ሰሜን ሸዋ የጦር መሳሪያ በታጠቁ ሃይሎች ከፍተኛ ጥቃት ደረሰባት

አባይ ሚዲያ ዜና 

ከፍተኛ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሃይሎች በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ አከባቢዎች  በንጹሃን ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መክፈታቸው ተገለጸ። 

የታጠቁት ሃይሎች እነማን እንድሆኑ በስም መጥቀስ ያልፈለጉት የአጣዬ ከንቲባ የሆኑት አቶ ጌታቸው በቀለ ከትላንት መጋቢት 28 ቀን 2011 አም የጀመረው የታጣቂዎቹ ጥቃት ዛሬም ቀጥሎ እንደዋለ ገልጸዋል። 

ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ታጥቀው ጥቃት እያደረሱ የሚገኙት ቡድኖች በትንሹ 9 ንጹኋን ነዋሪዎችን መግደላቸውን እንዲሁም በርካቶችን ለጉዳት መዳረጋቸውን  ከንቲባው አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። 

ከግድያ እና ከጥቃቱ በተጨማሪም የቤት ውስጥ ዘረፋ እንዲሁም ሰዎችን አፍኖ የመውሰድ ወንጀሎችም በነዚህ የታጠቁ ሃይሎች ተፈጸሟል ተብሏል።

ከፍተኛ የጦር መሳሪያ በመታጠቅ በሰሜን ሸዋ በሚገኙ አከባቢዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየፈጸሙ የሚገኙት እነዚህ ሃይሎች በእምነት ቤቶችም ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ተገልጿል። 

የኤፍራታና ግድም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደምሰው መሸሻ በበኩላቸው ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የታጠቁ ሃይሎች  ንጽሃን ሰዎችን በመግደል የእምነት ተቋማት ላይም ጥቃት ማድረሳቸውን ተናግረዋል። 

በቦታው የተገኘው የመከላከያ ሰራዊት ሁኔታውን ለማረጋጋት እንደተቸገረ  ዋና አስተዳዳሪው  አቶ ደምሰው መሸሻ በተጨማሪ ገልጸዋል።

ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን እንዲሁም ቦንቦችን በመጠቀም ይህን ያህል ወንጀል እና ወረራ እየፈጸሙ ያሉትን ሃይሎች በይፋ የመንግስት አካላት መግለጽ ባይፈልጉም  ብሄር ላይ  ያተኮረ ጥቃት እንደሆነ  እየተነገረ ይገኛል።

በዚህ አረመናዊ ጥቃት ህይወታቸውን በአሳዛኝ መልኩ ባጡ ዜጎቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን።