኢትዮጵያን መፍጠር እንጂ ሃሳቦች ማፈን እንዳልሆነ አስረድተዋል።

አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ መኖሪያ እንደሆነች በመግለጽ ሌሎች የአገራችንን ከተሞች ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የኔ ናቸው እንደሚለው አዲስ አበባም የኢትዮጵያውን ናት በማለት ጠቅላይ ሚንስትር  ዶክተር  አብይ በድርጅታቸው የምስረታ በአል አከባበር ላይ ተናግረዋል።

ለውጡን የሚያደናቅፉ አስደንጋጭ ሃሳቦች ሊሰሙ እንደሚችሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ በእንደዚህ ያሉ ሃሳቦች ሳይደናገጡ መስራት እንደሚገባ ለተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል። በተመሳሳይ መልኩ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንንም ለውጡ እንዳይሳካ የተደቀኑትን ፈተናዎች ለመወጣት በጋራ መስራት እንዲሁም ያልተመለሱ ጥያቄዎችንም ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ  በዚሁ የኦዲፒ 29ኛ የምስረታ በአል አከባበር ላይ ተናግረዋል።