ለማን ለማን ይጨብጨብ ( ግርማ ቢረጋ )

የሃገራችን ኢትዮጵያን የለውጥ ጎዳና በመጥረግ እና በማቆሸሽ ሂደቱ ላይ ሌላ ማንም ሳይሆን እኛው ኢትዮጵያውያን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ እራሳችን ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አድርገናል እያደረግንም እንገኛለን ። ለሚመጣው ነገር ሁሉ ኃላፊነቱ የጋራ እንዲሆን አድርገን ብንሰራው ስራችንም ብዙም  በስህተት አይጨማለቅም  ነበር ባይ ነኝ ይህም ማለት ከበይ ተመልካችነት ወጥተን ሃገራችን  ሊኖራት ስለሚገባው ዲሞክራሲ ያለንን አስተዋፅኦ ማበርከት ይኖርብናል ፣ ይህን ሳናደርግ ቀርተን ሌላው ሞቶ በሚያመጣው ነፃነት ላይ ለመቆም መውተርተር  በእርግጠኝነት ከሰውነት የመውረድ ማረጋገጫ ነው የሚሆነው።

ስለነፃነት ብዙዎች መስዋዕት ሆነዋል ብዙዎችም አካላቸውን አጥተዋል ፣ አያሌዎች በስደት አለም አካላቸው በስለት ተተልትሏል ብዙዎችም ሃገሪቷ የብቻቸው እስክትመስል ድረስ  ዕድሜያቸውን ሙሉ ስለ ሃገራቸው ነፃነት ታግለው አታግለዋል ።

በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ የለውጡን ጎዳና በመጥረግ ሃገራችን ወደ ተሻለ አቅጣጫ እንድትሄድ እጅግ ማስተዋል ባለበት ሁኔታ ግራ ቀኙን በማየት የሚጓዙትን ያህል በዛው ጎን ተሰልፈው ግን ለውጡን አጣድፈው ኢትዮጵያችንን ከአለችበት ሁኔታ ወደፊት በረጅም እርቀት ሊያስፈነጥሯት የሚፈልጉ ነገር ግን በጎዳናው ላይ ግራ እና ቀኝ ተሰልፈው እንቅፋት የሚሆኑትን ያለማስተዋል በሚጓዙበት  ሁኔታ ወይም በሚያደርጉት እሩጫ ግሳንግሱን ጠራርጎ እና  ረጋግጦ ለማለፍ ፍላጎት እና ህልም ያላቸው እንዳሉም ማየቱም ግድ ይላል ነገር ግን ረግጠነው በሄድን ቁጥር በውስጣችን ልናስተውል የሚገባው ነገር ቢኖር እሩጫው ተሳካም አልተሳካ የመጨረሻውን መስመር ስናልፍ ተጠያቂነቱም አብሮ መምጣቱ እንደማይቀር መገንዘቡ ላይ ነው ። የሄን ስል ባለ ጉዳዮቹ አይገነዘቡትም ማለት ሳይሆን ባለፍንበት ሃያ ሰባት ረጅም አመታት ውስጥ  የሃገርን ክብር እና ሃብት ከመዝረፍ ባለፈ በሰብአዊነት ላይ ከየትኛውም አለም ያላየነውን ግፍ እና መከራን በራሳቸው ህዝብ እና ወገን ላይ የፈጸሙ የዘመናችን እኩዮች አሁን እስካለንበት ሰዓት ድረስ በሆቴል የውስኪ ብርጭቆአቸውን ጨብጠው ትንባሆአቸውን እየማጉ ሽቅብ የሚያቀረሹ የሃገርን ሃብት ዘርፈውና ሃገሪቱን መቀመቅ ውስጥ ከተው ልጆቻቸውን በሰለጠነው አለም በውጭ ምንዛሪ ከፍለው የሚያስተምሩ እንዲሁም ለልጆቻቸውም ሆነ ለመላው ቤተሰቦቻቸው የማይናድ ክምር ሃብት በየስማቸው አስቀምተውላቸው በሌላኛው መንገድ ግፉ አልበቃ ብሏቸው በደቀቀ ህይወት ውስጥ መስዋዕትነት ከፍሎ እዚህ መሰላል ላይ የተንጠለጠለውን ህዝብ ለማባላት እጃቸው የረዘመ የዘመናችን እርኩሶች / ይሄን ስል ግፉ ተገልፆ ሊያልቅ የማይችል በመሆኑ እያሳጠርኩት ነው / ፍትህ አለማግኘታቸው አሁን እየተደረጉ ላሉ  ስህተቶች አስተዋፆው የትየለሌ ነው ።

ተጠያቂነት ሲኖር የሰው ልጅ አሁን ላለው እና ለሚፈፅመው ማንኛውም ተግባር ተኩረት ዋስትና በመግባት እራሱን ከስህተት በአቀበ አካሄድ እንዲሄድ ሊረዳ ይችላል  የሚል እምነት አለኝ ሆኖም ግን ከበቀል ርቀን ከማጥፋት ይልቅ ማስተማር እና ይቅር ባይነትን በማስተማር  ከአጥፊዎች የተሻልን መሆናችንን በግልፅ ማሳየት ይገባናል ይሄም ሲሆን በዋናነት መንግሥት በተሸፋፈነ መንገድ ሳይሆን ሃፍረት በሌለበት ሁኔታ ስህተቱን እርቃኑን አውጥቶ በመነጋገር ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን የሚባልበት እልባትን ማስረገጥ ይኖርበታል ይህም ከራስ ሲጀምር ተቀባይነቱ ወለል ብሎ እንዲታይ በር ይከፍታል።

ለውጡን የሚመሩትም ሆነ የለውጡ ሃሳብ ተስማምቷቸው ከለውጡ መሪዎች ጋር በትልቋ መርከብ ተሳፍረው በዝምታ የሚቀዝፉትንም ዝምታን ለምን መረጡ በሚል እጅግ ብዙ ትችቶች እና ከዛም ባለፈ እሰጥ አገባ ውስጥ ተገብቶ ግለሰቦችንም ሆነ ድርጅቶችን ፍፁም አድርገን የምንጠብቀወ እስኪመስል ድረስ በብዙ ጉዳዮች ላይ ላለመስማማት የተስማማን መሆናችንን በግልፅ እያሳየን ስህተቶች ሊታረሙ እንደሚችሉ አውቀን እንኳን ለተሳሳቱ ዜጎች የማስተካከያ  ጊዜ ከመስጠት ይልቅ  ከዛም ባለፈ ሃሳቦችን በተቃወምን ቁጥር እራሳችን   አግዝፈን እንደ እሩጫው ሁሉ ጋራ ቀኙን ባለማየት ሃሳቦችን ላለመሞገት ወይም ምንም ነገር ላለመስማት ጆሮዋችንን ደፍነን ብቻ የጭቃ ጅራፋችንን ማወናጨፍ ላይ እንሰለፋለን ነገር ግን የተሰነዘሩት የቃላት ጥቃቶች ሁሉ ከግለሰቡ ጆሮ ነጥረው ወደ ምስኪኑ ህዝብ ይገቡና ባለው ድህነት ላይ መረጋጋት እንዳይኖረው የመጥፎ ነገር ደወል ይሆንበትና ተስፋ ቆርጦ  ለስደት እንዲዳረግ ያስገድደዋል ። ስደቱንም ብዙ ልንልበት እንችላለን ነገር ግን ስደቱን መተረክ ሳይሆን መረጋጋት ለመፍጠር ሲባል ብቻ ከንፈር መጠጣውን ትተን ሃላፊነት ወስደን አስከፊነቱን ብቻ ሳይሆን ነፃነቱን ለማስመለስ አብሮ መሬት ወርዶ ማሳየትን ማስተማር ግድ ይላል።

ከሚገርመው ነገር ሁሌም የሚሆነው መንግሥት አብዝቶ ዲስኩር ያሰማል ዲስኩር ምግብ ወይም ነፃነት የሚሆን ይመስል  እኛም እናጨበጭባለን የግድ ነዋ ነገር ግን የኛስ ይሁን  የጭብጨባው አድማቂዎች ምሁራንም መሆናቸው ከምንም በላይ የሚገርም  ነው  ፣ ዝም ካልክ ደግሞ ሃይ ባዮች ይነሱና  ለምን በሚል ስሜት በግልምጫ ያነሱናል ይሄኔ ነው እንግዲህ  በእርግጥም የተነገረን  ሁሉ ገብቶን ነው ወይ ያጨበጨብነው ? አይመስለኝም ማለቴ ምክንያቱም ለመንግሥት ዲስኩር ያጨበጨብነው እኛ እራሳችን በሰከንዶች ውስጥ የተቃውሞ የመልስ ምት በሃቀኞች  ወደ መንግሥት ግብ  ሲመታም እንደውም ጎሉ ከመግባቱ በፊት ተናጋሪውን ካወቁትማ  በቀብድ መልክ ለተናጋሪው ቀድመን እናጨበጭብለታለን  ከዛም ባለቤቱ ሃሳቡን በቅጡ ከማስተላለፍ ይልቅ በግርምት  ውስጥ ሆኖ   የጉድ ሃገር ብሎ ያሳላስላል ፣ ይሄኔ ነው እንግዲህ የመንግሥት ተብዬው ፊታውራሪዎች  ያ የነጋዴው /ትሁቱ /  አንደበታቸው ተቀይሮ ዛቻ እና ማስፈራሪያ የሚተፋው ለምን ቢባል በተቃውሞም ሆነ በድጋፍ የምናጨበጭብ መሆናችንን ያውቃሉና ።

ለነገሩ አሁንማ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ለምን አንዳንዶች ብቻ ይጠቀሙበት አይነት ሆኖ ነው መሰል  እነሱ ጫማ ሲልሱ ከነበረበት ዘመን ጀምሮ ስለ ሃገር እና ህዝብ ነፃነት ሲታገል የኖረን ቆራጥ የነፃነት ታጋይ ” የድል አጥቢያ አርበኛ ” ብለው መዝለፉን ተያይዘውታል  ለነገሩ ማንን ታሸንፋለህ ቢሉት አይነት ሆኖ እነሱ በሚመሩት ሃገር ላይ በጠራራ ፀሃይ 17 ባንኮችን የዘረፈ ፅንፈኛ ፈርቶ የነፃነት ታጋዮችን ለማስፈራራት የሚደረገው መፈራገጥ እራስን እርቃን ከማስቀረት በዘለለ ጠቀሜታው እጅግም ነው ። ለነገሩ አንባገነን መሆን ሲያምርህና ስልጣን እየጣፈጠህ ሲሄድ ሂሊናህ ይደፈንና በብዙ ጭብጨባዎች ሰክረህ ምንም ቢሉህ የምትሰማ ልትሆን ትችላለህ ፣ ከሁሉ ከሁሉ የሚያስተዛዝበው ኢትዮጵያን የመሰለች ሃገር ብዙ ምሁራን እያለዋት ልክ ማህፀንዋ የደረቀ አሽቃባጭ አሮጊት ይመስል ሁሌም በየ አደባባዩ አንድ አይነት ፊቶች ግዴታ የተጣለባቸው ይመስል ሲታክቱ ማየት ራሱ ለእናንት ተማርን ለምትሉ በየጉሮኖው እውቀትን ታቅፋችሁ ከግሳታችሁ በቀር ድምፃችሁን የማንሰማችሁ ምሁራን የታቀፋችሁትን እውቀት ሌላው ቢቀር ፖለቲካውን ወደ ጎን ትታችሁ ወጣቱን በስነ ስርዓት ለማነፅ ብትተጉ በአደባባይ በደማቸው መስዋዕትነት ከከፈሉት ጀግኖች እኩል ክብር በኖራችሁ ነበር ። ለነገሩ ምሁር ማለት ፈሪ ማለት ነው የሚል ተማሪ እያፈራችሁ እንደሆነ እያየን ነው ፣ ያ እንዳይሆን ኢትዮጵያውያን ምሁራን  ውጡ እና ኢትዮጵያን ታደጉዋት ፣ ወጣቱን በስነ ልቦና አንፁት ፣ ኢትዮጵያ ማለት የጥቂቶች ብቻ አለመሆንዋን ስበኩ እኒያ የናነተ ወላጆች እናንተን  ሞፈር ጨብጠው መሬትን ገምሰው እና ገልብጠው ነው ያስተማሯችሁ ነገር ግን ያ የቤተሰብ መስዋዕትነት በናንተ ውስጥ ሊታይ አልቻለም ። ለነገሩ እናንተ ምን በወጣችሁ ሞፈር አይደለም ብዕር ጨብጣችኋል  እነሱ ግን አሁንም ሞፈር እንደጨበጡ ነው። አንተ ስተወለድ የተጠቀለልክበትን ጋቢንም ተንከባክቦ ዛሬም እሱኑ እየለበሰ ነው ሌላ ቅያሪ የለውም ከአንተ ሳይማር ካስተማረህ ልጁ ሌላ ንፁህ ጋቢ እየጠበቀ ነዋ።

 ? ታዲያኮ  ክሽፈት ማለት ይሄ ነው የከሸፈ ምሁር። ከማረሻ የሰላ ብዕር ጨብጦ ማንቀላፈቱ ይቅር። /  ጥቂቶች ልፋታችሁ መና አይቀርም /

አፕሪል  2019

ስቶክሆልም